የአቶ ጌታቸው አሰፋ ጉዳይ፡ ፖለቲካዊ ወይስ ሕጋዊ መፍትሄ?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ከጥቂት ቀናት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመስሪያ ቤታቸውን የአምስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸውን እና መቀሌ የሚገኙትን የቀድሞው የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት በኩል ትብብር አለማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ከክልሉ ይሁንታ ካለመገኘቱም ጋር ተያይዞ “እሳቸውን ለመያዝ ሌላ ሰው መግደል የለብንም” በማለት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ የፌደራል መንግሥቱን አቋም አንጸባርቀዋል።

ይህንንም ተከትሎ በአንድ አገር ላይ የፌደራል መንግሥት በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ ሲጠይቅ ክልሎች ያለምንም ማንገራገርና ለህገ መንግሥቱ ታዛዥ በመሆን አሳልፈው ሊሰጡ ይገባል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ የክልሉ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት ተቀራርበው በመስራት ለጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊያበጁለት እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሚሰጡም አሉ።

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ክስ የቀረበባቸው አቶ ጌታቸው ጉዳይ፤ ፖለቲካዊ ወይም ህጋዊ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል የሚል የተከፋፈለ ስሜት በሚንሸራሸርበት ሰአት ከሕግ ጥያቄ ወጥቶ የፖለቲካ ጥያቄ የሚያደርገው ነገር መጀመሪያ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ ይናገራሉ።

ለዚህም የፌደራል ወይም የትግራይ ክልል መንግሥት ኃላፊነታቸውን ሊወስዱ ይገባል ባይ ናቸው።

ምንም እንኳን የፌደራል መንግሥቱ ባለው ስልጣን መሰረት የማንንም ፍቃድ ሳይጠይቅ ወደ የትኛውም ክልል ሄዶ በወንጀል የጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር የማዋል ስልጣኑ ቢኖረውም፤ ባላቸው የሻከረ ግንኙነት ምክንያት የፖለቲካ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል የሚሉ አካላት አሉ። ለአቶ ሙሼ ይህ የማያስማማቸው ጉዳይ ነው።

“ለኔ ማንኛውም ነገር ከህግ በታች ነው። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የህግ የበላይነት ላይ መተማመን ነው” ይላሉ።

የፌደራል መንግሥቱ የወንጀል ተጠርጣሪ አድርጎ ክስ እስከመሰረተባቸው ድረስ ማንኛውም ዜጋ በሚታይበት የህግ ስርአት መሰረት ነፃ፣ ገለልተኛ በሆነ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሊታይ እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ሙሼ፤ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ተጠቅመዋል አልተጠቀሙም የሚለውን በፍርድ ቤት ሂደት ተጣርቶ የሚደረስበት እንደሚሆን ይናገራሉ።

ለዚህ ሁሉ ግን የህግ የበላይነት ፅንሰ ሃሳብ ላይ ከስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚገባ አፅንኦት ይሰጣሉ።

የፖለቲካ ጥያቄ ለመሆን የሚያስችለው ጉዳይ ምንድን ነው? በማለት በዋነኝነት ጥያቄ የሚያነሱት አቶ ሙሼ፤ ”አቶ ጌታቸው እንደ ግለሰብ ባላቸው የፖለቲካ አቅም ነው? በዙሪያቸው የተሰባሰበው ኃይል አለ? ወይስ ክልሉ ነው የፖለቲካ ጉዳይ ያደረገው?” የሚለው መልስ ሊሰጥበት ይገባልም ይላሉ።

“ከነበራቸው የኃላፊነት ሁኔታ ጉዳዩ ታይቶ የሚያመጣውን ደስ የማያሰኝ ሁኔታ ለማረምና ለማስተካከል ተፈልጎ ከሆነ ጉዳዩን በውስጥ ውይይት መጨረስ ተገቢ ነው።” ይላሉ አቶ ሙሼ።

በጉዳዩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላናው ፖለቲካኛ ደግሞ ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው።

የፌደራል መንግሥት ጥያቄ ባቀረበው መሰረት፤ የትግራይ ክልል አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ የሚሰጥ ይመስልዎታል ወይ? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲመልሱ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ አሳልፎ መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህ ካልተከናወነ ግን በቀጣይ ፈታኝ ሁነቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።”የፌደራል መንግሥት በወንጀል የጠረጠረውን ግለሰብ ክልል አላስረክብም ማለት ሌላ መንግሥት መፍጠር ነው የሚሆነው፤ ይህ ደግሞ ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀጣይነት ፈታኝ ነው። መተባበሩ የሚመረጥ ይመስለኛል። ” በማለት ይናገራሉ።

በወንጀል የተጠርጠረ ሰው ሊያገኘው የሚገባው መብት ሳይነካ በፍትሃዊ መንገድ ጉዳያቸው እንዲስተናገድ ዋስትና ይሰጠኝ ብለው መጠየቅ ይገባቸዋልም ይላሉ ዶ/ር መረራ።

ወንጀለኛ ተብሎ የተጠረጠረን ሰው አሳልፎ ስለመስጠት ሕጉ የሚለው ግልፅ ቢሆንም፤ አሁን ባለው የሃገሪቱ ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ከፍተኛ ስጋትና፣ የኃይል ፍትጊያ በናረበት፣ ሃገሪቷን በሚመራው ኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈል እያለ በተለይም ኢህአዴግን እንደ ግንባር ተሰብስበው ከመሰረቱት ጥምር ፓርቲዎች መካከል አንደኛው ተነጥሎ ኢላማ በመደረግ ህብረተሰቡን ከፋፍሎታል የሚሉት በመቀለ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ዶ/ር መንግሥቱ አረፋይኔ ናቸው።

ስልጣን የያዘው ቡድን የብቀላ ፖለቲካ የሚመስል አካሄድ አለው በማለትም የፌደራል መንግሥቱን ይወነጅሉታል።

“አንድ ክልል እየተገለለ ለሁሉም ወንጀል ተጠያቂ ማድረግ ሰላምና መረጋጋትን ሊያመጣ አይችልም።” ይላሉ ዶ/ር መንግሥቱ አረፋይኔ።

ምንም እንኳን በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ወንጀል የሰሩ ግለሰቦች የየትኛውም ብሔር አካል ይሁን ማንኛውንም ቋንቋ ይናገሩ ተጠያቂ ሊሆኑ ቢገባም ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችንና ጦርነቶችን ማስቆም፣ መፈናቀልን መቀነስና ሃገሪቱ ከገባችበት ውጥንቅጥ የማረጋጋት ስራ መሰራት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህም ምክንያት ክልሉ አሳልፎ የመስጠት ያለመስጠት ቀላል ጥያቄ ነው ይላሉ።

“ለሃገሪቱ የሚያስብ መንግሥት ከሆነ የአንድ ወይም ጥቂት የግለሰቦች መታሰር ትልቅ ልዩነት አያመጣም።” ይላሉ

“ሃገሪቱ ውስጥ ብዙ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ተፈትተዋል፤ መንግሥት ላይ ጦር ያነሱ ሰዎች በሰላም ግቡ ተብለዋል። በአንድ በኩል የእርቅ መንፈስና ሂደት መንግሥት እያከናወነ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችን ሰዎች ማሰር ምን አመጣው?” በማለት ጥያቄ ያነሳሉ።

አቶ ሙሼ በበኩላቸው የትግራይ ክልል አሳልፎ ሊሰጥ ይገባል ወይም አይገባም ከሚለው በፊት፤ የአቶ ጌታቸው ጉዳይ የትግራይ ክልል ጉዳይ ለመሆን መነሻው ምንድን ነው? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው ይላሉ።

ከዚህ በተቃራኒው ግን ይላሉ አቶ ሙሼ “በአግባቡ ያሉትን ሕጎች፣ ሕገ-መንግሥቱን ማዕከል ከማድረግ ይልቅ ጉዳዩ የህዝብ ግንኙነትና የመድረክ ፍጆታ ነው የሆነው። ይሄስ ጉዳይ ለህዝብ ፍጆታ የሚውለው ለምንድን ነው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ምንም እንኳን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ የአቶ ጌታቸው አሰፋን ተላልፎ መሰጠት የትግራይ ህዝብ እንደሚቃወም ተደርጎ ቢቀርብም የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ አቶ ጌታቸው ለትግራይ ህዝብ አጀንዳ አይደሉም ይላሉ።

ለዚህም እንደ መነሻነት የሚያነሳው አቶ ጌታቸው ከነበራቸው ስልጣን ተነስተው ወደ ትግራይ ክልል በመጡበት ወቅት ጥያቄ አለመነሳቱን ነው።

“የትግራይ ህዝብ በአንድ ግለሰብ አቋም አይዝም ብየ ነው የማስበው። የአቶ ጌታቸው መያዝ ወይም አለመያዝ የህወሃት መሸነፍ ወይም አለመሸነፍ ተደርጎ መወሰዱ የብሔር ፖለቲካ ተደርጎ መወሰዱን ያሳያል።” ይላሉ አቶ አብረሃ።

ፓርቲያቸው አረናስ ሕጉን በተከተለ መልኩ ተላልፈው ሊሰጡ ይገባል ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “የኢህአዴግ ጉዳይ ነው። እርስ በርሳቸው ተነጋግረው፤ ተስማምተው መወሰን ይችላሉ። አሁን እየተከሰተ ያለው የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በውስጣቸው መከፋፈል ተፈጥሯል። ሕግም ማስከበር አይችሉም፤ ፖለቲካውን ማስተካከል አቅቷቸዋል። ህዝብን ማስተዳደር አቅቷቸዋል።” በማለት ይናገራሉ።

የአቶ አብርሃ አስተያየት ከአቶ ሙሼ የተለየ አይደለም። መፍትሄ ብለው የሚያቀርቡትም የክልሉ እና የፌደራል መንግሥታት በጉዳዩ ላይ በመወያየት ከስምምነት መድረስ ነው።

አቶ አብረሃ “ሕግ የሚኖረው ፖለቲካው ሲስተካከል ነው። ስምምነትና ትብብር ከሌለ ወደ ግጭት እንዲሁም ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል። ሰላማዊ ሰዎችም ሊጎዱ ይችላሉ።”

ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው የተያዙ የሜቴክ አመራሮችና ሌሎች ሰራተኞች እስርን ተከትሎ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል “ጉዳዩ ከሰብዓዊ መብትና ሙስና ጥያቄዎች ወጥቶ የትግራይ ህዝብን ወደመምታት የፖለቲካ እርምጃ ሄዷል።” በማለት ማውገዛቸው የሚታወስ ነው።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ ውንጀላውን በማጣጣል የትኛውም ብሔር ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ ገልጿል።

የትግራይ ክልል ጌታቸውን አሰፋን አሳልፎ የማይሰጠው በአንድ ብሔር ወይም በትግሬዎች ላይ ኢላማ ያደረገ ነው በሚል እምነት ከሆነ በግልፅ ሊናገር እንደሚገባ ዶ/ር መረራ ጉዲና አፅንኦት ይሰጣሉ።

“ወንጀለኞቹ እነማን እንደሆኑ እነ ዶ/ር ደብረ ፅዮን የተሻለ ስለሚያውቁ እነዚህን ወንጀል የሰሩ ሰዎችን ትታችሁ አንድን ብሄር ለምን ኢላማ አደረጋችሁ? የሚለውን በአደባባይ ይዘው ሊወጡ ይገባል” የሚሉት ዶ/ር መረራ፤ አክለውም “የኦሮሞና አማራ ሌባ ቁጭ ብሎ የትግራይ ብቻ የሚታሰርበት ምንም ምክንያት የለም። ያንን ለመጠየቅ ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ነው።” ይላሉ።

የትግራይ ክልል እስሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ነው የሚል ከሆነ የሚያቀርባቸው መረጃዎች ምንድንናቸው ብለው የሚጠይቁት ደግሞ አቶ ሙሼ ናቸው።የትግራይ ክልል አሳልፌ አልሰጥም ቢል በቀጣይ ምን ሊከሰት ይችላል?

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ አቶ ጌታቸውን ለመያዝ ሰው መግደል የለብንም ማለታቸው ይታወሳል። አቶ አብረሃም አቶ ጌታቸውን ለመያዝ የኃይል እርምጃ ሊወሰድ እንደማይገባ ይናገራሉ።

“አንድን ሰው ለመያዝ ተብሎ ወደ ጦርነት ይገባሉ ብዬ አላስብም የፌደራል መንግሥትም ፖለቲካውን ለማስተካከል ሲል ዝምታን ይመርጣል ፤ የትግራይ ክልልም የራሱን ህዝብ የራሱን ደህንነት ይጠብቃል ብየ አስባለሁ።” ይላሉ።

BBC

Share.

About Author

Leave A Reply