የቲም ለማና የኦሮሞ ባለሀብቶች ግብግብ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አብይ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ወንበር እንደያዘ ጥቂት የኦሮሞ ባለሀብቶች መሰባሰብ ጀመሩ፤ተሰባስበዉ አብይንና ለማን አናግሩን ብለዉ መወትወትና በየእለቱ ቢሯቸዉን ማንኳኳትና አማላጅ መላክ ጀመሩ….አብይም ለማም የኦሮሞን ባለሀብቶች ለይተን የምናነጋግርበት ሁኔታ የለም ብለዉ መልስ ሰጡ….

እነዚሁ ጥቂት የኦሮሞ ባለሀብቶች የነ ለማን የአሜሪካን ጉዞ ተጠቅመዉ ሚኒሶታ ላይ አግኝተዋቸዉ ለማነጋገር እቅድ ነደፉ፤ከነ አብይ ቀድመዉ በመሄድ የአቀባበል ኮሚቴ አባል ሁሉ ሆኑ….በሚኒሶታም እነ ለማ በጭራሽ በጓሮ በር የሚያነጋግሩት ቡድን እንደማይኖር ሀሳብ አለኝ የሚል ሁሉ በተያዘዉ ፕሮግራም ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችል ገለፁ….

የዚህ የባለሀብቶች ቡድን የመጀመሪያዉ ፍላጎት ወደ ግል ይዘዋወራል የተባለዉን የአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ያለ ጨረታ በድርድር መግዛት ሲሆን ትልቁ ፍላጎቱ ደግሞ በነ አብይ ድጋፍ ተደርጎለት ኢኮኖሚዉን በዝርፊያና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ መቆጣጠር ነበር….ቲም ለማ አሻፈረኝ በማለቱ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያለዉ የባለሀብቶች ቡድን ቲም ለማን በጠላትነት ፈረጀዉ፤አንድ በሉ….

የቲም ለማን ቡድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩና በኦህዴድ የተለያዩ አደረጃጀት ዉስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ ያልነበራቸዉ አድፋጭ ሙህራኖች ቲም ለማ ቤቴን እያንኳኳ ስልጣን ያድለኛል ሚኒስትርነት ባጣ የቢሮ ሀላፊነት አላጣም ብሎ የተኮፈሰ ሀይል አለ….እነዚህ ሙህራኖች ከቲም ለማ የጠበቁት የስልጣን በረከት እንዳላገኙ ሲያረጋግጡ በቲም ለማ ላይ ጠላት ሆኑ፤ሁለት በሉ….

በማንኛዉም መንገድ ጥቅም ካገኙ ህዝባቸዉን ከመሸጥ የማይመለሱ በሙስናና በዝርፊያ የተጨማለቁ በቲም ለማ የተገፉና ከስልጣን የተነሱ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ካድሬዎች በቲም ለማ ላይ በጠላትነት ተነሱ፤ሶስት በሉ….

ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ኦህዴድ አስራናለች ገርፋናለች ከሀገር አሰድዳናለች ብለዉ በኦህዴድ ላይ በእጅጉ ያቄሙ ቲም ለማ ወርቅ ከሰማይ ቢያዘንብ እንኳ ጥላቻቸዉን ለማንሳት የማይፈልጉ ሀይሎች የቲም ለማ ጠላት ሆነዉ ብቅ አሉ፤አራት በሉ….

ለዉጡን ለመቀልበስ የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ያሉ ሀይሎች በጥቅም የገዟቸዉ ቡድኖች ቲም ለማ ጠላቴ ነዉ አለ፤አምስት በሉ….

ይህ አምስት ሀይል በተለያየ መነሻ የቲም ለማ ጠላት ይሁን እንጂ የጋራ ግብ የሌለዉ ከኦሮሞ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ የራሱን የግል ፍላጎት ብቻ ለማሳካት እላይ እታች የሚል ነዉ….ይህ የጥፋት ሀይል ኦነግን እንደ ከለላ እየተጠቀመ ኦህዴድን በማፈራረስ ላይ ተጠምዷል፤በመላዉ ኦሮሚያ ህግና ስርአት እንዳይኖር የአስተዳደር የፀጥታ ተቋማት እንዲፈርሱ ጠንክሮ እየሰራ ነዉ….

ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት እንኳን ከኦነግ ጋር የሚያስተሳስር የፖለቲካ ተሳትፎ ሊኖረዉ ቀርቶ ኡርጂና ሰይፈ ነብላባል ጋዜጦችን ለማንበብ እጁ ይንቀጠቀጥ የነበረዉ ሁሉ ዛሬ ኦነግ ነኝ ብሎ ለጥፋት ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ነዉ ….ቲም ለማ ራሱን ለመስወዕትነት አዘጋጅቶና ፊት ለፊት ተጋፍጦ ያመጣዉን ለዉጥ በዜሮ ለማባዛትና ኦሮሚያን ብሎም መላዉ ሀገሪቱን ወደ ለየለት ትርምስ ለመክተት ከፍ ካለም የኦሮሞ ህዝብን እርስ በእርሱ እንዲባላ እየተሰራ ነዉ፤ዛሬም አርቆ ማየት የተሳናዉና የፖለቲካ ሴራን በሴራ ለመምታት ዝግጁነትና ፍላጎት የሌለዉ የኦሮሞ ፖለቲካ በእጁ የገባዉን እድል ለማስነጠቅ በሚባል ደረጃ እየተንቀሳቀሰ ነዉ….

የቲም ለማ ሆደ ሰፊነትና አርቆ ማሰብ ሰፊ እድል የሰጠዉ ሀይል በቲም ለማ ላይ በከፈተዉ የዉስጥ ጦርነት በአንዳንድ የኦሮሚያ ዞኖች ከፍተኛ ዉጥረት ከመፍጠሩም በላይ የህዝቡ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ተገድቧል….በእርግጥ ቲም ለማ ወደ አስመራ አቅንቶ በየዋህነትና ከፖለቲካ ከፀጥታና ደህንነት ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ታዛቢም ሆነ ገዢ የስምምነት ሰነድ ሳይኖር የፈፀማቸዉ “ስምምነቶች” አሁን ለተፈጠሩት ችግሮች አስተዋፅኦ አልነበረዉም ማለት አይቻልም።

ሳᎀኤል ብዙነህ

Share.

About Author

Leave A Reply