የአማራ ፖለቲካ ለቅሶ ይበዛዋል!

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ወደ ራሳችን፣ ወደ ውስጣችን ማየት አለብን ብዬ ከደመደምኩኝ ሰነባብቻለሁ። ሁሉንም ችግሮቻችን ጠላት አመጣሽ አድርጎ ማዬት ትክክል አይደለም። ውሻ በቀደደው ጅብ መግባቱ የአባት ነው። መጀመሪያ ነገር በርህን ዘግተህ ውጣ። እንደነገሩ አለመዝጋትህን እርግጠኛ ሁን! በርህን ጠርቅመህ ከዘጋህ ውሻ ሊገባ አይችልም። በርህን እንደነገሩ በዛኒጋባ አውሸልሽለህ ጠላት ገባ ብለህ ማለቃቀሱ ግን የአንተን ተገማችነት ያሳብቅ ካልሆነ በቀር ምንም ፋይዳ የለውም።

የአማራን ህዝብ “ጠላት ነው መጥፋት አለበት” ብሎ የሚሰራ እንዳለ ሁሉ የአማራን ህዝብ እንደ ነፍሱ የሚወድ መኖሩንም መዘንጋት አያሻም። አማራ የዳበረ እና የጠነከረ ባህል ባለቤት መሆኑን አትዘንጋ። የአማርኛ ቋንቋ በሁሉም ህዝብ ዘንድ መነገር እንዴት ሀብት እንደሚሆን አሰላስል። በኢትዮጵያ በሙሉ ተሰራጭቶ መኖሩንም እንደ መጥፎ እድል አትቁጠር። ይልቁንስ ይህን የህዝብ ስርጭት እንዴት አድርጌ ወደ ጸጋ ልቀይረው ብለህ አስብ። የአማራ ህዝብ በዓለም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ ጠላቱ እንደሆነ አድርጎ ማሳበቅና እንደ ቃዬል ተቅበዝባዥ አስመስሎ መሳልም ትክክል አይደለም። ሲሆን ሲሆን ለሌላ እንዲተርፍ አድርጎ መስራት፣ ሳይሆን ደግሞ ለራሱ የሚበቃ ማድረግ የእኛ የልጆቹ ግዴታ ነው። ለዚህ አንድ ጠጠር ወርውር! ይኸ ሳይሆን ቀርቶ ግን 24/7 ስለመጥፋትህ ብታላዝን ጠብ የሚልልህ ነገር አይኖርም።

ዓለም የምትመራው በግራቪቲ ህግ ነው። በግራቪቲ ህግ ደግሞ ወደ አንተ አብዝተህ የሳብከው ሁሉ ከአንተ ጋር ይዛመዳል ማለት ነው። law of atraction ማለቴ ነው። ቀኑን በሙሉ ደካማ እንደሆንክ እና ልትጠፋ አንድ ሀሙስ የቀረህ መሆኑን ስትሠብክ እየዋልክ አሸናፊነትን መጠበቅ ከብት ባላሰማራህበት ሜዳ ኩበት ለመልቀም ቅርጫትህን ይዘህ እንደመውጣት ያለ ሞኝነት መሆኑን ማወቅ አለብህ። ለራስህ ጠንካራ እንደሆንክ ንገር! ጠንካራ ትሆናለህ። ይኸን ስልህ ግን አጉል የሌለህን እንዳለህ አድርገህ ታበይ እያልኩኝ አይደለም። በልክህ ልክ ኑር ለማለት ነው።

እውነት ለመናገር የአማራ ፖለቲካ ለቅሶ ይበዛዋል። ይኸ ትክክል አይደለም! አንድም እኛን ደካማ አድርጎ መሳሉ በህዝባችን ላይ የሚያስከትለው የሞራል መቀጨጭ እንዳለ ሆኖ ለሌላውም ያልሆነውን እብጠት ያላብሳል። ይኸ ደግሞ ከባድ ኪሳራ ነው! በተለይ በዚህ ሁሉም በነቃበት ዘመን ሲሆን ኪሳራው እጥር ድርብ ነው! ብልጠት ያሻል!

(ጋሻው ማስረሻ)

Share.

About Author

Leave A Reply