የኢሰፓና የሞረሽ ወገኔ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች አዲስ አበባ ገቡ፡፡

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በደርግ ጊዜ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩት እና በአሜሪካ በስደት ሲኖሩ የነበሩት አምባደር ዶ/ር ካሳ ከበደ  ዛሬ  ረፋድ  ወደ አገር ቤት ገቡ፡፡

ዶ/ር ካሳ ወደ አገር የገቡት መንግስት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው  ገብተው የለውጡ አካል እንዲሆኑ ባቀረበው ጥሪ መሰረት  ነው፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር  አቶ አህመድ ሺዴ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

አምባሳደር ካሳ ከበደ  በደርግ የስልጣን ጊዜ በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ ነበር፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የሞረሽ ለወገኔ የአማራ ሲቪክ ማህበር መስራች አና የአማራ ህልውና በኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አንቀሳቃሽ አቶ ተክሌ የሻው ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡

አቶ ተክሌ በስደት ከነበሩበት አሜሪካ ከ17 ዓታት ቆይታ በኃላ ነው ወደ አገር ቤት የተመለሱት፡፡

አቶ ተክሌ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰዳቸው የለውጥ እርምጃዎችና  የዲሞክራሲ ስርዓቱን አሳታፊ ለማድረግ  በጀመራቸው እንቅስቃሴዎች እና በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ተሳትፎ ለማድረግ ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡

በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታም ኢዴፓና ቅንጅት በነበራቸው የውጭ አገራት  እንቅስቃሴ ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበርና ከአማራ ጋር የተገናኙ ስራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

አቶ ተክሌ ስለ አንድነትና ኢትዮያዊነት እየተሰራ ባለው ስራ በመደሰቴ ወደ አገሬ ለመግባት ወስኛለሁ ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላም ሰላም፣ ፍቅርና እንድነትን  ለወጣቶች በማስተማር ተሳትፎ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትሩ አህመድ ሺዴና አቶ ተፈራ ደርበው በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ሀብታሙ ደባሱ

Share.

About Author

Leave A Reply