የኢትዮ- ኤርትራ የሰላም ጥሪ አማራጭ ሓሳብ (አብረሀ ደስታ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ውል “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ” መቀበሉ ሰምተናል። በዚሁ መሰረት ለኤርትራ የተወሰኑ የኢትዮጵያ መንደሮች ተላልፈው ይሰጣሉ ማለት ነው።

ሲጀመር ይህ አሰራር ህገ ወጥ ነው። አንድ ፓርቲ በሀገር ጉዳይ ላይ መወሰን አይችልም። መወሰን የነበረበት በኢትዮጵያ መንግስት ነው። ፓርቲና መንግስት ይለያያሉና። ይህ ጉዳይ በፌደራል መንግስት ብቻ የሚወሰንም አይደለም፤ ፌደራላዊ ስርዓት ነው ምንከተለውና። በፌደራላዊ ስርዓት አወቃቀር ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በራሳቸው አስተዳደር ላይ የመወሰን ህገመንግስታዊ ስልጣን አላቸው። እነዚህ ወደ ኤርትራ እንዲዛወሩ የተወሰነባቸው የኢትዮጵያ ወረዳዎች ፍላጎታቸውን አልተጠየቁም። እነሱን ሳይመክሩበት የሚወሰን ውሳኔ ኢ-ፍትሓዊም ሕገወጥም ነው፤ ውሳኔው በነሱ ህይወት ላይ የሚተላለፍ ስለሆነ።

የዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤት የወሰነው ስለሆነ ምን ማድረግ እንችላለን? የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተጀመረው ሻዕብያ የኢትዮጵያን መሬት በመውረሩ ነው። የኢትዮጵያ ሰራዊት ባከባቢው ባልነበረበት ወቅት ሻዕብያ ባድመ እና ሌሎች አከባቢዎች በሓይል ተቆጣጥሮ ጠንካራ ምሽግ ገንብቶ ነበር። ሀገር ስትወረር ለመከላከል ወደ ጦርነት ትገባለህ። ገባንም።

ጦርነት መጥፎ ነው፤ በሁለት ወንድማማቾች መካከል የተደረገ መሆኑ ደግሞ አስከፊ ያደርገዋል። ጦርነቱን ለማስቀረት ችግሩ በድርድር መፍታት ነበረብን። ጥረት ተደርጓል። ሻዕብያ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ፍቃደኛ አልነበረም። ከጦርነት ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረንም። ሻዕብያን አሸንፈን መሬታችንን አስመለስን።

ብዙ መስዋእት ከፍለን መሬታችንን ካስመለስን በኋላ ግን የኢህአዴግ መንግስት ከባድ ስህተት ሠራ፤ ወደ ድርድር ገባ። ከጦርነት በኋላ ድርድር!? ድርድር ኮ የሚደረገው ጦርነትን ለማስቀረት ነው። አንድ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ነው። ወይም ከጦርነት በኋላ ድርድር ከተደረገ ተሸናፊውን ለመቅጣት ያለመ እንጂ የአሸናፊውን ድል ለመቀልበስ አይደለም። አሳዛኝ!

ግን ከጦርነት በኋላ ወደ ፍርድቤት ተኬደና የኢትዮጵያ መሬት ለኤርትራ ተሰጠ። የፍርድቤቱ ውሳኔ “የመጨረሻና አሳሪ Final and Binding ነው” ተባለ። አያይዞም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች ከግጭት ቦታው 25 ኪሜ እንዲርቁ አዘዘ። የዓለም ዓቀፉ ፍርድቤት ውሳኔ ይግባኝ የማይባልበት ነው። ግን በህጉ መሰረት አንዱን ወገን (Party) የውሳኔውን አንድ አካል (Provision) ከጣሰ/ካፈረሰ ሌላኛውን ወገን (Second party) ውሳኔውን ውድቅ (Void) የማድረግ መብት አለው። የሻዕብያ መንግስት “ከድንበሩ 25 ኪሜ መራቅ” የሚለውን የውሳኔው አካል በመጣስ ወደ ድንበሩ ተጠግቶ የሰላም አስከባሪ ሐይሉ ማባረሩን ይታወሳል። ስለዚህ ሻዕብያ የፍርድቤቱን ውሳኔ ጥሷል ማለት ነው። በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ለማክበር ምትገደድበት ህጋዊ ማዕቀፍ የለም።

ታድያ ምን ማድረግ አለብን? ችግሩ ሳይፈታ 20 ዓመት ሆኖታል። በሁለቱም ሀገሮችና ህዝቦች መካከል ሰላም የለም (No War -No Peace)። ሁለቱም ህዝቦች ተቆራርጠዋል። ባከባቢው የሚኖር ህዝብ ክፉኛ ተጎድቷል። እናም ችግሩ መፍትሔ ማግኘት አለበት። ሰላም መስፈን አለበት። ጥያቄው ሰላም እንዴት ማስፈን ይቻላል? የሚለው ነው።

ኢህአዴግ “የፍርድቤቱ ውሳኔ ተቀብለን እንተገብራለን” ሲል ትኩረቱ ምንድነው? የመቀበሉ ዓላማ ምንድነው? ሰላም ለማስፈን ነው? ወይስ የፍርድቤቱ ውሳኔ ለማክበርና ለማስከበር ነው? ህግን ለማክበር ከሆነ የተጣሰውን ህግ ለማክበር የራሳችንን ዜጎች መብትና ህግ በመጣስ መሆን የለበትም። ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት የማክበር ግዴታ የለባትም፤ ሻዕብያ ጥሶታልና። ውሳኔው ኢ-ፍትሓዊም ጭምር ነው። የነዋሪዎች ህይወት ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም።

“የአልጀርሱን ስምምነት የምንተገብረው በሁለቱም መካከል ሰላም ለማውረድ ነው” ከተባለ ግን የፍርድቤቱ ውሳኔ በሁለቱም ሀገሮች ሰላም የሚፈጥር ሳይሆን ችግሩን የሚያባብስ ነው። ችግሩ የተፈጠረው ኢትዮጵያ ውሳኔውን ስላልተቀበለች አይደለም፤ ከፍርድቤቱ ውሳኔ በፊት ግጭት ነበርና። እስካሁን ውሳኔውን እንዳይተገበር የተደረገውም መፍትሔ እንዳልሆነ ስለታወቀ ይመስለኛል።

አሁን ዙርያ ጥምጥም ሳንሄድ አሁን ያለንበት ሁኔታ ላይ ሁነን ሰላም መስፈን አለበት ወይስ የለበትም? ሰላም መስፈን አለበት አራት ነጥብ። ሰላም መስፈን ያለበት የት ነው? ችግሩ የተፈጠረበት ቦታ ላይ! ኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አከባቢ።

መጀመርያ የኢትዮጵያ መሬት ተወረረና ግጭት ተፈጠረ። ዜጎችም ከቀያቸው ተፈናቀሉ። ድንበር አከባቢ በመሆኑ የሁለቱም ሀገሮች ዳር ድንበር (ዶብ) ተዘጋ። ፍርድቤቱም አጨቃጫቂው መሬት ለኤርትራ ወሰነ። ግን እስካሁን ተላልፎ አልተሰጠም። ኢትዮጵያውያን ይኖሩበታል። ለዚህም ነው ሰላሙም ጦርነቱም የሌለው። አሁን አጨቃጫቂው መሬት ወደ ኤርትራ ይካለል ሲባል እንደገና ማጨቃጨቁ አይቀርም። ምክንያቱም ዜጎች አሉ፤ ከቀያቸው መፈናቀል የማይፈልጉ ኢትዮጵያውያን! ዜጎቹም ከነ መሬታቸው ለኤርትራ አሳልፈን ልንሰጣቸው ነው? ፍርድቤቱ ኮ መሬቱን እንጂ ነዋሪውን ለኤርትራ አልወሰነም። ወይስ ከቀያቸው አፈናቅለን ሌላ ቦታ ልናሰፍራቸው ነው? ቤተሰቦች እና ብሄረሰቦች ኮ ለሁለት ይከፈላሉ። የኢትዮዮያ ህገመንግስት ብሄር ብሄረሰቦች ሳይከፋፈሉ ራሳቸው በራሳቸው እንዲተዳደሩ መብት ይሰጣልኮ። ወይስ ህገመንግስታቹ የኢሮብ ብሄረሰብ ላይ ሲደርስ አይሰራም? ያከባቢው ነዋሪዎች ተከፋፍለውና ተፈናቅለውስ እንዴት ባከባቢው ሰላም ይኖራል? ያከባቢው ህዝብ መሬቱ ተነጥቆ እንዴት ሰላም ይሆናል?

ሲጀመር ሰላም ምንድነው? ለማነው ነው? ባከባቢው ሰላም ተፈጠረ ቢባልና ወታደሩ ካከባቢው ቢወጣ ሰላም የሚያስፈልገውኮ እዛ የሚኖር ህዝብ ነው። መሬቱ የተነጠቀ ህዝብ እንዴት ሰላም ይኖረዋል? እንዴት መሬት ነጣቂ እና ተነጣቂ አብረው ይኖራሉ? ቦርደሩ አከባቢ ሰላም ከሌለ እንዴት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ይሆናሉ?

ልክ ነው። የአከባቢው ህዝብ በችግሩ ምክንያት ተጎድተዋል። ሰላምም ይፈልጋል። የቦርደሩ መከፈት ይፈልጋል። መረዳት ያለብን ጉዳይ ግን አለ። እዛው የሚኖር ህዝብ የችግሩ ቀማሽ በመሆኑ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ ሲወተውት “መሬታችን ከኛ ነጥቃቹ ለኤርትራ ስጡት” እያለ አይደለም። ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋራ በፍቅር መኖር እንፈልጋለን፣ ንግድ ማከናወንና ማህበራዊ ህይወታችንን እንደገና ማደስ ስለምንፈልግ ዶቡ (ድንበሩ) ይከፈትልን፤ እንደፈለግንን እንግባ እንውጣበት እያለ ነው።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም ለመመለስ ቦርደር አከባቢ ያለው ህዝብ ሰላም ሊኖረው ይገባል። ሰላም እንዲኖረውም መሬቱ ሊወሰድበት አይገባም፤ ሊከፋፈል አይገባም። ቦርደሩ ሰላም ካልሆነ ከኤርትራ ጋር ምን ዓይነት ጠቃሚ ግንኙነት ይኖረናል? ንግድ ማከናወን? የዓሰብ ወደብን መጠቀም? በየት በኩል? አይቻልም።

መሬቱ ተሰጥቷል ተብሎ የኢትዮጵያ ወታደር ከባድመ ይውጣ እንበል። የባድመ ህዝብ መሬቴን አለቅም አለ። የኤርትራ ወታደር ባድመ ይገባና ይቆጣጠረዋል። ኢትዮጵያኖችም ይባረራሉ ወይ ታፍነው ይወሰዳሉ። ሰላም ሰፈነ? የኢትዮጵያ ወታደርስ ዝም ይላል? ለሰላም ብለህ መሬት መስጠት ችግሩን ያባብሰዋል።

ምን ይደረግ? አማራጭ ሓሳብ! የአልጀርስ ስምምነት ከመተግበር (መሬት ከመስጠት) ይልቅ ዕርቅ ይቅደም። ለምሳሌ ኢህአዴግ እና ህግደፍ (ሻዕብያ) ይታረቁ። ወታደሮቻቸውም ከድንበሩ ያስወጡ። የተዘጋውን ዶብ ይከፈት። ያከባቢውን ህዝብ ንግዳዊ ይሁን ማህበራዊ ግንኝነቱ እንደገና ይጀምር። ቦርደር አከባቢ ሰላም ይፈጠር። የተጣለ ህዝብ ካለም እንዲታረቅ ይደረግ። ዕርቅ ሳይፈፀም መሬት መስጠት ግን ችግሩን ማባባስ ነው።

ከሁሉም በላይ ግን ችግሩን ለመፍታት እዛው ቦርደር አከባቢ የሚኖረውን ህዝብ ማነጋገር ይኖርብናል። መፍትሔ ሓሳብም ይሰጠናል። የሁለቱም ሀገሮች ችግር መንስኤ የመሬት አለመሆኑም መረዳት አለብን። ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት እውነተኛውን መንስኤ (የፖለቲካ ኢኮኖሚ አለመጣጣም) መፈተሽ ነው።

ዕርቅ ሳይፈፀም ዶብ ለማካለል መጣደፍ የሁለቱም ሀገሮች ህዝብ ያራርቃል እንጂ አያቀራርብም። ዶብ ኮ ህዝብን ከህዝብ ጋር ለመለያየት የሚተከል ዕንቅፋት ነው። ዶብ ስለተካለለ ብቻ የህዝብ አንድነት አይመጣም።

እናም የኢህአዴግን “የሰላም ሐሳብ” የምቃወመው በሁለቱም ሀገሮች ሰላም እንዲሰፍን ስለማልፈልግ ሳይሆን የመሬት መስጠቱ ጉዳይ ሰላም የሚያመጣ ሳይሆን ሰላምን በባሰ ሁኔታ የሚያጠፋ መሆኑ ስለምረዳ ነው።

ሰላም ይስፈን። አሜን!

Share.

About Author

Leave A Reply