የኢትዮጵያ አንድነት በተገቢው ያልተወከለበት የዛሬው ጉባኤ (መሀመድ አሊ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

መድረኩ ግርታ ይፈጥራል። የአንድነቱ ጎራ ሳስቷል ወይም በአግባቡና በበቂ ደረጃ አልተወከለም። ባለፉት ግማሽ ምዕተ-ዓመታት ገደማ በሀገራችን የተካሄደውን ትግል ጠቅለል አድርገን ስናዬው በዋነኝነት የዘውግ አስተሳሰብን በሚያራምዱና የኢትዮጵያን አንድነት/ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅኑ ኃይሎች መካከል ነበር ማለት ይቻላል። በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች የመንግሥትን ሥልጣን ስለተቆጣጠሩ ዘውገኝነት ገዥ አስተሳሰብ ሆኖ የመውጣት ዕድል የታየበት ሲሆን; በአንፃሩ የኢትዮጵያዊነት/የዜግነት አስተሳሰብ የተሸነፈ መስሎ ታይቷል።

ዛሬ ላይ; ኢትዮጵያዊነት በሀገርና/በመንግሥት መሪዎች ደረጃ የሚቀነቀንበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የአንድነት ኃይሎች ባለፉት 27 ዓመታት በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባካሄዱት ትግል የመንግሥት ሥልጣን መያዝ ባይችሉም የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ እንዳይጠፋና መልሶ እንዲያንሠራራ እርሾ መሆን ችለዋል። በርግጥ ደጋግሜ እንደምለው “ኢትዮጵያዊነት በቀላሉ ሊጠፋ የማይችል የተዳፈነ ረመጥ ነው።” እናም “ረመጡን ከነካኩት በቀላሉ ሊቀጣጠል የሚችል” መሆኑ የነለማ መገርሳና/አብይ አህመድ ተሞክሮ ጥሩ ማሳያ ነው።

እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ግልፅ መሆን አለበት። ኢትዮጵያዊነት እነለማ/አብይ የፈጠሩት አዲስ አስተሳሰብ አይደለም። እነሱ ያደረጉት የተዳፈነውን ረመጥ መገላለጥ ብቻ ነው። ረመጡን ሲገላልጡት በቀላሉ ተቀጣጥሎ ብሩህ ዘመን ሲፈነጥቅ ታያቸው። እናም በዚህ ብርሃናማ አስተሳሰብ እየተመሩ የሄዱበት መንገድ አሁን ላሉበት የሞራል ከፍታ አበቃቸው። ምስጢሩ ይኸው ነው። ከዚህ በተቃራኒ ያለው ትርክት ገለባ ነው። ገለባው ረመጡን አዳፍኖ የማቆዬት አቅም እንደሌለው በተግባር ተፈትኗል።

ይሁንና በዚህኛው መድረክ የአንድነቱ ጎራ በአግባቡና በበቂ ደረጃ አለመወከሉ ሆድ ያስብሳል። ለዚህ ግን እነዶ/ር አብይ ተጠያቂ አይደሉም። ለዚህ ዋነኛው ተጠያቂ በተለይ የወያኔው ሥርዓት ነው። ወያኔና ግብረ-አበሮቹ እንደድርጅትና የያዙትን የመንግሥት ሥልጣን በመጠቀም የአንድነቱን ካምፕ ለማፈራረስ ባለ በሌለ ኃይላቸው ተረባርበዋል። የአንድነቱ ጎራ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰነዘሩበትን ከባባድ ጡጫዎች በመቋቋም እየተንገዳገደ ለመቆምና ለመራመድ ቢሞክርም; ተቀናኞቹን እስከመጨረሻ ካልደመሰሰ የሥልጣን/የህልውና ደህንነት የማይሰማው የወያኔ ሥርዓት በተለይ የ1997 ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ከፍተኛ ምት አሳርፎበታል።

የቀረውን እኛው ጨረስነው ማለት ይቻላል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአንጋፋ ሰዎቻችን ላይ ሆ! ብለን ዘመትንባቸው። እነሱ የሞቱላቸውን; የታሰሩላቸውን; የተሰደዱላቸውን ዓላማዎችና እሴቶች ጥያቄ ውስጥ አስገባናቸው። በዕድሜ ብቻ ሳይሆን በዕውቀትና በአስተሳሰብ የገዘፉ ሰዎቻችንን እየተንጠራራን በስድብ አጮልናቸው። ታላላቆቻችንን እንደዋዛ እየዘረጠጥን ጭቃ ላይ አንደባለልናቸው። እናም የአንድነቱን ጎራ ሰው አልባ አደረግነው።

እኔም መድረኩን ሳዬው ሆድ ብሶኛል። እኔ የማውቀው በእንዲህ ዓይነት መድረኮች እንደ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል; ፕ/ር መስፍን; ዶ/ር አድማሱ ገበየሁ; ዶ/ኃይሉ አርኣያ; ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማሪያም; ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው; ክፍሌ ጥግነህ; ሻ/ቃ አድማሱ መላኩ; ልደቱ አያሌው; ሙሼ ሰሙን… ወዘተ የመሳሰሉ ጉምቱና ለዐይን የሚሞሉ ሰዎች ሲንጎባለሉበት ማዬት ነው። ከዚህ አንፃር መድረኩ ቢሳሳብኝ አያስገርምም።

በርግጥ ዛሬ ላይ እነኢ/ር ኃይሉ ሻውልን የመሳሰሉ የአገር አድባሮች በዚህ ዓይነቱ መድረክ ተሰይመው ማዬት የማይሆን ምኞት ነው። ይህም ሆኖ ግን; ሌላው ቢቀር “ምናለበት በህይወት ኖረው የነአብይን ዘመነ-መንግሥት ለማዬት ቢታደሉ ኖሮ” ብዬ ሳስብ ዐይኔ የቋጠረውን እንባ ዘረገፈው። ግን ምን ዋጋ አለው?!

“ዱሮ ነበር እንጅ አልሞ መደቆስ;
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ”
እንዲሉ ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply