የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ባደረጉት የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከካፋ ጉርማሾ (ወጣቶች) የተላለፈ መልዕክት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በቦንጋ ከተማ ሰኔ 27/2010 ላይ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በሀገራችን እያመጡ ላሉት ሁለንተናዊ ለዉጥ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ባደረጉት የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከካፋ ጉርማሾ የተላለፈ መልዕክት!!!!

ዉድ የዚህ የመደመር ሰልፍ ታዳሚዎች እንኩን ለፍቅር እና ለሰላም ቀን አደረሰን!!

“ቃል ይተክላል”

ቃል ይነቅላል

ይህ የኢትዮጵያ ተስፋና የምጥ አዋላጅ የሆነዉ የጠቅላይ ሚ/ራችን የዶ/ር አብይ ድምጽ ነዉ!!

እዉነት ነዉ!

ቃል ያፈርሳል ቃል ያንፃል!

ቃል ያቆስላል ቃል ያግማል!!!!

በተለይም የህዝብ መሪዎች ከሆኑ ግለሰቦች አንደበት የሚፈልቁ ቃላት ለበርካታ ህዝብ እልቂት ፍጅትና መፈናቀል ምክንያት ሆነዉ አልፈዋል። በተቃራኒዉ እነ ማንዴላና ጋንዲን የመሰሉ መሪዎች አንደበት መቃቃርን መፋጀትንና ጥላቻን አስወግደዉ ፍቅርን ምህረትንና መቻቻልን አዉርደዉ፤ ህዝቦች ተደምረዉ ወደ እድገትና ልማት እንዲያመሩ አድርገዋል:: የዚህን አባባል ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ብዙም ሳንጉዋዝ ያለፉትን ጥቂት አመታት ክስተቶች ካለፉት ጥቂት ወራቶች እዉነቶች ጋር ማነጻጸር ብቻ በቂ ነወ።

በዚህ ሰዓት በዚህ ቦታ የተገናኝነዉም የዚህን የእዉነተኛዉን የፍቅር፤ የመደጋገፍ፤ የይቅርታና የሰላም ሀሳብ ከፍ አድርጎ ያነገበዉን፤ በነገየቱ ሀገራችን : “ከየትም ይምጡ ከየትም ይወለዱ” በፍቅርና በወንድድማማችነት አብረዉ የሚፈነድቁ ልጆቻችንን ለማያት የሚያስችለንን ራዕይ አንግቦ መራመድ ለጀመረዉ መሪያችን ድጋፋችንን ልንሰጠዉ፤ ልናበረታታዉና ከጎኑ መቆማችንን በማረጋገጥ ጉልበት እና ሀይል ልንሆነወ ነዉ።

ዉድ የመደመር ሰልፍ ታዳሚዎች

ዓለም ለሰዉ ልጆች የተሰጠች መኖሪያቸዉ ስፍራቸዉ ነች። ይህችን ሰፊና በቂ የሆነች መኖሪያ፤ ጥቂቶች በፈጠሩትና በሚፈጥሩት ብጥስጣሽ የአጥር ክልል ምክንያት በመሰናክሎችና ግጭቶች የተሞላች እንድትሆን አድርገዋት ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ዛሬ ዛሬ ዓለማችን ለአንድነት እየተጋች ወደ አንድ መንደርነት እየተሰበሰበች ፈጣሪዋ እንዳበጃት እንደመጀመሪያዉ ለመሆን እየተንጠራራች ትገኛለች።

የሰዉ ልጆች ከመካከላቸዉ ካሉት ልዩነቶች ይበልጥ አንድ የሚያደረጉቸዉ የጋራ ፍላጎቶች፤ በአንድነት ብቻ ሊወጡአቸዉ የሚችሉቸዉ ችግሮች እንደሚበልጡባቸዉ በማመን ለመደመር እና ለመፈቃቀር፤ ለሰላም እና ለአብሮነት ዕለት ተዕለት እየተጉ ይገኛሉ። …………… እኛም ከእርስ በርስ የድሃ ወንድማማቾች ጠብ ልንወጣ ጎህ ቀዶልናል።

እያንዳንዱ ዘመን የራሱ ጎርፍ፣የራሱ ፍሰትናየራሱ ደለል አለዉ። የጎርፉን ዉሃ የከተረና ኩሬዉን የሞላ ብልህ በረኽኛ ደለሉን በአግባቡ የተጠቀመ ታታሪ አምራች መጪዉን በጋ በብልጽግናና ደስታ ሲወጣዉ ጎርፉ ያስከተለዉን ጉዳት ሲተርክ የወሰደበትን እንስሳት ሲቆጥርና ሲያሰላ የሰነበተዉ ግን ከጎርፉ በበለጠ በጋዉ ይበረታበታል። በጎርፉ ላይ ቂም ቢይዝ፤ ጥርስ ቢነክስ- ትርፉ ነገን ማጨለም ብቻ ነዉ! ጎርፉ አልፎአል!!!!

ዉድ ወገኖቼ

የጠለለና ኩልል ያለ ታሪክ በዓለም ላይ አልታየም።የዛሬዎቹ ታላላቅና ሀያላን ሀገራት ምስረታ በዉይይትና በስምምነት የተካሄደ ሳይሆን በአስከፊ ጦርነትና መሸናነፍ የተሞላ ነበር። ዛሬ የነዚህ ሀገራት ህዝቦች ታላቅ የሆነችዉ የሀገራቸዉን መመስረት እንደገድል ሆነዉ ይዘክሩታል፤ ዛሬን እንዴት መኖር እንዳለባቸዉ በእዉቀት ላይ ተመስርተዉ ይመክሩበታል እንጂ በሂደቱ የተፈጠረዉን ጉድለትና የግጭቶችን ጠባሳ እያነሱ በመቆዘም እርስበርሳቸዉ የሚጠፋፉበትን የቂም ቐያ እያቀጣጠሉ በእቶኑ አይለበለቡም። እኛ ኢትዮጵያዊያንም ከልዪነታችን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን እሴቶችና የሚያስተሳስሩን ጉዳዮች እጅግ የበዙና ተቆጥረዉ የማያልቁ እንደሆኑ በመረዳት መደመር እንጂ መለያየት እንደማይጠቅመን የምናምን ጥንትም በዉስጣችን የነበረ ህዝቦች ነን። የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የእንደመር ጥሪ መላዉን ኢትዮጵያዊ “ሆ“ ብሎ እንዲቀበለዉ ያደረገዉም ይህ መለያየትን የመጥላትና ፍቅርና መደመርን የመዉደድ ዉስጣዊ አቁማችን ነዉ።

እኛ ካፌቾዎች ደግሞ በዚህ ረገድ የምንዘክርና በኢትዮጵያዊነት ተምሳሌነታችን የሚተረክ ታሪክና ጽናት ያለን ነን። “ይህ ክልል የእኔ ብቻ ነዉ………… ከክልሌ ዉጣ”…… ማለት ብሒል በሆነባቸዉ የኢትዮጵያ ጥቁር ታሪክ በተመዘገበባቸዉ ዓመታት ጨዋነታችንን አስመስክረናል። ነገ ወንድሞቻችንና ልጆቻችን በየትኛዉም የኢትዮጵያ አካባቢ በኩራት አንገታቸዉን ከፍ አድርገዉ እንዲኖሩና እንዲሰሩ አኩሪ ታሪካችንንና ኩሩ መሆናችንን አዉርሰናቸዋል። ይህ ፅናትና ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ከጥንት አባቶቻችን የተማረነዉ ለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ምስክር ናቸዉ። ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ “መለያየት ሞት ነዉ” በሚለዉ መፃህፉ ላይ እንዳሰፈረዉ በካፋዉ ንጉስ ጋኪ ሻረቾና በአፄ ምኒሊክ ጦር መካከል በተካሄደዉ ከፍተኛ ዉጊያ ከዑጋንዳ የእንግሊዝ ጦር ለካፋዉ ንጉስ ለቀረበላቸዉ የእንርዳዎት ጥያቄ ንጉሳችን ጋኪ ሻረቾ የሰጡት….. “በወንድማማች ፀብ ዉስጥ ምን አገባህ?” የሚለዉ ምላሽ ዛሬም ነገም የምንኮራበት የኢትዮጵያዊነታችን ማህተም ነዉ። ከዚያም በመለስ የካፈቾ ዘማቾች በማይጨዉ ጦርንት የፈፀሙት ገድል የሚዘከርና፤ የከሰከሱት አጥንት ከሌሎች መስዋዕት ወንድሞቹ ደም ጋር ተደባልቆ በሰሜን ኢትዮጲያ፤ ኢትዮጲያ ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።

ውድ የቦንጋና የአካባቢዉ ነዋሪዎች

የዉድ መሪያችን የኢትዮጲያዊነትና የመደመር ምናብ ከሀገራዊ ጥምረት ባሻገር የእያንዳንዱ ዜጋ አዕምሮ መፈታትን የሚያመላክት ነዉ። ዜጎች በክልል አጥር ዉስጥ እንድንኖር ብቻ ሳይሆን፤ ተለክቶ በተሰጠን አሰተሳሰብም ዉስጥ ብቻ እንድናስብ መሆናችን፤ ነፃነት ያሳጣን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባችን እና ምናባችንን እንዲቀጪጩ አድርጎን ቆይቱአል። በነፃነት ማሰብ ፣መፃፍና መናገር የተከለከለ ትዉልድ፤ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት ለመሆን በፍፁም አይቻለዉም!!!

ኢትዮጲያዊያን ያሳለፍነዉ የሚገርም ዘመን ነዉ። …….“እኔ ስሰርቅና ስዘርፍ እንኩን መናገር ማየት ምን ፈቀደልህ?” ማለት ምን አይነት አይን አዉጣነት ነዉ? “ስዘርፍ እንዳታይ….. ተነካከስ እንጂ አትሳሳም ” ማለት ምን የሚሉት ቢህል ነዉ? “እኔ በማምንበት አስተሳሰብ ብቻ ተመራ!” በሌላ መንገድ ካሰብክ፤ ሌላ አማራጭ ካከረብክ የሀገሪቱ ጠላት እንደሆንክ ተቆጥሮ፤ የተለያየ ተቀፅላ እየተሰጠህ እንድትገለል፣ እንድትሰደድ፤እንድትታሰር መደረጉ ቀርቶ ማንኛዉም ዜጋ ለሀገሬ ይበጃታል የሚለዉን ማንኛዉንም ሀሳብ በነፃነት አቅርቦ ህዝቡ ዳኝነት እንዲሰጥ የሚደረግበት ስርዓት ለመፍጠር ዶ/ር አብይና አጋሮቻቸዉ የጀመሩት እርምጃ—በኢትዮጲያ የነፃነት ቀንዲል የተሎከሰበት የታሪክ ምዕራፍ ነወ!!!

ዶ/ር አብይ አህመድን ለመደገፍ፣ ለማወደስና ከጎኑ መቆማችንን ለማረጋገጥ በዚህ አደባባይ የተገኘነዉ ቃሉ የፍቅርና የይቅርታ፤ የኢትዮጲያዊነትና የመደመር በመሆኑና እነዚህን ሀሳቦች ወደ ተግባር እየለወጠ የሚገኝ ስለሆነ ነወ። ጠቅላይ ሚኒስቴራችን የፈሪ ፖለቲከኛን የጥርጣሬ፤ የዜጋን ስለላና የጠላትነትን ስሜት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበሩ፤ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የይቅርባይነትና የሰላም መሲህ ናቸዉ። “ መጋደልንና ቂም በቀልን፤ በይቅር ባይነት ድል እንንሳ!” የሚል በራሱ የሚተማመን መሪ፣ ሊደገፍ እና ሊወደስ ይገባል።

ዉድ የዚህ የመደመር ሰልፍ ተሳታፊዎች

ማንኛዉም በጎ ሀሳብና ቀና ተግባር ተፃራሪዉን እንዳያጣ የአለም ተፈጥሮ ሆነና፤ ይህ የሰላም የመፈቃቀርና የይቅርባይነት ሀሳብም የሚፃረረዉ አላጣም። ባለፈዉ የአዲስ አበባዉ የድጋፍና የመደመር ሰልፍ ላይ የተወረወረዉ ቦንብ፣ የእዉቁን የአገራችንን ገጣሚ የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን ግጥም ያስታዉሰናል፤

“የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለዉ፤

የጅምሩን ካልጭረሰዉ?

የተበደለ ቢችልም፣

ቢሸሸግም ቢደበቅም፣

የበደለ ዝም አይልም።

…………..

ዝም ካለማ ጉድ ፈላ፣

ነገር በጤና ሲብላላ፣

እያደር ሲጠራ በዋላ፣

ግፉ ይፋ ይሆናላ። ………………………………………………………..ያሉት ተፈፀመ።

በመሆኑም ቦንብ ወርዋሪዎችና አጋሮቻችሁ፤ በሰላም፣በፍቅርና በይቅርባይነት ላይ ያነሳችሁትን የሲኦልና የጨለማ እጆች እንድታነሱ በጥብቅ ለማሰጠንቀቅ እንወዳለን።

ዶ/ር አብይን መደገፍ

ፍቅርን መደገፍ ነዉ!!!!!!

ሌላዉ በዚህ አጋጣሚ ሳናነሳዉ የማናልፈዉ ጉዳይ፣ ገጣሚ ኤፍሬም ስዪም እንዳለዉ እኛ ማለት …..

የአንድ አፈር አፈሮች፣

የአንድ እናት ልጆች፣

ወንድምና እህቶች……………………….ሆነን ሳለ በጨና ና ሺሾ እንዴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረዉ ግጭት የቦንጋ ከተማ ወጣቶች እና የዚህ ድጋፍ ሰልፍ አስተባባሪዎች በጣም ያዘንን መሆናችንን እየገለፅን የቦንጋ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ከሚመለከተዉ ጋር በመሆን ይህንን ቸግር በአስቸኩይ እንድትፈቱ በትህትና እንጠይቃለን።

በመጨረሻም – የሰለፉ አስተባባሪዎች

ሀሳባችንን ግራ ቀኝ ሳንገላምጥ፣ በነፃነት ለመናገር እንድንችል መስዋትነት ለከፈሉ ወገኖቻችን ምስጋና እና ክብር በመስጠት፤

ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ በቃችሁ! ያለንን ፈጣሪያችንን ለማመስገን እንወዳለን!

ፈጣሪ ኢትዮጲያንና ህዝቦቹአን ይባርክ

የቦንጋ ከተማ ወጣቶች (የካፋ ጉርማሾ)

ሰኔ 27 2010

ቦንጋ/ ካፋ

እናመሰግናለን

Share.

About Author

Leave A Reply