የኢቲ 302 የመጨረሻዎቹ ስድስት ደቂቃዎች

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በዓለም አቀፉ አሠራር መሰረት የተለያዩ አካላት ተሳትፈውበታል የተባለለት በአደጋው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላይ የቦይንግ 737 ማክስ 8 የበረራ ቁጥር የኢቲ 302 የመጨረሻ ደቂቃዎች የበረራ ታሪክ ዝርዝር መረጃ ወጥቷል።

የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር የተደረገውን ምልልስ፣ በበረራ መረጃ መመዝገቢያ ሳጥን ውስጥ የተገኘውን መረጃ እና ከአብራሪዎች ክፍል ውስጥ የተቀረጸውን ድምጽ ዋቢ አድርጓል። ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አብራሪ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ላይ በመመስረት የኢቲ 302 የመጨረሻዎቹ ስድስት ደቂቃዎች ምን ይመስሉ እንደነበር ለቢቢሲ እንደሚከተለው አስቃኝቷል።

እሁድ ጠዋት መጋቢት 1/2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንግድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የአየር መንገዱን 8 ሰራተኞችን ጨምሮ 157 መንገደኞችን በመያዝ ወደታቀደለት ናይሮቢ ኬንያ ለመብረር እየተዘጋጀ ነው።

ጠዋት 02፡37፡34- የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አውሮፕላኑ በረራውን እንዲያደርግ እና በ119.7 ሄርዝ ላይ በራዳር አማካኝነት ግንኙነት እንዲፈጽም ፈቃድ ሰጥተው አውሮፕላኑ ለመነሳት ዝግጅቱን ጀመረ።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አንድ አውሮፕላን እንዲነሳ ፍቃድ (ቴክ ኦፍ ክሊራንስ) ከመስጠታቸው በፊት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ያረጋግጣሉ።ከነዚህም መካከል በተመሳሳይ ሰዓት የሚነሱ እና የሚያርፉ አውሮፕላኖች አለመኖራቸውን፣ ለመንገደኞች የሚደረጉ የበረራ ላይ ደህንነት ገለጻዎች መጠናቀቃቸውን እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።

ከዚያም አውሮፕላኑ ተንደርድሮ ወደ ሚነሳበት የመንደርደሪያ ጥርጊያ (ራንዌይ) 07R (07ቀኝ ማለት ነው) መጠጋት ጀመረ። ማብራሪያውን የሰጠን አብራሪ እንደሚለው ከሆነ አውሮፕላን ተንደርድሮ የሚነሳበት መንገድ (ራንዌይ) ስያሜውን የሚያገኘው በአቅጣጫ መጠቆሚያ መሰረት ነው። አብራሪው ጨምሮም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥሮችም አውሮፕላኑ ወዴት እንደሚበር ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ኢቲ3xx ብለው የሚጀምሩ የበረራ ቁጥሮች መዳረሻቸው ምሥራቅ አፍሪካ ሲሆን ኢቲ5xx ብለው የሚጀምሩት ደግሞ ሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም ኢቲ6xx ብለው የሚጀመሩ የበረራ ቁጥሮች መዳረሻቸው ሩቅ ምሥራቅ ነው።

02፡37፡34 – የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ አውሮፕላኑን እያበረረ እንደሆነ ገልጿል። 02፡38፡44 – አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ወዲያውኑ ማለትም አውሮፕላኑ ለመነሳት መንቀሳቀስ ከጀመረበት ከአንድ ደቂቃ ከ10 ሰከንዶች በኋላ የአውሮፕላኑ በግራ እና በቀኝ ክንፉ በኩል አንግል ኦፍ አታክ ሴንሰር የተመዘገበው መረጃ ከተገቢው ውጪ መሆኑን ያሳያል።

02፡38፡46 – ረዳት አብራሪው ”Master Caution Anti-Ice” ማስጠንቀቂያ መምጣቱን ለዋና አብራሪው ሲናገር ተሰምቷል። ማስተር ኮሽን (Master Caution) በአውሮፕላን ሥርዓት ላይ አንዳች ችግር ሲያጋጥም ለአብራሪዎች የሚጠቁም ሥርዓት ሲሆን በዚህ ሰዓት የደረሳቸው ”Master Caution Anti-Ice” ማሰጠንቀቂያ የአውሮፕላኑን አካል ከከፍተኛ ቅዝቃዜ የሚጠብቀው አካል ችግር እንዳጋጠመው እንደሆነ አብራሪው ያስረዳል።

02፡38፡58 -ዋና አብራሪው ”ኮማንድ” በማለት አውሮፕላኑን ”አውቶፓይለት” ሥርዓት ላይ ለማድረግ ቢጥርም፤ አውሮፕላኑ አውቶፓይለት ላይ እንዳልሆነ የሚያስጠነቅቅ መልዕክት መጣ። አውቶፓይለት ማለት አውሮፕላኑ በተወሰነለት አቅጣጫ በእራሱ ሥርዓት እንዲበር የሚያደርግ ዘዴ ነው።

ከሁለት ሰከንዶች በኋላ ማለትም 02፡39፡00 ላይ ዋና አብራሪው በድጋሚ ”ኮማንድ” በማለት አውሮፕላኑን ”አውቶ ፓይለት” ሥርዓት ላይ ለማድረግ ቢሞክርም ከአንድ ሰከንድ በኋላ (02፡39፡01) አውሮፕላኑ አውቶ ፓይለት ላይ እንዳልሆነ የሚያስጠነቅቅ መልዕክት ከአውሮፕላኑ መጣ።

02፡39፡06 – ከአምስት ሰከንዶች በኋላ ማለት ነው፤ በዋና አብራሪው ትዕዛዝ ረዳት አብራሪው ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር ግንኙነት አደረገ። ረዳት አብራሪው ”SHALA 2A departure crossing 8400 ft and climbing FL 320” በማለት ሪፖርት አደረገ።
አብራሪው ይህንን ሲል ‘ሻላ 2ኤ’ ማለት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ የሚወስድ የተወሰነ የበረራ አቅጣጫ ሲሆን፤ 8400 ጫማ ከፍታ እያቋረጡ እንደሆነ እና 32000 ጫማ ከፍታ ይዘው እንደሚበሩ ነው ረዳት አብራሪው ሪፖርት ያደረገው።

02፡39፡45 – ዋና አብራሪው ፍላፕስ አፕ (Flaps up) በማለት ለረዳት አብራሪው ትዕዛዝ ሰጠ። ረዳት አብራሪውም ትዕዛዙን ተቀበለ። ፍላፕስ የአውሮፕላኑ አካል ሲሆኑ አውሮፕላኑ ከመሬት ለመነሳት በሚያደርገው ጥረት በቂ ፍጥነት እንዲያገኝ የሚያስችሉ ናቸው። ማብራሪያውን የሰጠን አብራሪ እንደሚለው የኢቲ 302 አብራሪዎች እንዳደረጉት ሁሉ አንድ አውሮፕላን ከተነሳ እና በቂ ከፍታን ከያዘ ፍላፕሶቹን ይሰበስባል።

02፡39፡50 – አውሮፕላኑ የበረራውን አቅጣጫ ከ072 ወደ 197 ዲግሪ መቀየር ጀመረ። በተመሳሳይ ሰዓት ዋና አብራሪው በተፈቀደው የበረራ አቅጣጫ ላይ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጠ።

02፡39፡55 – አውሮፕላኑ ከአውቶ ፓይለት ተላቀቀ (ዲስኢንጌጅ አደረገ)። 02፡39፡57 – ረዳት አብራሪው በዋና አብራሪው ጥያቄ መሰረት ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አውሮፕላኑን የመቆጣጠር ችግር እንደገጠማቸው አሳወቀ።

02፡40፡03- ”Ground Proximity Warning System (GPWS)” የተባለው የአውሮፕላኑ ሲስተም (ስርአት) ”ቁልቁል አትመዘግዘግ” (DON’T SINK) የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠ። ይህ ሲስተም አውሮፕላኑ ወደሚበርበት አቅጣጫ ከመሬት ወይም ከግዑዝ ነገር ጋር የመጋጨት አደጋ እንደተደቀነበት ለማሳወቅ ለአብራሪዎች መልዕክት ለመስጠት የተቀረጸ ነው።

02፡40፡03 እስከ 02፡40፡31 ድረስ ባሉት 28 ሰከንዶች ውስጥ ሦስት (GPWS) የ”DON’T SINK” ማስጠንቀቂያዎች ተመዝግበዋል። 02፡40፡27 – ዋና አብራሪው የአውሮፕላኑን አፍንጫ በአንድ ላይ ክፍ እንዲያደርግ ረዳት አብራሪውን ጠየቀው።

02፡40፡44 – ዋና አብራሪው ሦስት ግዜ ”ቀና አድርገው” (ፑል-አፕ) አለ፤ ረዳት አብራሪውም እንደተባለው አደረገ። 02፡40፡50 – ረዳት አብራሪው በዋና አብራሪው ጥያቄ መሰረት ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር ግነኙነት በማድረግ 14ሺህ ጫማ ላይ መቆየት እንደሚሹ እና በረራውን የመቆጣጠር ችግር እንዳጋጠማቸው አሳወቀ::

02፡41፡30 – አሁንም በድጋሚ ዋና አብራሪው ረዳት አብራሪው አውሮፕላኑን አብሮት ከፍ እንዲያደርግ ጠየቀ። እሱም እንደተባለው አደረገ። 02፡42፡10- ዋና አብራሪው ረዳት አብራሪው ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር ግነኙነት እንዲያደርግ እና መመለስ እንደሚፈልጉ እንዲያሳውቅ ነገረው። ረዳት አብራሪውም እንደተባለው አደረገ፤ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹም ፍቃድ ሰጡ።

02፡42፡30 – የአየር ትራፊክ መቆጣጣሪያውም ኢቲ 302 ወደቀኝ ዞሮ 260 ዲግሪ እንዲይዝ ትዕዛዝ ተሰጠው። ረዳት አብራሪውም ትዕዛዙን ተቀበለ።

02፡43፡04 – ዋና አብራሪው ረዳቱን አሁንም በድጋሚ አውሮፕላኑን አብሮት ከፍ እንዲያደርግ ጠየቀ። ዋና አብራሪው መልሶም አውሮፕላኑ በበቂ ሁኔታ ከፍ አለማለቱን ተናገረ።

አውሮፕላኑ አፍንጫውን እሰከ 40 ዲግሪ ደፈቀ። ስለክስተቱ የአደጋውን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት መሰረት አድርጎ ማብራሪያውን ለቢቢሲ የሰጠው አብራሪ እንደሚለው ከሆነ እንደየ አውሮፕላኖቹ የሚለያይ ቢሆንም አንድ አውሮፕላን ለማረፍ ሲቃረብ 3 ዲግሪ ያክል ብቻ ነው የፊተኛው አካሉ ዝቅ የሚለው።

02፡43፡43- ቀረጻው ቆመ።የአውሮፕላኑን መከስከስ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ለአውሮፕላን አደጋ መርማሪ ቢሮ አስታወቁ። ከደቂቃዎች በኋላም የኢቲ302 መከስከስ ዜና ተሰማ።

የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ አብራሪዎቹ በቦይንግ እና በአሜሪካ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዘንድ ተቀባይነት ያለውን የደህንነት ቅድመ ተከተል ተግባራዊ በማድረግ በበረራው ላይ ያጋጠማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን በግልጽ አመላክቷል። አብራሪዎቹ ተገቢውን እርምጃ ቢወስዱም ያጋጠማቸውን ያልተቋረጠ አውሮፕላኑ አፍንጫውን የመድፈቅ ችግርን መቆጣጠር ተስኗቸዋል።

Share.

About Author

Leave A Reply