የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዘጠኝ ወራት በኋላ የመሬት ሊዝ ጨረታ አወጣ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየወሩ የመሬት ሊዝ ጨረታ እንደሚያወጣ ቢደነግግም፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ያህል ሲቀረው በጉጉት ሲጠበቅ የቆየውን 29ኛውን የሊዝ ጨረታ አወጣ፡፡

29ኛው የሊዝ ጨረታ ከዚህ ቀደም የተለመደው ልማዳዊ አሠራር እንደማይኖር፣ ይልቁንም አስተዳደሩ ባበለፀገው አዲስ ሶፍትዌር ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ 29ኛው የሊዝ ጨረታ ሊዘገይ የቻለበትን ምክንያት ለሪፖርተር ሲገልጽ፣ ጨረታው በመሬት አቅርቦት ችግር የዘገየ ቢሆንም ከቅሬታ ነፃ የሆነ ዘመናዊ አሠራር መከተል ስለሚያፈልግ ሶፍትዌር የማበልፀግ ሒደት ጊዜ በመወሰዱ ነው ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት በ29ኛው የሊዝ ጨረታ በየካ 29፣ በቦሌ 36፣ በንፋስ ስለክ ላፍቶ ዘጠኝ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ሰባት፣ በአራዳ ስድስት፣ በአዲስ ከተማ አንድ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ 12 በድምሩ 100 ቦታዎች አቅርቧል፡፡

ቦታዎቹ ለመኖሪያ ቤት፣ ለቅይጥና ለቢዝነስ አገልግሎት ግንባታ የሚውሉ ናቸው፡፡ የጨረታ ሰነዱ ከግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ መሸጥ የጀመረ ሲሆን፣ ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጨረታውን በይፋ መክፈት እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

28ኛው ሊዝ ጨረታ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2008 ዓ.ም. የወጣ ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ በኋላ ባሉት ዘጠኝ ወራት ምንም ዓይነት የሊዝ ጨረታ አልነበረም፡፡

28ኛው ሊዝ ጨረታ ከተከፈተ በኋላም አሸናፊ ከሆኑ የተወሰኑ ሰዎች ጋር ውል ሊፈጸም ባለመቻሉ ከፍተኛ ውዝግብ ተቀስቅሶ ነበር፡፡ አስተዳደሩ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ጨረታውን የመሰረዝ መብት አለኝ በሚል አቋሙ በመፅናቱ አሸናፊዎቹ ሳይዋዋሉ ቀርተዋል፡፡

ምንጭ፤ ሪፖርተር

Share.

About Author

Leave A Reply