Thursday, January 17

የአቢሲኒያ ባንክ የዘረፋ ትራጄዲ።

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ከቀኑ 12:00 አካባቢ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ሻይ ቡና ለማለት ቦሌ መድሀኒያለም ጀርባ በሚገኘው አቢሲኒያ ኮፊ ፊት ለፊት የያዝነውን መኪና ፓርክ በማድረግ ቁጭ ብለን የባጥ የቆጡን የወዳጅ ወጉን እናወጋለን ባጋጣሚ እኔ የተቀመጥኩት ወደ መንገዱ አቅጣጫ በመሆኑ በፎቶው ላይ የምትመለከቷት ቪትዝ እኛ ቀደም ብለን ካቆምናት የጓደኛየ መኪና ጋር በሀይል ትላተማለች እኔም በሁኔታው በመደናገጥ በፍጥነት ተንደርድሬ በመውረድ ላይ እያለሁ ግጭቱን ያደረሰችው መኪና አሽከርካሪ ለማምለጥ ወደፊት መንዳት ይጀምራል ከማንም በፊት አደጋ ያደረሰችውን መኪና ለማስቆም እየሮጥኩ ከፊት ለፊቴ የማየውን የፓርኪንግ ሰራተኛ አስቁመው እያልኩ ጮኩ በሚገርም ሁኔታ የፓርኪንጉ ሰራተኛ በሀይል በመጮህ እንዲያቆም በያዘው ዣንጥላ እያስጠነቀቀው መሀል አስፓልት ላይ በመቆም መንገዱን ዘጋበት።

ወዲያውኑ በግጭቱ ምክንያት ባላንሧን መጠበቅ የተሳናት መኪና በግምት ሀምሳ ሜትር ያህል እንደተጓዘች ለመቆም ተገደደች ሾፌሩም በፍጥነት ተስፈንጥሮ በመውረድ ወደፊት መሮጥ ይጀምራል ጋቤና ከሾፌሩ ጋር የነበረው ሌላኛው ተሳፋሪም ሾፌሩ ወደ ሄደበት አቅጣጫ ተከትሎ ይሮጣል በወቅቱ በሾፌሩ እና በእኔ መካከል የነበረው ክፍተት በግምት አምስት ሜትር ያህል ብቻ ነበር።

በሾፌሩና በተሳፋሪው እሩጫ ግራ ስለተጋባሁና የሮጡበትና እንደዚህ የበረገጉበት ምክንያት ስላልገባኝ በመደናገጥ እንደ መቆም ስል ባካባቢው የነበረው ህዝብ ያዘው ያዘው እያለ ሾፌሩን ተከትሎ መሮጡን ተያያዘው ወዲያውኑ ከመኪናዋ የሗላ በር ጥቁር ሌዘር የለበሰ በግምት አርባወቹ እድሜ ላይ የሚገጅ ጠብደል የመኪናዋን በር ከፍቶ ሊወጣ ሲል ከኔ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጥን በእጁ ጩቤ ይዟል እኔን በጩቤው እያስፈራራ መንገድ ካስለቀቀኝ በሗላ ሾፌሮቹ ከሮጡበት አቅጣጫ በተቃራኒ በእጁ የያዘውን ጩቤ እያወናጨፈና ሰው ለመውጋት እያስፈራራ እግሬ አውጭኝ አለ በሚገርም ሁኔታ ባካባቢው የነበረው ህዝብ በያዘው ጩቤ ሳይደናገጥ ወደ ሌባው በመሮጥ ሰውየውን ጠልፎ በመጣል እንዲወድቅ ካደረገ በሗላ መደብደብ ጀመረ።

ያሁሉ ሲሆን እኔን ጨምሮ በአካባቢው የነበረው ህዝብ መኪና ገጭተው ለማምለጥ ሙከራ ያደረጉ ተራ ግለሰቦች እንጂ ባንክ ዘርፈው የመጡ ወንበዴዎች መሆናቸውን አላወቅንም ነበር።

ወዲያውኑ ግጭት ወዳደረሰችው መኪና ተመልሼ ስሄድ አንድ ቀጭን ትራፊክ ፖሊስ እና የፓርኪንግ ሰራተኛው እንዲሁም ከአምስት የማይበልጡ ሰወች መኪናዋን ከበው ቆመዋል ጋቤና ውስጥ በትልቅ ቀይ ማዳበሪያ የታሰረ በእኔ ህሊና የበቆሎ እሸት የሚመስል ነገር ተመለከትን እኔም በማዳበሪያ የታሰረውን ነገር ምንነት ለማወቅ በእግሬ እየመታሁ ትራፊኩን የጫኑት ነገር ምንድነው ስለው እሱም እንደኔ ምንነቱን አላወቀም ነበርና ምን እንደሆነ ማወቅ እንዳልቻለ ነገረኝ።

ይሄ ሁሉ ሲሆን በግምት ወደ ሰላሳ ደቂቃወች አልፈዋል ከዛ በሗላ የሆነ ልጅ እየሮጠ ግጭት ወዳደረሰችው መኪና መጣና በማዳበሪያ ውስጥ ያለው ብር መሆኑን እና ሰዎቹ ኤድና ሞል አካባቢ ከሚገኘው አቢሲኒያ ባንክ ሰራተኞቹን በማገት ገንዘብ ዘርፈው እንደመጡ ነገረን።

በጣም የሚገርመው ብሩን የያዘችው መኪና ለሌላ ሌቦች አለመዳረጓ ነበር።

ሾፌሩን ጨምሮ መጀመሪያ ላይ መኪናዋ ውስጥ ከነበሩት ወንጀለኞች በሩጫ ከኛ ያመለጡት ሁለቱ ሌቦች ፊት ለፊታቸው እንዲቆሙ ከጠየቋቸውን የፌደራል ፖሊሶች አንደኛውን እጁ ላይ ጉዳት በማድረስ ለመሰወር እንደሞከሩና አንደኛው እንደተያዘ ሰማን።

እኛም የያዝነውን ሌላኛውን ሌባ ለፌደራል ፖሊሶች ካስረከብን በሗላ ብር የጫነችውንና ጉዳት የደረሰባትን የጓደኛየን መኪና ስንጠብቅ እስከ ምሽት ሁለት ሰአት ተኩል ድረስ ቆየን ሌላ ተጨማሪ ሀይል መጥቶም ገንዘቡን ለመቁጠርና ኤግዚቪት ለማድረግ በፖሊስ መኪኖች ጭነው ወስደውታል።

የብሩ መጠን ስንት እንደሆነ ግን በወቅቱ ለማወቅ አልቻልኩም ነበር ከሌቦቹ መካከልም የባንኩ ዘበኛ እንደሚገኝበትም ለማወቅ ችያለሁ በዚህ አጋጣሚ በአካባቢው የነበረውን ህዝብ እርብርብ ሳላደንቅ ማለፍ አልችልም።

ምነው በየቢሮው ያሉ የዚህን ምስኪን ህዝብ የሚዘርፉ ህሊና ቢስ ሌቦችን እንዲህ እያሯሯጥን በመያዝ መንግስትን ማገዝ በቻልን ስል ተመኘሁ::

(አንተነህ ረዳኢ)

Share.

About Author

Leave A Reply