የአፍሪካ ህብረትና አውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት መፈራረማቸውን አደነቁ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአፍሪካ ህብረት እና አውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት መፈራረማቸውን አደነቁ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ባወጡት መግለጫ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈረሙትን የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት አድንቀዋል።

የሁለቱ ሀገራት የህዝባቸውን የጋራ ተጠቃሚነት በማስቀደም ግንኙነታቸን ለማሻሻል የወሰዱትን እርምጃ እንደሚያደንቁም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአሁኑ ወቅት የጀመሩት የሰላም ሂደትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 አፍሪካን ከጦር መሳሪያ ድምጽ ነፃ ለማድረግ ለተያዘው እቅድ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉም አወድሰዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በቀጣይም ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ለሚያነናውኑት ተግባራት የአፍሪካ ህብረት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ሊቀመንበሩ ሙሳ ፋቂ መሃመት አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ፥ ፥ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የተፈራረሙት የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት ታሪካዊ እና የሚደነቅ ነው ብሏል።

የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ፌድሪካ ሞግሄሀርኒ ባወጡት መግለጫ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈረሙት ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያሻሽል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላለፉት 20 ዓመታት በመካከላቸው የነበረውን ችግር በመፍታት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸው በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ቀጠናዊ ትብብር እንዲጠናከርና ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ነውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት አስተማማኝ ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ድረስም የአውሮፓ ህብረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቷ ገልፀዋል።

ግብፅ መንግስትም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪዎች አስመራ ላይ ተገናኝተው ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን እንደሚያደንቅ አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተገናኝተው መወያየታቸውም ለሀገራቱም ሆነ ለአካባቢው የሚኖረው አስተዋጽዎ ከፍተኛ መሆኑን የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የኤርትራ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል አዲስ መዕራፍ ከመክፈት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ፅጥታ እና መረጋጋትን ከማስፈን አንጻር ያለ ጥርጥር ከፍተኛ አስተዋጽዎ ይኖረዋል ብሏል።

በተያያዘ ዜና የሲዊዲን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርጎት ዎሊስትሮም ኢትዮጵያና ኤርትራ የፈረሙትን የሰላምና የወዳጅነት ስምምነትን እንደሚደግፉ ገልፀዋል።
ሲዊዲን ለሁለቱ ሀገራት አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።

በትናንትናው እለትም የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፖል ካጋሜ እና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ስምምነቱን ተከትሎ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ነኸያንም ስምምነቱን በማድነቅ፤ ሀገራቸው ሁለቱ ሀገራት በትብብር ሰላምና ብልፅግናን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታግዝም አረጋግጠዋል።

 

Share.

About Author

Leave A Reply