የኤርትራው ፕሬዘዳንት የአማራ ከተሞችን መጎብኘታቸውን በተመለከተ ከአብን የተሠጠ መግለጫ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አደጉበትና ፊደል ወደቆጠሩበት የአማራ ምድር እንኳን ደህና መጡ እያልን የፕሬዘዳንቱ መምጣት የአማራንና የኤርትራን ህዝብና የመንግሥት ግንኙነት የሚያጠናክር በመሆኑ አብን በመልካም ጎኑ ይመለከተዋል።
..
የአማራና የኤርትራ ህዝብ ለዘመናት አብሮ በመኖር የተገመደ ማንነት ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር በንግድ ትሥሥር እና በድንበር መጋራት ተጎራብቶና ተከባብሮ የኖረ ህዝብ ነው። በሁለቱ ሀገራት የነበረውን ጦርነት ተከትሎ ትውልድ ኤርትራዊያን በብዛት ከሀገር እንዲወጡ ሲደረግ የአማራ ህዝብ በአማራ ምድር ይኖሩ የነበሩ ኤርትራዊያንን በጓዳው በመሸሸግ ከወከባ እንዲድኑ ከማድረጉም ባሻገር ወደ ኤርትራ የተመለሡ ኤርትራዊያንን በለቅሶና በሀዘን ሀብት ንብረታቸውን ይዘው እንዲወጡ በማድረግ የክፉ ቀን አለኝታነቱን አሥመሥክሯል። ሀብት ንብረታቸውን ጥለው የወጡ ኤርትራዊያንን ንብረታቸውን ጠብቆ በማቆየት ለባለቤቶቹ የመለሠ ለመሆኑ ከሠሞኑ ከ20 አመታት በፊት ጥለውት የሄዱትን ቤት ሲጠብቅ ቆይቶ ያሥረከበው የደብረማርቆሡ አማራ እንደ ማሳያ የሚጠቀሥ ይሆናል። የአማራና የኤርትራ ህዝብ ሠፊ ድንበር የሚጋሩ ህዝቦች እንደመሆናቸው መጠን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ሁለቱንም ህዝቦች የሚጠቅም ይሆናል ብሎ አብን ያምናል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኤርትራው ፕሬዘዳንት ከዚህ በፊት በአማራ ህዝብ ላይ በሀሠት ይሠበክ የነበረውን የቅኝ ገዥነት ትርክት በማሥተካከል በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረውን የመልካም ጎረቤትነት ታሪክ ይመልሳሉ ብለን እናምናለን። በዚህ አጋጣሚ የኤርትራ ህዝብና መንግሥት የአማራ ህዝብ ለነጻነት እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ትግል እንዲደግፉ ጥሪ እናቀርባለን።

የፕሬዘዳንት ኢሳያስ ቆይታ መልካምና የተሳካ ይሆንላቸው ዘንድ እየተመኘን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አድጎና ፍሬ አፍርቶ የቀደመ መልካም ግንኙነታችን እንዲጠናከር አብን የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ!

Share.

About Author

Leave A Reply