የኢትዮጵያ ማርቺንግ ኦርኬስትራ ከአስመራ አቻው ሲነጻጸር ወደ ኋላ ቀርቷል። – ሰርጸ ፍሬ ስብሀት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር እየኾነ ያለው ኹሉ ከቃል አቅም እና ከመደነቅ ክኂል በላይ ነው፡፡ ጸጋው ለአካሎቻችን ኤርትራውያን ምን ስሜት እንደፈጠረ፤ ኹላችን ያየነው እና “ጉድ” ያስባለን ነገር ነው፡፡ ይህ ኹሉ እንግዲህ፤ ከላይ ከመንበረ ጸባዖት የተፈቀደ ቢኾን እንጂ፤ በዚህ ዓይነት ምልዓት እንዴት ሊሳካ ይችላል? ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡

በአስመራ ከተገለፀው ደስታ መሐል ትልልቅ ጥበቦችን መታዘብ ችያለኹ፡፡ ከኹሉ ያስደሰተኝ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በትልቅ ሙዚቃዊ ጥንቃቄ በማርቺንግ ኦርኬስትራው ሲከወን መስማቴ ነው፡፡ ከኤርትራ የማርቺንግ ኦርኬስትራ፤ የእኛዎቹ ወታደራዊ የሙዚቃ ክፍሎች ሊማሩት የሚገባ ቁም ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ ከግል ትዝብቴ ብነሳ፤ ብሔራዊ መዝሙራችን ዘብረቅረቅ እያለ እና እየተንጠባጠበ የሰማሁባቸው እና ያየሁባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ነበሩ፡፡ በተለይ የኤርትራን ልዑካን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ሲደረግለት የነበረው ትዝብት ውስጥ የሚከት የሙዚቃ አቀራረብ ይህንን ለማለቴ ዋቤ ይኾነኛል፡፡ ከዚህ አንፃር፤ በዓለም ሀገር ወክሎ የሚሰማውን ብሔራዊ መዝሙራችንን ልክና መልኩን አሳውቀን ማቅረብ ያለብን እኛ ነን እንጂ፣ የእኛን መዝሙር ሌሎች “እንዲህ ነው የሚዘመረው” ብለው እስኪያስደንቁን በጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ (ከተሳሳትኩ ለመታረም አላቅማማም፤)

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ክብር በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ የቀረቡት የኤርትራውያን የሙዚቃ ሥራዎችም በየመልካቸው በጣም ግሩም ነበሩ፡፡ “መተባበር ቢኖር”(1983 ዓ.ም) የሚለውን የንዋይ፣ የአረጋኸኝ፣ እና የጸጋዬን ዜማ አስመራ ላይ ሲዘመር መስማት ምን እንደሚፈጥር በቃላት መግለፅ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ከኹሉም ከኹሉም፤ በሀገረ ሰብዕ የሙዚቃ ባንድ ታጅበው የቀረቡት የኤርትራን የተለያዩ ጎሳዎች ወደ መድረክ ያመጡ ጨዋታዎች ዕጅግ የሚደነቁ ነበሩ፡፡ የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ዕይታ ብቻ ብዙ የሚያስብል ነው፡፡ የሳሎን ዝግጅት እንደመኾኑ “የሳውንድ” ችግር የነበረ ቢኾንም፤ የኤርትራ ሙዚቀኞችን ችሎታ ከማቀድነቅ የሚያቅብ ግን አልነበረም፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች እና ኤርትራውያን ሙዚቀኞች የጋራ ኮንሰርት አስመራ ላይ ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኦው…ለካ “አበባየሽ ወይ” የሚባለውም አስመራ ላይ ነው፡፡ ግሩም….ግሩም…ግሩም…!!!

Share.

About Author

Leave A Reply