የኢትዮጵያ ሆኖ ሳለ ‹‹የኦሮሚያ ካልሆንኩኝ›› የሚል መንግስት……

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢትዮጵያ ሆኖ ሳለ ‹‹የኦሮሚያ ካልሆንኩኝ›› የሚል መንግስት…… | በአሳዬ ደርቤ

‹‹ለውጥ መጣ›› ብለን ማውራት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ነውጦችን ስናስተናግድ ቆይተናል፡፡ ለማስረጃም ያህል፡-

-‹‹ከሌላ ክልል መጥታችሁ በእኔ ምድር ላይ አትኖሩም›› የሚሉ ሐይሎች ከ3 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን አፈናቅለዋል፡፡

-ከ8 ሚሊዮን የሚበልጥ ዜጋ በሰው-ሰራሽ ችግር የተነሳ የእለት ጉርሱን ተነፍጎ አፋጣኝ እርዳታ የሚፈልግ ሁኗል፡፡

– ‹‹የኔ መሬት ላይ የተመረተ ምርት ወደዚህ ክልል አይሄድም›› የሚሉ ሐይሎች መኪና አስቁመው የተጫነውን ሲያራግፉና ሲደፉ አይተናል፡፡

– ዜጎችን ለምግብ እጥረት የዳረጉ ሰዎች ‹‹የእርዳታ እህል አናስገባም›› ብለው መንገድ ሲዘጉና አንዱ በጥጋብ፣ ሌላው በርሃብ ሲንገላታ ታዝበናል፡፡

-በሰላማዊ መንገድ ይደራደሩ ዘንድ ወደ አገራቸው የተመለሱ ተቃዋሚዎች ምድር ላይ ካረፉ በኋላ ‹‹የኔ ወታደሮች ከሰፈሩበት ግዛት የመንግስት የጸጥታ ሐይሎች መርገጥ አይችሉም›› የሚል ክልከላ አምጥተው በአንድ አገር ውስጥ ሌላ አገር ለመመስረት ሲሞክሩ አስተውለናል፡፡

ብቻ በአጠቃላይ ‹‹የኔ አስፓልት፣ የኔ ምርት፣ የኔ መሬት፣ የኔ ቤት፣ የኔ ልማት…ለእኔ ማንነት ብቻ መሆን አለበት›› የሚሉ ሐይሎች በየጊዜው እየተነሱ በሌላው ሕይወትና መብት ላይ ሲረማመዱ ሰንብተዋል፡፡

ይሄም ሆኖ ግን አንደኛ ነገር የዚህን አይነት እኩይ ድርጊት የሚፈጽመው መላው ሕዝብ ሳይሆን የተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦች መሆናቸውን በመገንዘብ፣ በሁለተኝነት ደግሞ ያለንበት ጊዜ የሽግግር ወቅት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት… አዲሱ መንግስት በሁለት እግሩ መቆም ችሎ ችግሩን እስኪፈታው ድረስ በትዕግስት ሆነን ስንጠብቀው ከርመናል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የሆነ የጥፋት ድግስ ሲከሰት በድርጊቱ ላይ በቀጥታ ሲሳተፍ ያየነውን ቡድን በመውቀስ ፈንታ ከጀርባ ሆነው ሴራውን ይጠነስሳሉ የምንላቸውን ሐይሎች ስናብጠለጥል ሰንብተናል፡፡ መንግስትም ቢሆኑ የሚታየውን ትቶ የማይታየውን አካል ‹‹የጥፋቱ ጠንሳሾች›› እያለ እንደ እኛው ሲወነጅል ነበር፡፡

ታዲያ የሚያሳዝነው ነገር…. በአንዳንድ ወገኖች ሲፈጸም የነበረውን ይሄንን የጥፋት መንገድ ይዘጋዋል ብለን የምናስበው ድርጅት እሱ እራሱ የድርጊቱ ተሳታፊ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ በእኔነት ፈንታ እኛነትን ያሰፍንልናል ብለን የምናስበው አካል የዚህ እኩይ ሃሳብ ሰለባ ሲሆን እየታዘብን ነው፡፡

ለምሳሌ ያህል ትናንት ለገጣፎ ላይ የጨረቃ-ቤቶችን ያፈረሰችው ከንቲባ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያጋጥማት ‹‹ጩኸቱ የበረታው ከመሬታችን ላይ ያፈረስናቸው ቤቶች የእነ እንትና በመሆኑ ነው›› የሚል ገለጻ ስታደርግ ነበር፡፡

በቀደም ደግሞ ከሌሎቹ በላቀ መልኩ የለውጡም ሆነ የሥርዓቱ ባለቤት የሆነው ኦዴፓ ‹‹ የኮዬ ፈጨ ኮንዶሚንየም በእኔ መሬት ላይ የተገነባ ስለሆነ መሰጠት ያለበት ለእኔ ክልል ተወላጆች ብቻ ነው›› የሚል የአቋም መግለጫ አውጥቶ ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን ሰውተው እኒህን ቤቶች ሲጠባበቁ የኖሩ ሰዎችን ህልም አምክኗል፡፡

እኛም ይሄንን አስገራሚ መግለጫ ስንሰማ የምንጠብቀው ለውጥ አልፎን መሄዱን ወይንም ደግሞ ሳይመጣ መቅረቱን ተገንዝበን ከአዲሶቹ መሪዎች ላይ ያሳደርነውን ተስፋ ቆርጠን ለመጣል ተገደናል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም….. ከኢትዮጵያ ተነስቶ ሜድትራሊያን የሚገባው የአባይ ወንዝ የውሃው የአማራ፣ ግድቡ ደግሞ የቤኒሻንጉል መሆኑን ተገንዘብናል፡፡ አገራችን ላይ የተገኘው ድፍድፍ ነዳጅ የሶማሌ ክልል ሐብት መሆኑን አምነናል፡፡

በፌደራል በጀት የተገነቡት እና እየተገነቡ ያሉት የስኳር ፋብሪካዎች የክልሎች እንጂ የአገር ሐብቶች አለመሆናቸውን፣ በአንዱ ክልል ከተገነባ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ላይ በገመድ ተጠልፎ ወደሌላ ክልል የሚሄደው በህገ-ወጥነት መሆኑን በተዘዋዋሪ ከኦዴፓ ተረድተናል፡፡

አክሱም የትግራይ፣ ላሊበላ የአማራ፣ የያዮ ጥብቅ ደን የኦሮሚያ፣ የኮንሶ እርከን የደቡብ ሆኖ ሳለ….. በዩኔስኮ መዝገብ ላይ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች›› ተብለው መመዝገባቸው ስህተት መሆኑን በመግለጫው በተዘዋዋሪ ተብራርቶልናል፡፡

ምን ይሄ ብቻ…

በትዳሩ ላይ በመማገጥ ወንጀል በሚስቱ የተከሰሰ አባወራ ከኦሮሚያ መንግስት የቀሰመውን ልምድ ተግባር ላይ በመዋል ‹‹በራሴ ሰውነት ላይ የተፈጠረ ብልት የእኔ እንጂ የሚስቴ ስላልሆነ ማገጠ ተብዬ ልከሰስ አይገባኝም›› የሚል መከራከሪያ እስካቀረበ ድረስ በነጻ ሊሰናበት እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተውናል፡፡

ነገ ደግሞ ልክ እንደ ቤት እጣው … ነገ በስራ ጉዳይ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄደን የቆረጥነው የሎተሪ እጣ ቢወጣልን…. የክልሉ መንግስት የባለእድለኛውን ማንነትና የጃዋርን አስተያየት ካጣራ በኋላ ሎተሪው የተቆረጠው በእኔ ምድር ላይ በመሆኑ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ለባለእድለኛው ምንም አይነት ገንዘብ ከመስጠት እንዲቆጠብ አሳስባለሁ›› የሚል መግለጫ ሲያወጡ እንሰማ ይሆናል፡፡

ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ኢትዮጵያን የመምራት እድሉን አግኝቶ ‹‹የኦሮሚያ ብቻ ካልሆንኩኝ›› የሚለን መንግስት የማሰብ አቅሙ ተመልሶለት መተሳሰብን እንዲያስርጽብን እመኛለሁ፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply