የአማራ ምሁራንና ብአዴን ከጣውንትነት ወደየት?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአማራ ምሁራንና ብአዴን ከጣውንትነት ወደየት?

ከሚያዝያ 12-14 በውቢቱ ባህር ዳር ከተማ የተካሄደው የአማራ ምሁራን የምክክር መድረክ ፣ በዓይነቱ ለየት ያለና በክልሉና ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ ከ300 በላይ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የታደሙበት ነበር:: በዚህ የክልሉ መንግስት በጠራው የሶስት ቀን ጉባኤ በዋነኝነት ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ብናልፍ አንዷለምና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን የተገኙበት ሲሆን ፣ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በሁለተኛው ቀን ከመጡ በኋላ የመድረኩን መሪነት ተረክበው እስከመደምደሚያው ዘልቀዋል::በተረፈ በፀረ- አማራነታቸው የሚመፃደቁት አሮጌ የህወሃት- ብአዴን አምበሎች አንዳቸውም ዝር አላሉም:: በትክክል የዘመኑ ንፋስ መለወጡን አሽትተው ይሆናል::

ይህ የምክክር መድረክ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጉብኝትና ከጣና የመሪዎች ፎረም ጋር መደራረቡ ፤ ጉልህ የጥድፊያ ምልክቶች የሚታይበት መሆኑ ፤ እንዲሁም በመድረኩ መርሃ ግብር በመነሻ ሃሳብነት ሊቀርቡ ከተዘረዘሩት ወረቀቶች ውጭ የውይይቱን አቅጣጫና መድረሻ ግብ የሚጠቁሙ ትልሞች አለመኖራቸው ሲታይ ፣ የክልሉ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምሁሩን ትርታ ከመሰለል ያለፈ ፍላጎት አለው ወይ ያሰኛል::

በተጨማሪም በኦሮምያና በትግራይ ከተጠሩት ተመሳሳይ መድረኮች በኋላ የተከተለ በመሆኑ የበላይ ትዕዛዝ ዓይነት ጥርጣሬ በታዳሚው ዘንድ አሳድሯል:: ነገር ግን የክልሉ ባለስልጣናት ለረዥም ጊዜ አቅደነው የከረመ ጉዳይ ነው ሲሉ አስተባብለዋል:: የኢህአዴግ ግርፍ የሆነው ብአዴን ከምሁሩ መደብ ጋር በቋጠረው ደመኝነት የተነሳ ፣ አገልጋይ ሲያሰኘው ብቻ እየመለመለ ያሰማራል እንጂ ከአማራ ምሁራን ጋር ከልብ ተመካክሮ አያውቅም:: እንዲያውም የአማራ ምሁራን የኢህአዴግ መንግሥት ዋነኛ ዒላማዎች ሲሆኑ ፣ በውሃ ቀጠነ ከየስራቸው ሲባረሩ ፣ በሃላፊነት እንዳያገለግሉ ሲገለሉ ፣ በእኩልነት ተወዳድረው የሚኖሩበት ፍትህ ሲነፈጋቸው ፣ በየስብሰባው ስምና ታርጋ እየተለጠፈላቸው ሲወገዙ ፣ በአጠቃላይ ከጨዋታ ውጭ እንዲሆኑና አንገታቸውን እንዲደፉ ሲዘመትባቸው ብአዴን በፊታውራሪነት ተሳትፏል:: ስለዚህም ከዚህ የህብረተሰብ ክፍል ጋር አይተማመንም ፤ ከናካቴው የሚግባባበት የጋራ ቋንቋ እንኳን የለውም:: በድንገት ወደ ጉባኤው የተጠራው ምሁር የመጀመሪያ ጥያቄ ‹‹ስለምንድነው የምንመካከረው?›› የሚል ቢሆን አያስገርምም:: ነገር ግን ተሰብሳቢው በአማራው ህዝብ እጣፈንታ ላይ ካደረበት ተቆርቋሪነት በመነሳት ፣ በአንድ መንፈስ የምክክሩን ሂደት አቅጣጫና ግብ ለማስተካከል ሞከራል::

ጥሪውን አክብሮ የመጣው አካዳሚያዊ ትንታኔዎችን ለማዳመጥ ሳይሆን ፣ በአማራ አንገብጋቢ ብሄራዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መወያየትና ለመፍትሄው ከክልሉ መንግሥት ጋር መሥራት ይችል እንደሆን ለመወሰን መሆኑን በአፅንኦት አስገንዝቧል:: በዚህም መሰረት በሶስቱ ቀናት ውይይቶችና ምክክሮች ያጠነጠነባቸው አበይት ርዕሶች የአማራውን ህዝብ የህልውና አደጋ ፤ የብአዴንን ያለፈና መፃኢ ሚና ፤ እንዲሁም የአማራ ብሄርተኝነትና የምሁሩን ሚና የሚመለከቱ ነበሩ:: በአጭር በአጭሩ ላቅርባቸው:: ሀ. አማራና ህልውናው ለአማራ ብሄር እንቅልፍ ላለመስጠት የተማማለው በትህነግ/ወያኔ የሚመራው ኢህአዴግ ፣ የአማራውን ህዝብ በሁሉ መንገድ ለማዳከም ለ27 ዓመታት በመሬቱ ፣ በሀብቱ ፣ በክብሩና ማንነቱ ላይ ግልፅና ስውር የጥቃት ዘመቻ ከፍቶበታል:: አማራው ከብሄራዊው ማህበረሰብ አባልነቱ ተዋርዷል ፤ ከጋራ ማዕዱ እንዳይቋደስ ተገፍቷል:: በገዛ አገሩ ተዘዋውሮ እንዳይኖር ፣ እንዳይሰራ ፣ እንዳይነግድ ፣ ሀብት እንዳያፈራ ተፈርዶበታል:: አማራው ክልልህ የተባለው ግዛት እንኳን ባለቤት አለመሆኑ ፣ ከሌሎች ክልሎች ህገ መንግሥቶች በተለየ በወረደለት ህገ መንግሥቱ በግልፅ ተደንግጎበታል:: አማራው በክልሉም ከክልሉም ውጭ ለከፍተኛ የህይወትና የንብረት ኪሳራ ፣ ለፅኑ የሥነልቡና ጥቃት ተጋልጧል:: ታሪኩ ተበርዟል ፣ ጠልሽቷል::

ለአገር የከፈለው ልፋቱ ፣ መስዋዕትነቱ ተክዷል:: ጥላቻና ቅጥፈት በፖሊሲ ተቀርፆ ፣ በሥርዓተ ትምህርት ታግዞ ተነዝቶበታል:: በዚህ ሁለገብ ወረራ አንገቱን ለመድፋት ፣ ማንነቱን ለመሸሽ ተገድዷል:: ‹‹አማራ ነኝ›› ከማለት ይልቅ ‹‹ከአማራ ክልል መጣሁ›› ፣ ‹‹አማርኛ ተናጋሪ ነኝ›› ይላል:: አልፎም ‹‹ኢትዮጵያዊ እንጂ አማራ የለም›› የሚል የሽሽት ስልት የሙጥኝ እስከማለት ተደርሷል:: በዚህ ሞልቶ በፈሰሰ ግፍና ጥቃት ምክንያት ፣ በምክክሩ ወቅት ከተነሱት ርዕሶች ጎልቶ የወጣው የአማራው ህዝብ በህልውናው ላይ ካንዣበበው አደጋ እንዴት ይውጣ የሚለው ጉዳይ ነበር:: በተለይም ደግሞ የወልቃይትና የራያ ህዝቦች ፣ የተከዜና የአባይ ምላሽ ግዛቶች ፣ እንዲሁም ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ውጭ የሚኖሩ ብዙ ሚሊዮን አማሮች እጣፈንታ የአማራ ብሄርተኝነት የደም ስር እንደሆነ ታይቷል:: በ‹‹አባይ ትግራይ›› የተስፋፊነት ቅዠት የሚናውዙ ጊዜ የሰጣቸው ልሂቃን ፣ ለአማራው አባቶቹ በደማቸው ያኖሩለትን አፅመ ርስቱን ነጥቀውታል ፣ አስነጥቀውታል::

በየዘመኑ ከሚነሱ ወራሪ ሃይሎች በህይወቱና በአካሉ ለመከተላቸው ውለታ ክፍያ በገዛ ባድማው ባይተዋርና ተሳዳጅ አድርገውታል:: የትግራይንም ህዝብ በሰሜን ከኤርትራ በደቡብ ከአማራ በግዛት ይገባኛል ስንጥቅ ውስጥ ከትተውታል:: ጉልበት የወሰደውን ጉልበት እስኪመልሰው ድረስ በነዚህ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የሰላም እንቅልፍ አይኖርም:: ትህነግ/ወያኔ እስከዛሬም የጠላትነት ማኒፌስቶውን አልቀደደም:: በአማራው ህዝብ ላይ በፈፀመው ግፍ አልተፀፀተም ፣ ይቅርታም አልጠየቀበትም:: እንዲያውም የጦር ድቤ እየጎሰመ ነው:: ለመሆኑ ከጓሮው ባድሜን ለማስመለስ አቅም ያጣ ቡድን ፣ የአማራን መሬት ነጥቄና አስነጥቄ በዋዛ ፈዛዛ እኖራለሁ ብሎ ማሰቡ የጤንነት ነውን ? ይህንን ትልቅ አስተዋይነት የጎደለውና ትውልዶችን ደም የሚያፋስስ ጉዳይ እንደ ተራ የህገ መንግሥት ጥያቄ ማየት ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ነው:: ይልቅስ ብቸኛው መፍትሄ ሰከን ብሎና ሃፍረትን ዋጥ አድርጎ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ መሬቱን ለባለቤቱ መመለስ ነው:: በትጋት የተሰራበት የአማራን ህልውና የማጥፋት ዘመቻ ፍሬው በገሃድ እየታየ ነው:: በአለማቀፍና አገራዊ ጥናቶች እንደተረጋገጠው የአማራ ክልል በትምህርት ፣ በጤና ፣ በመሰረተ ልማት ፣ በኢንዱስትሪ በየትኛውም ሰብዓዊ ልማት መለኪያ የአገሪቱ ጭራ ነው:: በህፃናት አቀንጭር ፣ በወላድ እናቶች ሞትና በመሳሰሉት ወሳኝ የህልውና መስፈርቶች ደግሞ ፊት መሪ ነው:: እጅግ የሚከነክነው ክልሉ ከአፈፃፀሙ በብቸኝነት የተሳካለት የቤተሰብ ምጣኔ ጉዳይ ነው::

ይህ ከመስመር ያፈነገጠ ‹‹ስኬት›› ሁለትና ሶስት ሚሊዮን ህዝብ እንደዘበት ጠፋ በሚባልበት ክልል ብዙ ጥያቄ ያስነሳል:: እንደሚታወቀው በቤተሰብ ምጣኔና በዘር ማጥፋት መካከል ያለው ቀጭን መስመር ፈቃደኝነት ይባላል:: በታህሣሥ 1941 የጸደቀው A/RES/260A(III) ደንብ ‹የዘር ማጥፋት ወንጀልን ስለመከላከልና መቅጣት ስምምነት› አንቀጽ 2 መሰረት፣ ዘር ማጥፋት የሚባለው አንድን ብሄረሰብ ፣ ዘውግ ፣ ዘር ወይም ኃይማኖታዊ ማህበረሰብ በጠቅላላው ወይም በከፊል ለማውደም በማሰብ የሚከተሉት አምስት ተግባራት ሲፈጸሙ ነው:: 1/ የቡድኑን አባላት መግደል፤ 2/ በቡድኑ አባላት ላይ ፅኑ አካላዊ ወይም አእምሮአዊ ጉዳት ማድረስ ፤ 3/ ሆን ተብሎ በማህበረሰቡ አኗኗር ላይ በሙሉ ወይም በከፊል አካላዊ ጥፋት ለማስከተል የተሰላ እርምጃ መውሰድ፤ 4/ በማህበረሰቡ ውስጥ ወሊድ እንዳይደረግ የታለመ እርምጃ መጫን ፤ 5/ የማህበረሰቡን ህጻናት በግድ ወደሌላ ማህበረሰብ ማዛወር ናቸው:: የአማራው ህዝብ ከነዚህ ውስጥ ምን ያልደረሰበት ነገር አለ ? ከያቅጣጫው እንደምንሰማው ክልሉ ይህንን ውጤት አስመዘገብኩ ብሎ የሚኩራራው እናቶችን ያለፈቃዳቸው በማምከን ፣ በገዛ ወገኖቹ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመ ነውን ? ገና ይህንን ክስ የሚያስተባብል ወገን አልታየም:: ለ. የብአዴንን የማያኮራ ሚና በተመለከተ ኢህዴን የተባለው የብአዴን አባት መጀመሪያ ኢህአፓን በኋላም አማራውን የሸጠ ከዳተኛ ጥርቃሞ ነው::

ገና ከማለዳው በአማራው ላይ ለተፈፀሙት አበይት ወንጀሎች አባሪ ተባባሪ ነበር:: እንደሚታወቀው በሃምሌ 1983 ዓ.ም የሰላምና ዲሞክራሲ ጉባኤም ሆነ በሽግግሩ መንግሥት ግልጽ ውክልና ያላገኘ ብሄረሰብ ቢኖር አማራው ነበር:: ጥቂት ቆይቶ አማራው ከየአካባቢው ሲዋከብና ሲገደል ፣ ተቆርቋሪ አጣ ሲባል ቆዳ መቀየር የተካነው ኢህዴን የአማራው አባት እኔ ነኝ ብሎ ብቅ አለ:: ይህ ቡድን የመከፋፈል ሴራውን የጀመረው በ1984 ዓ.ም በባህር ዳር ባደረገው ‹የጭቁን አማሮች› በተሰኘው አስቂኝ ጉባኤ ነበር:: ለጥቆም አማራውን መነጠል ፣ ማዋከብና ማምከን በእጅ አዙር ኢትዮጵያዊነትን የማጥፊያ ስልት አድርጎ መሰረተ:: አማራውን መስደብ በኢህዴን ዘንድ የሚያሾም የሚያሸልም ሆነ:: ይህ ማህበረሰብ የታሪክን ጉድፍ እንዲሸከም ፣ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማው ግልጽና ረቂቅ የስነልቡና ዘመቻዎች አወጀ:: የማንነት ቀውስ የሚንጣቸው የኢህዴን ወፈፌ ካድሬዎች አማራውን ግዳይ ጥለው ለመሸለም መሽቀዳደም ዋነኛው መለያቸው ሆነ:: ታዲያ ብአዴንስ የእባብ ልጅ አይደለምን? የአማራው ህዝብ ለሁለት አሥርት አመታት ፍዳውን የሚያስቆጥር ርብርቦሽ የተደረገበት በብአዴን ጋሻ ጃግሬነት ነበር:: ብአዴን እስከዛሬ ከክልሉ ውጭ ከቀያቸው በሚፈናቀሉ ፣ በውሃ ቀጠነ ከሥራቸው በሚባረሩ አማሮች ላይ ሲመቸው ይሙት በቃ እየፈረደ ፤ሳይመቸው ከደሙ እጁን እየታጠበ ቆይቷል::

ከክልሉ ውጭ ለሚኖር አማራም እቆማለሁ የሚል ደምፁን በለሆሳስ ያሰማው ከ20 ዓመታት በኋላ ዘንድሮ ገና የፊጥኝ ሲያዝ ነው:: በዚህ የከረፋ ማህደሩ የተነሳ ዛሬም ብአዴን ከችግሩ ወደ መፍትሄው አካልነት ለመሸጋገርና ቁርጠኛ የሰላም ሃይል ሊሆን ስለመቻሉ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው:: በውይይቱ የተነሳው ፅኑ ወቀሳም ብአዴን የአማራን ህዝብ ቁመና የማይወክልና የአማራ ወዝ የሌለው ጎፍላ ድርጅት ነው የሚል ነበር:: ታዳሚው የሰነዘራቸው ‹‹አማራን በአናቱ ላይ ቂጥ ብለው የሚዛበቱበትን መሪዎች አቅፋችሁ እስከመቼ ነው የምትዘልቁት?›› ‹‹የአማራ ብሄር ጠላቴ ናት ብሎ ከሚሰብክ ድርጅት ጋር ተጋብታችሁ የምትኖሩትስ በማን ስም ነው ?›› የመሳሰሉት ጥያቄዎች ከብአዴን አመራሮች አጥጋቢ ምላሽ አላገኙም:: እስከ ዶቃ ማሰሪያችን ብትነግሩን እንቀበላለን በሚል ታልፈዋል:: ነገር ግን በቅርብ ጊዜ በድርጅቱ መካከለኛና የበታች አመራር ውስጥ እየተጠናከረ የመጣው የአማራ ተቆርቋሪነት ፣ ድርጅቱ በብሄራዊው የፖለቲካ መድረክ ያንፀባረቀው የነፃነት አቋምና በአጠቃላይ በአገሪቱ የናኘው የለውጥ ንፋስ ተደራርበው ብአዴን አዎንታዊ ሃይል ሊሆን የሚችልበት ጭላንጭል የሚታያቸው አልጠፉም::

አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ብአዴን ራሱ ፅኑ የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል:: ስለዚህም በወቅታዊ አቋሙ ከጌቶቹም ከህዝቡም ያጣ መሃል ሰፋሪ ሆኖ መቀጠል አይችልም:: እንዴት እንሂድበት እንመካከር የሚለውም መድረክ ከዚህ የመውጫ ቀዳዳ ፍለጋ የመነጨ ይመስላል:: ብአዴን ከህዝብ የመጣበትን የበቀል ቁጣና ከአማራው ብሄራዊ ንቅናቄ ያንዣበበትን ማዕበል ለመቋቋም ፤ አጋሩ ኦህዴድ እንዳደረገው የህዝብን አመኔታ ለማግኘትና አነቃንቆ ከጎኑ ለማሰለፍ እንደገና መወለድ ይኖርበታል:: ይህ ከተፈለገ ርዕዮታዊ ፣ ስልታዊና መዋቅራዊ አብዮት ማካሄድ የግድ ነው:: በመጀመሪያ ራሱን ከባርነት ነፃ አውጥቶና መቅለስለሱን ትቶ በግልፅ የአማራ ወገንተኝነት ማሳየት አለበት:: የጌቶቹን ፊት እያየ ሳይሆን የአማራውን ጥቅም እያሰበ ፣ ከህዝብ የሚያቀራርብ ስራ በመሥራት ለሃጢአቱ ንሠሃ መግባት ይኖርበታል:: ሁለተኛ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፣ ልማታዊ መንግሥት ፣ ብሄር ብሄረሰቦች ምንትሴ የሚባሉትን ውዥንብሮች ወዲያ ጥሎ ፣ የአማራን ብሄርተኝነት በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ለማራመድ መዘጋጀት ወሳኝ ነው:: በአማራው ውርደት የከበሩ ቅጥረኞችንና ፊርማቶሪዎችን ከመዋቅሩ ጠራርጎ በማስወገድ ፣ በአዳዲስና ለህዝባቸው ቀናኢ በሆኑ ወጣት አመራሮች መተካትም ያስፈልገዋል::

ለዚህም መላውን የአማራን ህዝብ በተለይም የወጣቱን ሃይልና የምሁሩን ክፍል የማያወላውል ድጋፍ ማግኘት የግድ ነው:: እንዳያማህ ጥራው አይነት ሳይሆን ፣ በክልሉ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ሃይሎች ጋር በጋራ ለመስራት በቅንነት በሩን ክፍት ማድረግ አለበት:: ስልጣንን ለህዝብ ለመመለስ እርምጃ መጀመር አለበት:: ነገር ግን በተለመደው አፋኝነት ፣ ብልጣብልጥነትና አግላይነት እቀጥላለሁ ፤ የክልሉን ውስብስብ ችግሮች በትህነግ/ወያኔ መፍትሄዎች እመልሳለሁ ካለ መጀመሪያ የአሾክሻኪነቱን በትር መቅመሱ አይቀርም:: ሐ. የአማራ ብሄርተኝነትና የምሁራን ሚና ትእግስቱና ሆደ ሰፊነቱ ለመገፋት የዳረገው የአማራ ህዝብ ብሄርተኝነት መንፈስ እንደ ቋያ እሳት እየተንቀለቀለ መሆኑ ዓይን ላለው ሁሉ በግልፅ ይታያል:: ይህ ስሜት በጉባኤውም ላይ በጉልህ ተንፀባርቋል:: በሌላ በኩል አማራና ብሄርተኝነት የሚሉት ቃላት አብረው መታየታቸው ፣ ገና ከወዲሁ ከየአቅጣጫው ጩኸት አስነቷል:: አንዳንድ ሟርተኞችና ፀረ- አማራ ጉጅሌዎች ‹‹የአማራ ምሁራን የጦርነት ነገሪት እየጎሰሙ ነው›› ብለው ማራገብ የጀመሩት ገና ጉባኤው ሳይጋመስ ነበር:: እነዚህ በጎሰኝነት የሰከሩ ቡድኖች በአማራው ላይ ይህ ሁሉ ግፍ ሲወርድበት ትንፍሽ ያላሉ ናቸው:: ዛሬ እንዲህ ምን አንዳንገበገባቸው እናውቃለን:: ሌሎች ደግሞ የበግ ለምድ ለብሰው ‹‹ኢትዮጵያ አለቀላት›› ፣ ‹‹ወያኔ በፈለገው መስመር ገባንለት›› የሚል ሙሾ ያወርዳሉ:: ለነዚህም ሰዎች 27 ዓመት ሙሉ ከማለቃቀስ የተሻለ መፍትሄ አላመጣችሁም እንላቸዋለን::

ነገር ግን በቅን ልቡና ፅንፈኛ ብሄርተኝነት አገራችንን ይዞአት የገባበትን መቀመቅ በማየት የአማራ ብሄርተኛ መነሳሳት ያሰጋቸው አሉ:: ከነዚህ አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ ናቸው:: ዶ/ር አብይ ከጎንደርና ባህር ዳር ህዝብ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች የክልሉን በቁጭትና ቁጣ የነደደ ስሜት በትክክል ተገንዝበዋል:: ስለዚህም ለምሁራኑ ባደረጉት አጭር ንግግር ኦህዴዶች ‹‹ለከት በሌለው ብሄርተኝነት ትልቁን የኦሮሞን ህዝብ አውርደን መንደር ውስጥ መክተታችን ስህተት ነበር:: እናንተም በስሜት የአማራን ትልቅ ህዝብ በዚያ መንገድ እንዳትነዱት:: ለብሄርተኝነታችሁ ገደብ ማበጀት እንዳትዘነጉ ፣ በጥናትና ምርምር ደግፉት›› ሲሉ አደራ ብለዋል:: በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ በሁለተኛው ቀን ከቀትር በኋላ በድንገት በአዳራሹ ውስጥ ሲገኙ ታዳሚው በግርምትና በጭብጨባ ነበር የተቀበላቸው:: በግል እንደታዘብኩት እኝህ ሰው ከህዝብ መደባለቅ የማይቸግራቸው ፣ ማራኪ ስብዕና ያላቸውና የአድማጫቸውን ቀልብ በቀላሉ መግዛት የሚችሉ ናቸው:: ያለአንዳች የአግቱልኝና ጋርዱልኝ ጋጋታ ወደ መድረኩ በመውጣት ስጋታቸውን ሲገልፁ ፣ ‹‹በአገሪቱ ተዘዋውሬ ያየሁትና የሰማሁት ችግርና ምሬት ደረጃ አስደንግጦኛል:: ከፊታችን የተደቀነውን ታላቅ ብሄራዊ አደጋ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን ካልሆነ በጭራሸ አንፈታውም›› ብለዋል:: በአገራችን መጨረሻው ያልለየለት ቀውስ መስፈኑ እውነት ነው::

በአንድ በኩል ማህበረሰቦች ከጨቋኝ ፣ ዘረኛ ፣ ሌባና አረመኔ መንግሥታቸው ጋር ተፋጥጠዋል:: ቁጭት ፣ ጥቃትና ቁጣ የቀሰቀሰው ህዝባዊ ማዕበል አስፈሪነቱ ታይቷል:: በሌላ በኩል ስርዓቱ የፈለፈላቸው የጎሳ ነጋዴዎች ፣ የራሳቸውን ሥልጣንና ጥቅሙን ለማዳን ማህበረሰቦች በጥርጣሬና በጥላቻ ለደም መፋሰስ እንዲሰለፉ ደፋ ቀና ይላሉ:: እምቢተኝነት ፣ አድማ ፣ ግርግር ፣ አመፅ ፣ ግጭት ፣ መፈናቀል ፣ የንብረት ውድመት ፣ የህይወት መጥፋት የዕለት ተዕለት ክስተቶች ከሆኑ ከራርመዋል:: ገና አሁንም ማህበራዊ ሰላም ፣ ብሄራዊ ሰላም የለም:: መ. የአማራ ብሄርተኝነት ስጋት የማይሆነው ለምንድነው? እነዚህ ከየፉካቸው ለሚንጫጩ ወገኖች ፣ ‹‹አይዟችሁ አትስጉ›› ማለት ብቻ በቂ አይደለም:: የአማራ ብሄርተኝነት ለሌሎች ኢትዮጵያዊን ወንድሞቹ ስጋት የማይሆንባቸው ነባራዊና ታሪካዊ ምክንያቶች አሉ:: በእኔ አመለካከት አንደኛው ምክንያት የአማራ ብሄርተኝነት ሞልቶ ከፈሰሰ በደልና ከተጨባጭ የህልውና አደጋ መነሳቱ ነው:: በጥላቻ የሚነዳ ጎሰኝነት ሳይሆን በአማራ ህዝብ ላይ የተንሰራፋበት ጭቆና ፣ ኢፍትሃዊነት ፣ ማናለብኝነት ፣ ዝርፊያና ዘረኝነት ውጤት ነው:: እውነተኛ የነፃነት ፣ እኩልነት ፣ ፍትህ ፣ ወንድማማችነት ፣ ተስፋ ፣ ክብርና ማንነት ጥያቄ ነው:: ስለዚህም ከሥርዓቱ አቀንቃኞችና ጋሻ ጃግሬዎች ውጭ ለማንም የአማራ ብሄርተኝነት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ስጋት የማይሆንበት ተጨማሪ ምክንያት የብሄረሰቡ ትክለ ስብዕና ነው:: አማራ የጥበብ መሃንዲስ ፣ ታሪክ ሰሪ ፣ ድንበር አስከባሪ ፣ አስተዋይ መሪ ነው:: ለአከርካሪው ሲቃጡት አናት የሚያፈርስ የጀግኖች አውራ ነው:: እንደ ኢትዮጵያ ቤተሰብነቱ አማራ የእግዜር የበኩር ልጅ ነው:: በሃይማኖቱ ፣ በቁርጠኝነቱ ፣ በደግነቱና በትዕግስቱ ያሰበበት ደራሽ ነው ስጋት አይሆንም::

ብሄርተኝነት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ልያዘው ወይስ ልተወው እያሉ በአመክንዮ የሚወስኑት ምርጫ አይደለም:: በ‹‹ዘር›› የሚተላለፍም ደመነፍሳዊ ባህሪ አይደለም:: ማህበረሰቦች ካለፈ ታሪካቸውና ተመክሮአቸው ተነስተው ወደፊት የተደቀነባቸውን የህልውና ስጋት ለመቅረፍ የሚከተሉት የትግል ስልት ነው:: መንግሥት ለማህበረሰቦች ዘላቂ ዋስትና መስጠት ካቃተው ፣ ተጠቂዎች ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ብሄርተኛ መንገዶችን ይከተላሉ:: የአማራም ብሄርተኝነት በዚሁ ዓይነት ሂደት የተፈጠረ በመሆኑ ፣ ሊያስገርመን የሚገባው እስከዛሬ ተዳፍኖ መክረሙ ነው:: የአማራ ብሄርተኝነት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ስጋት የማይሆንበት ተጨማሪ ምክንያት የብሄረሰቡ ትክለ ስብዕና ነው:: አማራ የጥበብ መሃንዲስ ፣ ታሪክ ሰሪ ፣ ድንበር አስከባሪ ፣ አስተዋይ መሪ ነው:: ለአከርካሪው ሲቃጡት አናት የሚያፈርስ የጀግኖች አውራ ነው:: እንደ ኢትዮጵያ ቤተሰብነቱ አማራ የእግዜር የበኩር ልጅ ነው:: በሃይማኖቱ ፣ በቁርጠኝነቱ ፣ በደግነቱና በትዕግስቱ ያሰበበት ደራሽ ነው:: አማራው በታሪኩ ዘውግ ተኮር ጥቃት ሲደርስበት የመጀመሪያው አይደለም:: ቢያንስ የቅርቡን የፋሽስት ጣልያንን ዘመነ አፀባ ማስታወስ ይቻላል::

ነገር ግን ይህ ሆደ ሰፊና አስተዋይ ህዝብ አገሩን ከራሱ በማስቀደም ለባንዶችም ፣ ለፊርማቶሪዎችም ፣ ለአስካሪዎችም ፣ ለልጆቻቸው ለገንጣይ አስገንጣዮችም የሰላም እጁን ዘርግቶ ከማቀፍ ውጭ የበቀል በትር ሰንዝሮ አያውቅም:: አማራ በኩሩና ታላቅ ስብዕናው የተነሳ ብሄርተኝነቱ ከበታችነት መርዝ የፀዳ ነው:: ስለዚህ ለማንም ወገን ስጋት አይደቅንም:: ታዲያ ምን ይደረግ ? የአማራው ብሄርተኝነት ንቅናቄ ገዥ መንፈስ ብሄራዊ እኩልነትና ፍትህ ነው:: አማራው አንገቱን ቀና አድርጎ በእኩልነት የሚኖርባት አገር በመጠየቁ ሊያፍርበት አይገባም:: እስካሁንም ከትዕግስትና ከፀሎት ባለፈ ፣ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝለት አቤት ሲል ኖራል:: ፕሮፌሰር አስራትና አጋሮቻቸው በዚያች ቀውጢ ቀን የመላው አማራን ድርጅት በመመስረት ድምፃቸውን ለማሰማት ሞክረዋል:: በርካቶችም የንብረት ፣ የአካልና የህይወት መስዋዕትነት ከፍለውበታል:: እነዚህን ፋና ወጊዎች ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል:: ዛሬም የአማራ ህዝብ የተጋረጡበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት የሚችለው በሰላማዊ ትግል በየደረጃው ነው:: በውይይቱ እንደተሰመረበት የአማራው ብሄርተኝነት እርምጃ የሚጀምረው በኢትዮጵያዊነቱና በአማራነቱ መካከል የተፈጠረበትን ብዥታ በማጥራት ነው:: ታሪክ እንደሚነግረን ከራሱ ከአማራው ገዥ መደቦች ጭምር ፣ በየጊዜው የሚነሱ ባዕዳንና አገር በቀል ጠላቶቹ የአማራውን የብሄር ንቃተ ህሊና ክፉኛ ይፈሩታል:: ስለዚህም በኢትዮጵያዊነቱና በአውራጃዊነቱ መካከል ያለውን ብሄረሰባዊ ማንነቱን ለማደብዘዝ ይተጋሉ::

የዘመናችንም አንዳንድ የዋህ ሊቃውንት እንደሚመኙት ፣ አማራው ብሄርተኝነት የህልውና አልፋና ኦሜጋ በሆነበት ሥርዓት ውስጥ ማንነቱን ችላ ብሎ ወይም ነገሮች በተዓምር እስኪቀየሩ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ አይችልም::

(ይህ ጽሁፍ የተወሰደው በዚህ ሳምንት ከታተመው ግዮን መጽሄት ነው)

Share.

About Author

Leave A Reply