የአቶ ምግባሩ ከበደ የሕይወት ታሪክ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አቶ ምግባሩ ከበደ ከአባታቸው አቶ ከበደ አውነቱ ከእናታቸው ወይዘሮ የሺ ውበቱ ሐምሌ 23 ቀን 1966 ዓ.ም በቀድሞው ጎንደር ክፍለሃገር በደብረ ታቦር አውራጃ በአሁኑ የደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን ወረሃ ወረዳ ልዩ ስሙ ወፍ አርግፍ ታምሬ ልደታ ቀበሌ ነው የተወለዱት፡፡

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወፍ አርግፍ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአምበሳሜህ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በባህር ዳር ጣና ሃይቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡

በጣም ፈጣንና ጎበዝ ተማሪ በመሆናቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጣም ባጠረ ጊዜ ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲሁ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በህግ ተመርቀዋል፡፡ በህግ ትምህርት ብቃት ያላቸውና ብልህ ህግ አዋቂ ለመሆን በቅተዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በተማሩበት የህግ ሞያ በምዕራብ ጎጃም ዞን የደጋ ዳሞትና ሰካላ ወረዳዎች በአቃቢ ህግነት ህዝባቸውን በብቃት፣ በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡

በወረዳ ደረጃም በአቃቢ ህግነታቸው ባሳዩት ብቃትና ሞያዊ ችሎታ የሞያ እድገት አግኝተው የምስራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ የዞን አቃቢ ህግ በመሆን በተመሳሳይ መልኩ ሞያዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡ ህዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነትም አገልግለዋል፡፡

በፖለቲካ ብቃታቸውም አንቱ ለመባል የበቁት አቶ ምግባሩ፣ የወቅቱ የክልሉ መሪ ፓርቲ የቀድሞው ብአዴን የምስራቅ ጎጃም ዞን አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሆነው እንዲሰሩ መድቧቸው ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ በዚህም የዞኑ ህዝብ ለጥቅሙና ለመብቱ መረጋገጥ ተደራጅቶ እንዲታገልና የአካባቢው ሰላም እንዲጠበቅ፣ ልማት እንዲፋጠን ከትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ብቃት ያለው አመራር ሰጥተዋል፡፡

የፖለቲካ ብቃታቸውን በየጊዜው እያሳደጉ እና የህዝብ እምነት እያተረፉ የመጡት አቶ ምግባሩ፣ ከ1999 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ የምስራቅ ጎጃም ዞን የአቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ፣ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንዲሁም ከ2003 እስከ 2008 ዓ.ም የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ህዝባቸውን በታማኝንት፣በቅንነትና በህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ማገልገል የቻሉ ጓድ ነበሩ፡፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን ለዓመታት አመራር በሰጡበት ወቅት የዞኑን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሌት ተቀን አመራር የሰጡ ሲሆን፣ በተለይም የዞኑን ልማት ለማፋጠን ባላቸው ቁርጠኝነት የምንቆረር ኮንስትራክሽን ድርጅት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላ ድጋፍ አግኝቶ የዞኑን የመሰረተ ልማት ማፋጠን እንዲችል ግንባር ቀደም አመራር በመስጠት ብቃታቸውን ያረጋገጡ ጓድ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የጎጃም ህዝብ ቱባ ባህልና ጥበብ እንዲለማ ለትውልድም እንዲሸጋገር ከልብ በማሰብ የባህልና የኪነት ቡድኖች እንዲቋቋሙ የጎጃም ባህል ማዕከል በግንባታ እና በሃሳብ ደረጃ መሬት እንዲነካ እንደዚሁም የተለያዩ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡

አቶ ምግባሩ ከበደ ከ2008 ዓ.ም አንስቶ በሀገራችን እና በክልላችን የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በተከናወነው ተግባር የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ በዚህ ወቅት በሰሜን ጎንደር ዞን የታየውን አለመረጋጋት ወደ መረጋጋት ለመመለስ ከጓደኛቸው አቶ እዘዝ ዋሴ ጋር በተሰጣቸው ተልዕኮ በቦታው ተገኝተው ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ዞኑ የተረጋጋ እንዲሆን የአመራር ብቃታቸውን አሳይተዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ የተለያዩ ታሪካዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ካጠናቀቀ በኋላ የድርጅቱን ጽህፈት ቤት ብቃት ባላቸው ቁርጠኛ አመራሮች ለማደራጀት በነበረው ቁርጠኝነት አቶ ምግባሩ ከበደ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪ እንዲሁም የለውጥ መሪው አዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን የሽግግር ወቅት የሚመጥን ብቃት ያለው አመራር ሰጥተዋል፡፡

ከየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመሆን መስዋእት እስከሆኑበት ያለፈው ቅዳሜ ድረስ የፍትህ ተቋሙን ሪፎርም በመምራት መሰረት ጥለዋል።

አቶ ምግባሩ ከበደ በአማራ ክልልና በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ከትግል ጓዶቻቸው ጋር ተሰልፈው ብቃት ያላቸው የለውጥ መሪ መሆናቸውን ያረጋገጡ ፣ የህዝብን ጥቅም አስቀድመው ለአማራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች መብት መከበር በግንባር ቀደምትነት የታገሉ ጓድ ነበሩ።

አቶ ምግባሩ ከበደ ለውጡ በሂደት የሚያጋጥመውን ውጣ ውረድ ቀድመው በመተንተንና የመሻገሪያ ስትራቴጂና ታክቲኮችን በመንደፍ የፖሊሲ ሃሳቦችንና ፖለቲካዊ አቋሞችን ለህዝብ በማድረስ አሳማኝ መሞገቻዎችን በማቅረብ ብቃት ያለው አመራር ያረጋገጡ ጓድ ነበሩ።

ፈጣን አዳዲስ የለውጥ ሃሳቦችን የሚያመነጭ መፍትሄ ሰጪና ችግር ፈቺ አዕምሮ ባለቤት የነበሩት አቶ ምግባሩ ፣ ለህግ የበላይነት መከበር ፅኑ አቋም ነበራቸው፡፡ ከሰሜን ጎንደር አካባቢ በተጨማሪ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና በሰሜን ሸዋ ዞን አጎራባች ወረዳዎች አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈጠረውን አለመረጋጋት ወደ መደበኛ ሁኔታው እንዲመለስ ግጭቶች እንዳይባባሱና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲሻሻል ብቃት ያለውና ቁርጠኛ አመራር ሰጥተዋል።

አቶ ምግባሩ ከበደ ላመኑበት አቋም ግንባራቸውን የሚሰጡ ፅኑና ደፋር ታጋይ ነበሩ። ሙያዊ ብቃታቸው ከፍ ያለ፣ ጠንካራ ተደራዳሪ ፖለቲከኛ፣ ትሁት፣ ሰው አክባሪና ተግባቢ የመልካም ስነምግባር እና የከፍተኛ ትዕግስት ባለቤትም ነበሩ፡፡ ሰዎችን በአለቃና በሰራተኛ ግንኙነት ሳይሆን እንደ ጓደኛ የሚያዩ፣ ለመግባባትም ፈጣንና ውጤታማ አመራር ነበሩ።

አቶ ምግባሩ ከበደ በክልሉና በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለምንም እረፍት ሌት ተቀን እየሰሩ ባለቡት ወቅት የክልሉን መንግስት በሃይል ለማስወገድ ክልሉንና አገሪቱን የከፋ አደጋ ላይ ለመጣል ታስቦ በተቀነባበረውና ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ቅዳሜ ዕለት ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ፅህፈት ቤት የመስተዳድሩ ምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስብስባ ላይ በነበሩበት በተደረገ ጥቃት ከሌሎች ሁለት የስራ ባልደረቦቻቸው ማለትም ከዶክተር አምባቸው መኮንንና ከአቶ እዘዝ ዋሴ ጋር በጥይት ተመተው ተሰውተዋል።

አቶ ምግባሩ ከበደ መሰዕዋት ለአገሪቱና ለአማራ ክልል ህዝቦችና ለመላ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የልብ ስብራት በመሆኑ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ለትግል ጓዶቻቸው ለመላው የአማራ ክልልና የኢትዮጵያ ህዝቦች መፅናናትን እንመኛለን፡፡ አቶ ምግባሩ ከበደና የትግል ጓዶቻቸው ህዝቡን አስተባብረው የጀመሩት ትግል ዳር እንዲደርስ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደ ህዝብ አንድነታችንን የምናበረታታበት ወቅት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።

Share.

About Author

Leave A Reply