የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ታስረው በዋስ ተፈቱ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፐሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ታስረው በዋስ ተፈቱ፡፡

አቶ ካሳሁን ለእስር የተዳረጉት ፍርድ ቤት በሚመሩት ተቋም ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲፈጽሙ በተደጋጋሚ ሲጠየቁ ሊፈጽሙ ባለመቻላቸው፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ አንደኛ አፈጻጸም ችሎት ትዕዛዝ በመስጠቱ መሆኑ ታውቋል፡፡

አቶ ካሳሁን የታሰሩት በሥራ ክርክር ምክንያት እንደሆነ ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ውስጥ ከሰኔ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በክትትልና ግምገማ ባለሙያነትና በሲኒየር ማኅበራዊ ጉዳይ ኤክስፐርትነት ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩት አቶ ሲሳይ ለሞምሳ የተባሉ ግለሰብ፣ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከሥራ መሰናበታቸውን ገልጸው በመሠረቱት ክስ ነው፡፡ ግለሰቡ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ እንዳስረዱት፣ በኢሠማኮ የክትትልና ግምገማ ባለሙያ ሆነው በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም. ተቀጥረዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ከነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ደመወዛቸው እንዲያድግ ከተደረገ በኋላ የሥራ ኃላፊነታቸውም ሲኒየር የማኅበራዊ ጉዳይ ኤክስፐርት መደረጋቸው ተገልጾ ደብዳቤ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሠራተኛውና ተቋሙ በሰላም እየሠሩ ለሦስት ዓመታት እንደቆዩ፣ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ የሥራ ውላቸው መቋረጡን እንደተነገራቸው በክስ ማመልከቻቸው ላይ ገልጸዋል፡፡

ከሦስት ዓመት በላይ በቋሚነት ሲያገለግሉ ቆይተውና ሥራውም ቀጣይነት እያለው እንደ ጊዜያዊ ሠራተኛ ‹‹ውሉ አልቋል›› ተብለው ከሥራ መሰናበታቸው ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ፣ ስንብቱ ‹‹ሕገወጥ ነው›› ተብሎ የካሳ፣ የማስጠንቀቂያ ጊዜ፣ የስንብት ክፍያና በተቋሙ ውስጥ ሊከፈላቸው ይገባ የነበረ የጉርሻ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው እንዲወሰንላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር፡፡

ተከሳሹ ኢሠማኮ (አቶ ካሳሁን) ለቀረበባቸው የክስ አቤቱታ በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፣ ከሳሽ የተቀጠሩት በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም. ሳይሆን ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ ከሳሽ የሥራ ውላቸው ሲቋረጥ መቋረጡን ተቃውመው አቤቱታቸውን ለአቶ ካሳሁን ማስገባታቸውን አረጋግጠው፣ ምላሽ ሳይሰጧቸው ግን ለሌላ ሥራ ወደ ክልል እንደላኳቸው የክስ አቤቱታው ያስረዳል፡፡ ባለሙያው በተላኩበት የመስክ ሥራ መሰናበታቸው ተገቢ መሆኑ ተነግሯቸው እንደ አዲስ ሥራ እንዲቀጥሉ ሲነገራቸው፣ አለመስማማታቸውን አቶ ካሳሁን ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከሳሽ የስንብት ደብዳቤያቸውን አልቀበልም ብለው ሥራቸውን የቀጠሉ ቢሆንም፣ የውል ጊዜያቸው ማለቁን ተከትሎ ስንብቱ መከናወኑ ተገቢ መሆኑንና ሊከፈላቸው የሚገባ ክፍያ እንደሌለ በመግለጽ፣ ምላሻቸውን መስጠታቸውን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይገልጻል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተለያዩ ጭብጦችን ይዞ ክርክሩን መመርመሩን፣ ምስክሮችንም ከሰማ በኋላም ሰበር ሰሚ ችሎች በመዝገብ ቁጥር 25526 የሰጠውን አስገዳጅ ትርጉም በማየት የመጨረሻ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ኢሠማኮ በከሳሽ ላይ የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ አለመሆኑንና የቀረበበትን ክስ ማስተባበል አለመቻሉን በመግለጽ፣ ከሳሽ ላቀረቡት ክስ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ኢሠማኮ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43(4ሀ) መሠረት 46,008 ብር የካሳ ክፍያ፣ በአንቀጽ 35(1ለ) እና 43(4ሀ) መሠረት የሁለት ወር ደመወዝ 15,336 ብርና በአንቀጽ 40(1 እና 2) መሠረት የስንብት ክፍያ 10,539 ብር፣ በልዩነት ሳይከፈላቸው የቀረ 7,486 ብርና ለደረሰባቸው የመጉላላት ኪሳራ 2,000 ብር በድምሩ 81,369 ብር እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ተቋሙ እንደ ፍርዱ ሊፈጽም ባለመቻሉ ፕሬዚዳንቱ አቶ ካሳሁንን ፎሎ በፖሊስ ታስረው ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የተሰጠ ቢሆንም ተበዳይ ግን፣ ‹‹ከአገር ወጥተው ላይመለሱ ይችላሉ›› የሚል ሥጋት ለፖሊስ በማመልከታቸው፣ ፖሊስ አቶ ካሳሁንን መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር አውሎ፣ በተቋሙ የውጭ ግንኙነትና ሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ መአሹ በሪሁ ዋስትና መፈታታቸው ታውቋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply