የእስክንድር ነጋ እና የአዲሱ አረጋ “ፌስታል”

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

እስክንድር ነጋ የታጋይ ተምሳሌት ነው፣ ሀሳብን ነፃነትን በመግለፅ ተምሳሌነት ነው። ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ተምሳሌት በመሆኑ ለበርካታ ጊዜ ተሸልሟል። እስክንድር ነጋ ለዓለም ተምሳሌት ሆኖ በተሸለመበት ወቅት እነ አዲሱ አረጋ ለትህነግ/ሕወሓት አቤት ወዴት የሚሉ ታዛዥ ካድሬዎች ነበሩ።

እስክንድር ለበርካታ ጊዜ በተምሳሌትነት ዓለም ሲሸልመው አፋኝነት፣ ድንቁርና ስለማያሸልም ነው እንጅ ትህነግ ሕወሓት በአፋኝነቱ በድንቁርና ዓለም ያወቀው ነበር። ለዚህ ድንቁርና አፋኝነቱ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የወሰዱት ታዛዦቹ ናቸው። ካድሬዎቹ ናቸው። እነ አዲሱ አረጋን የመሰሉ ትህነግሕወሓት አንዴ ሲጠራቸው አራት ጊዜ አቤት የሚሉ ካድሬዎቹ ናቸው በዓለም ለታወቀበት ድንቁርና የዳረጉት። አዲሱና እስክንድር የተለያዩ ሰዎች ናቸው። የሁለት ዓለም ሰዎች ናቸው። እስክንድር የበጎ ተምሳሌት ሆኖ ሲሰራ፣ አዲሱ ለጨለማው ዓለም ለሚሰራውና በድንቁርናው ለታወቀው ስርዓት ባሪያ ነበር። እስክንድር እስር ቤት ውስጥ የነፃነት ተምሳሌት ሲሆን እነ አዲሱ ከእስር ቤት ውጭ፣ ዓለምን እየዞሩ ከዓለም የማይማሩ የትህነግ ታፋኞች፣ ታዛዥ አፋኞች ነበሩ። እስክንድር ለነፃነት ሲል እስር ቤት ሲገባ፣ አዲሱ ድንቁርና መርጦ ከእስር ቤት ውጭ ታዛዥ ነበር።

የሰውን ልጅ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደሕንነት፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ያገደው የድንቁርና ስርዓት ስር ስር እነ አዲሱ አረጋ ነበሩ። ይህ የድንቁርና ስርዓት እንዲያከትም እስክንድር በብዕሩ ታግሏል። ያኔ እነ አዲሱ መብት የሚባል እንኳ አያውቁም። ዲሞክራሲ፣ ለውጥ የሚባልን ነገር የሚያርዳቸው የሕሊና ባርያዎች ነበሩ። እነ አዲሱ ሳይታሰሩ ለገንዘብና ስልጣን ታሰሪ ሲሆኑ እስክንድር ታስሮ እንኳ ለዓለም ማሕበረስ የእነ አዲሱን አዛዦች ድንቁርና አጋልጦታል። አዲሱማ ከዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ታዛዥ ነበር። የትህነግሕወሓት ፌስታል ነበር። እንደ ፌስታል መጠቀሚያ ነበር።

ትህነግ/ሕወሓት በዓለም ማሕበረሰብ እንዲጋለጥ ትልቁን ስራ የሰሩት እነ አዲሱ ውጭ ሆነው በሚላላኩበት ወቅት እስር ቤት ውስጥ የነበሩት እነ እስክንድር ነጋ ናቸው። ትህነግ ሕወሓት መቀሌ እንዲመሽግ እነ እስክንድር ለትውለዱ ፅናትን፣ እምብይተኝነትን አስተምረዋል። ትውልዱ አደባባይ ደፍሮ እንዲወጣ እነ እስክንድር እስር ቤት ሆነው እንኳ ባገኙት አጋጣሚ ሲያስተምሩ፣ ተምሳሌት ሲሆኑ እነ አዲሱ አረጋ ከእነ መለስ ዜናዊና ጌታቸው አሰፋ መንግስት ጋር አብረው በማስገድና በማሳሰር ነው የድንቁርና ስርዓቱ እንዲቀጥል ታግለዋል። ሆኖም የእነ እስክንድርን የለውጥ መንፈስ፣ የትግል ፈር አላሸነፉም።

እነ እስክንድር ሲታገሉበት የነበረው ዘመን ለእነ አዲሱ ሩቅ ነው። ባያስታውሱት አይገርምም። እነ እስክንድር ፌስታል ይዘው ከእስር ቤት የወጡት ለበርካታ አመታት በፅናት የታገሉለት ትግል ፍሬ በማፍራቱ እንጅ የትህነግ ሕወሓት ተላላኪና ፌስታል ተሸካሚ ዛሬ በበርካቶች መስዋዕትነት መናገር ስለቻለ በየ አደባባዩ እንደሚደነፋው አይደለም። እንደ ሕወሓት ፌስታል ተሸካሚዎችና ተላላኪዎች አላማ ቢሆን ኖሮ ቄሮ አደባባይ መውጣት ሳይሆን ሁለት እግሩን እንደተቆረጠው ምስኪን፣ እስር ቤት ውስጥ እንደተገደሉት ሰማታት በሆነ ነበር። የእነ እስክንድር አይነቱ ፅኑ የዘመኑን ትውልድ አደባባይ እንዲወጣ ሲያደርግ የእነ አዲሱ አይነት የሕወሓት ተላላኪና ፌስታል ያዥ ደግሞ ወጣቶችን ሲያሳስር ኖሯል።

የእነ እስክንድር ትግል ወጣቶች አደባባይ እንዲወጡ ሲያደርግ የእነ አዲሱ አይነት ካድሬ ተግባር በርካቶች በእስር ላይ ሕይወታቸው አልፏል። ለኦሮሞ ወጣቶች መታሰር፣ መሰቃየት፣ መገደል እነ አዲሱ ታዛዥ ሆነው አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ፣ እነ እስክንድር ደግሞ አደባባይ እንዲወጡ ተምሳሌት ሆኑ። በፅናታቸው ወጣቱን ከፍርሃት ነፃ አወጡት። እነ አዲሱ ከስር ሆነው ይደግፉት ከነበረው የድንቁርና ስርዓት ነፃ እንዲወጣ አደረጉት። እነ አዲሱ በሕወሓት ዘመን በእስክንድር ፅናት ሲበሳጩ ሆነዋል። ዛሬም እየተበሳጩ ነው። የሁለት ዓለም ሰዎች ናቸውና። እስክንድር ነጋ ከእስር ቤት ፌስታሉን ይዞ ከመውጣቱ በፊት ውጭ የታሰረውን ወጣትም አንቅቶ፣ ተምሳሌት ሆኖ ነው። ይህን ሲሰራ ሕሊናውን ነፃ አድርጎ ነው። በተቃራኒው እነ አዲሱ እነ እስክንድር ተምሳሌት የሆኑትን ሁሉ እያፈኑና እያሳፈኑ፣ ከእስር ቤት ውጭ ሆነው ሕሊናቸውን አስረው የሕወሓት የድንቁርና ፌስታል ተሸካሚዎች ነበሩ።

የእነ እስክንድር ተምሳሌት ብዙዎችን ነፃ አውጥቷል። ከእነሱ መፈታት በላይ ትውልዱ አደባባይ ወጥቶ መብቱን እንዲጠይቅ አድርጓል። እንደ እነ አዲሱ ያለው የትህነግ/ህወሓት ተላላኪ ከአዛዦቹ ነፃ እንዲወጡ አድርገዋል። የእነ እስክንድር ነጋ ትግል ባርያን ከአሳዳሪው ነፃ ያወጣ ትልቅ ትግል ነው። ሆኖም ላለፈው ገዥ ፌስታል ተሸካሚ ሆኖ ሲገዛ የኖረ ካድሬ ዛሬ ከአሳዳሪው መከራ ሲላቀቅ ውለታ አጣ። እስር ቤት ውስጥ ሆነው በዓለም ተምሳሌትነታቸውን አስመስክረው፣ ለትውልዱ የነፃነት አርዓያ ሆነው የወጡትን ለመዝለፍ በቁ። እነ እስክንድር ለነፃነት በለፉበት ወቅት የሕወሓት ፔስታል ያዦች ሕዝብን ዘርፈው ሀብት በሀብት ሲሆኑ እነ እስክንድር ለነፃነት ብቻ ለፍተው በመውጣታቸው ፌስታል ይዘው መውጣታቸው እንደ ስድብ ሆነ! እነ እስክንድር እንደ ሕወሓት ፌስታል ተሸካሚዎች ሕንፃና መሬት ሲያልሙ አልነበረም። እነ አዲሱ የሕወሓትን ፌስታል ተሸክመው መሬትና ሕንፃ ይኖራቸዋል። የድንቁርናው ስርዓት ያወረሳቸው ይህን ነው።

ጌታቸው ሽፈራው

Share.

About Author

Leave A Reply