የአዲስ አበባውን የድጋፍ ሰልፍ ያስተባበረው ኮሚቴ “የመደመር ጉዞ” በሚል ወደ አስመራ የጉዞ ዝግጂት እያደረገ ነው።

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ለ፡ ኢፌዲሪ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን_ጉዳዮች ፅ/ቤት

ጉዳዩ፡- “ለመደመር_ጉዞ” ትብብር እንዲደረግልን ስለመጠየቅ

ከሁለት ቀናት በፊት ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ተከፍቷል። ለረጅም ዘመናት በአብሮነት ሲኖሩ የነበሩ የሁለቱ ሀገር ዜጎች ይህን ቀን በታላቅ ጉጉትና ናፍቆት ሲጠብቁት እንደነበር መገመት ይቻላል። በመሆኑም በሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተፈረመውን የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጀመርና ማጠናከር ያስፈልጋል።

በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣዩ ሳምንት እሮብ ሐምሌ 11/2010 ዓ.ም ወደ አስመራ በረራ እንደሚጀምር አስታውቋል። በተመሳሳይ የኤርትራ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ በረራ እንደሚጀምር እየተገለፀ ይገኛል። ይሁን እንጂ፣ “የመደመር ጉዞ” የተሰኘ ግብረ-ሃይል የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር፣ እንዲሁም የብዙሃኑን ጥያቄና ፍላጎት መሰረት በማድረግ የሚከተሉትን ዓላማዎች መሰረት አድርጎ ተቋቁሟል፡-

1ኛ፡- የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በተግባር ለማረጋገጥና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣

2ኛ፡- የየብስ ትራንስፖርት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር የተሻለ አማራጭ በመሆኑ፣

3ኛ፡- አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሆነ ኤርትራዊ የአየር ትራንስፖርት የሚጠይቀውን ወጪ ለመሸፈን ያለው አቅም ውስን በመሆኑ፣

4ኛ፡- የአየር ትራንስፖርት በአሁን ሰዓት ውስን ሰዎች ብቻ የሚያስተናግድ መሆኑን ከግምት በማስገባት፣

“የመደመር ጉዞ” በሚል በአስር (10) አውቶቢሶች አምስት መቶ (500) ሰዎች ወደ አስመራ ለመጓዝ ቅድመ-ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል። ስለዚህ አስተባባሪ ኮሚቴው የጀመረው የጉዞ ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የኢፌዲሪ መንግስት ትብብርና ድጋፍ በእጅጉ ያስፈልገዋል። በዚህ መሰረት የሀገራችን መንግስት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግልን እንጠይቃለን፡-

1ኛ፡- የመደመር ጉዞን ዓላማና ግብ ለኤርትራ መንግስት በማሳወቅ በእነሱ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግልን መጠየቅ፣

2ኛ፡- በኢትዮጵያ ከሚገኙ የኤርትራ ዲፕሎማቶች ጋር በመነጋገር ተጓዦች ወደ ኤርትራ ለመግባት ፍቃድ እንዲያገኙ ማድረግ፣

3ኛ፡- ከሁለቱ ሀገራት የፀጥታና ደህንነት አካላት ጋር በመነጋገር በጉዞ ላይ እክል እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ፣

4ኛ፡- በሁለቱ ሀገራት ድንበር አከባቢ ያሉት መንገዶች ለሰላማዊ ዜጎች ጉዞ አመቺ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣

5ኛ፡- ተጓዦች በኤርትራ በሚኖራቸው ቆይታ የውጪ ምንዛሬ ችግር እንዳይገጥማቸው የኢትዮጵያን ብር እንዲገበያዩ ወይም የኤርትራ ናቅፋ ምንዛሬ የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻችት ድጋፍና ትብብር ያደርግልን ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

ከሠላምታ ጋር

የመደመር_ጉዞ አስተባባሪ ኮሚቴ

Share.

About Author

Leave A Reply