“የተጀመረዉ ለዉጥ እጁን መሰብሰብ ያለበትን ኃይል እጁን እንዲሰበስብ ያደርጋል”፡- አምባሳደር ትርፉ ኪዳነማርያም

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

“የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተጀመረው ለውጥ እጁን መሰብሰብ ያለበትን ኃይል እጁን እንዲሰበስብ ያደርጋል” ሲሉ በአውስትራሊያ የኢፌዴሪ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ትርፉ ኪዳነማርያም ተናገሩ፡፡

“የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለዉጥ ለሕዝባችን እፎይታን ያስገኘ ነዉ፤ የሕዝብን መንፈስ የመገንዘብ እና የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ ነዉ፡፡ በየክልሉ እየዞሩ ሕዝቡን ማወያየታቸውም መልካም ጅምር ነው” ብለዋል አምባሳደሯ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካን ችግሮች እና የሰላም ዕጦት ለመፍታት እየወሰዷቸው ያሉ እርምጃዎችም ያደነቁት አምባሳደር ትረፉ ከዓረብ ሀገራት ጋር የጀመሩትን ዲፒሎማሲ፣ ታራሚዎችን በአጭር ጊዜ እንዲፈቱ ማድረጋቸውንና ይቅርታ ማድረጋቸውንም አድንቀዋል፡፡
አምባሳደሯ በአዲስ አበባ ሰኔ 16 ቀን በምስጋናና ድጋፍ ሰልፉ ለሞቱት ቤተሰቦች እና ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ “የጥቃት እና ጥፋት ሥራ የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም፡፡ ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲጠራጠር የሚያደርጉ አካላት ተገቢውን ፍርድ ማግኘት አለባቸዉ” በማለት አሳስበዋል፡፡

“ሁሉም የተለያዩ አመለካከቶቹን በነጻነት የሚያንጸባርቅበት ዕድል ተመቻችቷል፡፡ ወጣቱ እና ሠርተዉ ያልደከሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ምሥራቅ አፍሪካን አንድ የማድረግ ዕቅዳቸዉ እንዲሳካም እመኛለሁ” ብለዋል፡፡

ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ የሚፈልጉ አካላት የይቅርታ እና የሰላም ጥሪዉን ደግፈዉ ቢሠሩ እንደሚሻላቸውም መክረዋል፡፡ “ለሀገር ስጋት የሚሆኑ አካሄዶችን ለይቶ ማዉጣት እና በሩቁ መመከት የሚችል የጸጥታ መዋቅር መዘርጋት ስፈልጋል፡፡ ዋናዉ አደጋችን ሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ነዉ፤ ይህ ሀገርን ያጠፋል፡፡ ዶክተር ዐብይ የጀመሩትን ሙስናን የማጥፋት እርምጃ ሁሉም ሊተባበር እና ሊደግፈዉ ይገባል”፡፡

ከቀበሌ ጀምሮ በኪራይ ሰብሳቢ እና በሙሰኞች የተጨማለቁትን ማጋለጥ እና መታገል በተለይም ከለዉጥ ፈላጊ ወጣቶች እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከግምገማ ያለፈ ጠንካራ የመተካካት ሥራ መሥራትና ያለውን የትውልድ ክፍተት መሙላት እንደሚገባም አምባሳደር ትርፉ አሳስበዋል፡፡

“የትግራይ ሕዝብ መጥፎ እና ጥሩውን ለይቶ ያዉቃል፤ ለዉጡንም ይፈልጋል፡፡ በክልሉ ኪራይ ሰብሳቢነትም ትልቅ አደጋ ነዉ፤ ለዉጥ ያመጣል፤ ሕወኃትም ወደ ለውጡ ይመጣል ብየ አስባለሁ፡፡ አሁን ካለዉ መንግሥት ጋርም ደጋፊ እንጂ ነቃፊ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ አሁን ያለዉ ሁኔታ ለኢትዮጵያ እና ለብሔር ብሔረሰቦች የሚመች በመሆኑ የትግራይ ሕዝብም ይደግፈዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አይደለም ኢትዮጵያን ምሥራቅ አፍሪካን ‘አንድ እናድርግ’ የሚልን መንግሥት መደገፍ ጥሩ ነዉ፡፡

 

Share.

About Author

Leave A Reply