‹‹የአማራ ክልል ሕዝብ እንደሀገር እያሰበ እንደ ክልል መሞት የለበትም፤ በአማራ ክልል ሕዝቦች ላይ ያነጣጠረ ሴራ ካለ የክልሉ መንግሥት በአስቸኳይ የራሱን ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡›› የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

(አብመድ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 5 ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 13 ኛ መደበኛ ጉባኤ ከሰዓት በኋላም ቀጥሎ ውሏል፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች እና በአማራ ክልል የሕዝብ ደኅንነትና ሠላም ግንባታ ቢሮ የዕቅድ አፈጻጸም ላይ የምክር ቤት አባላቱ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡

የሕግ ሥርዓቱ ያለመከበሩ በክልሉ የሚኖሩ ሕዝቦች አንድነት እንዲላላ በር እየከፈተ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የልማት ሥራዎች እንዲጓተቱ እና ጥያቄዎች ወደግጭት እንዲሂዱ ዕድል የፈጠሩ እንደሆነም አባላቱ አስታውሰዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ሕግ በማስከበር ረገድ ‹‹ከመንግሥት ጎን እንሆናለን›› እያለ መንግሥት ቸልተኛ በመሆኑ ነው የፀጥታ መደፍረሱ እንዲባባስ ያደረገው ሲሉም አባላቱ አስተያዬቶን ሰጥተዋል፡፡

‹‹የአማራ ክልል ሕዝብ እንደሀገር እያሰበ እንደ ክልል መሞት የለበትም›› ያሉት የምክር ቤት አባላቱ አማራ በተለያዩ ክልሎች እየተገፋ በመሆኑ ይህ እንዲሆን እያደረገ ያለ ሴራ ካለ የክልሉ መንግሥት በጥንቃቄ አይቶ መፍትሔ መስጠት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ የምክር ቤት ውሳኔዎች በተሿሚዎች ተፈፃሚ ባለመሆናቸው ችግሮች እየተፈጠሩ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ መንግሥት ለሕብረተሰቡ የሠላም ፀር የሆነውን ሴራ ከመበጠስ ይልቅ በየወቅቱ ‹‹እየሠራን ነው›› የሚባለው አሠራር ደረጃ በመጥፋቱ የዜጎች ሞት እንዲቀጥል፣ የመብት ጥሰቶች እንዲበራከቱ እንዳደረገ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹የክልሉ መንግሥት ለዚህ ቀውስ የበቃው በመርህ እና በሕግ ከመመራት ይልቅ በማኅበራዊ ድረ ገፆች ውሳኔ እየተዳደረ በመሆኑ ነው፤ አዴፓም ፈተና ውስጥ ነው›› ያሉት የምክር ቤት አባላቱ የሰኔ 15ን ግድያ የማጣራት ተግባር የክልሉ መንግሥት በአግባቡ መምራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
‹‹ከሰኔ 15 ግድያ ጋር በተያያዘ መፈንቅለ መንግሥት የሚመስል ነገር የለውም›› ያሉት አባላቱ ‹‹ከዚያ ይልቅ ሰዎች ተለይተው መገደላቸው ታይቷል›› ብለዋል፡፡ ‹‹የሰኔ 15 ግድያን ማድበስበስ አያዋጣም፤ ብንተወውም አይተወንም›› ሴራውን የፈፀመውን ለማውገዝ እና ከድርጊቱ ለመማር በግልፅ መናገር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹በሽታውን ያልተናገረ መድኃኒት አይገኝለትም›› እንዲሉ የሰኔ 15ን ሴራ ለይቶ አውቆ መታገል እንደሚያስፈልግ አባላቱ አሳስበዋል፡፡ አመራሮቹ የድርጊቱን አፈፃጸም መግለፅ እንደቻሉት ሁሉ የችግሩን ሴራ ለይቶ ለሕዝቡ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply