የታፈነው የምርጫ 97 አገራዊ ቀውስ አጣሪ ኮምሽን ሪፖርት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በ1997 አገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ቀውሶችን እንዲያጣራ በፓርላማው የተሾመውና በኃላም ደርሶብኛል ባለው ጫና ሪፖርቱ ከመቅረቡ አስቀድሞ ከአገር የወጡት የአጣሪ ኮምሽኑ ሰብሳቢ አቶ ፍሬህይወት ሳሙኤል የሚከተለውን ፅፈዋል። አቶ ፍሬህይወት መንግስት በወቅቱ ተመጣጣኝ እርምጃ አለመውሰዱን የሚገልፀው ሪፖርት በአሁን ሰአት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በሚቀርብበት ሁኔታ ከአፈጉባኤው ጋር ያደረጉትን ውይይትና የደረሱበትን ስምምነት እንደሚከተለው አስፍረውታል።

ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ ጋር በነበረን ቅድመ ውይይትና ስምምነት መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ከኮሚሽኑ አባል ከነበረው አቶ ምትኩ ተሾመ ጋር በቅርቡ ሄደን በ1997 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ ማግስት መንግስት ዜጎቹ ላይ ስለ ወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ እንዲሁም በዚሁ ጉዳይ የገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽኑን እውነተኛ ዉሳኔ ይዘትና ቀጣይ እርምጃ ምን መሆን እንዳለበት ከተወካዮች ም/ቤት አፈ–ጉባኤ፤ ከም/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በዝርዝር ተነጋግረን የጋራ ውሳኔ ላይ ደርሰናል፡፡

የውሳኔውም ጥቅል ፍሬ ሀሳብ ‹‹ ” የተወካዮች ም/ቤት በወቅቱ በኮሚሽኑ ላይ የደረሰውን ጫና እውቅና እንደሚሰጥ፤ ጉዳዩ የዜጎች ህይወትና መብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ በመሆኑ በፊት የተወካዮች ም/ቤት ፋይል ውስጥ የገባውን የሀሰት ሪፖርት አውጥቶ አሁን በእውነተኛው ሪፖርት በመተካት ሰነድን በሰነድ በመተካት ደረጃ ታጥሮ ከሚቀር ይልቅ እስካሁንም ድረስ ጉዳዩ በአግባቡ እንዳልተቋጨ ተቆጥሮ በእጃችን የሚገኘውን እውነተኛውን ውሳኔ ለምክር ቤቱ እንድናስረክብ እና ም/ቤቱም በቋሚ ኮሚቴው በኩል አዲስ በተቋቋመው የእርቅና የሰላም ኮሚሽን እንዲታይ እንዲያርግ፤ እኛም አዲሱን ኮሚሽን በሂደቱ እንድናግዝ፤ ይህም በሀላፍነት ስሜት ጉዳዩ እንዲያልፍ በማደረግ ለሰላም፤ለእርቅ፤ለፍትህ መስፈን አስተዋጽኦ ከማድረግ አልፎ ለእውነት መቆምን ተገቢ ዋጋ ሰጥቶ ጉዳዩን ከመቋጨት በተጨማሪ እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ጥፋት ወደፊት እንዳይፈጸም ለማገዝም ነው፡፡ “›› የሚል ነው፡፡

በዚሁ አጋጣሚ በተወካዮች ም/ቤት የነበረን ሙሉ የአንድ ሰዓት ተኩል ውይይት ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ከአፈጉባኤው ጋር በተስማማነው መሰረት እንዲፈጸም በአጽንኦት እየጠየቅኩ፤ ከታች በኢ.ቲ.ቪ. ዜና ላይ ተቆርጦ የቀረበው የንግግሬ ሙሉ አረፍተ ነገር ቀጥሎ ያለው ነው፡፡‹‹ “ከታሪክ መማር የማይችሉት ያለፉበትን ስህተት የሚደግሙ እርጉማን ናቸው እንደሚባለው እንዳይሆንብን፤ እኛ ቢሆን ቢሆን ከሌሎች ስህተት ልንማር ለዚያ ካልታደልን ደግሞ ከራሳችን ስህተትና ውድቀት ልንማር ካልቻልን ስህተትን መድገማችን ስለማይቀር ይህ እንዳይሆን የበኩላችንን ለማገዝ ጭምር ነው የመጣነው፡፡ በአጭሩ በዚህ ምድር በውራጎዳናዎቻችን ዳግም ሞት፤ ዳግም ለቅሶ እንዳይሆን ከትላንቱ ለቅሶ፤ ከትላንቱ ሞት ተምረን ለልጆቻችን የዞረ ‹ድምር የሁከት አጀንዳ› እንዳናወርስ ለማለት ነው፡፡

‹‹ በአጭሩ እኔም ሆንኩ ባልደረቦቼ ማንንም የመበቀል ስሜትም ሆነ አላማም የለንም፡፡ መሰደድ እና መበቃቀል በኛ በቅቶ ትውልድ ቢድን ብርቱ ፍላጎታችን ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንዶች የስፈራራችሁን፤ ከገዛ አገራችን የነቀላችሁን (የምናውቃችሁም ሆነ የማናውቃችሁ ) እኛ የመጣነው እናንተ ለተራ እንድትነቀሉ እና እድትሰደዱ ሳይሆን በፍጹም በእውነትና በእውቀት በሆነ ይቅርታ ካለፍንበት መንገድ በመማር መንፈስ ጭምር ይቅር ተባብለን ልጆቻችን ከልጆቻችሁ ጋር አብረው አገር ሲገነቡና ሜዳ ላይ ስጫወቱ ለማየት ካለን ምኞት ነው የመጣነው” ›› የሚል ነበር ፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply