የእብድ ውሻ በሽታ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የእብድ ውሻ በሽታ በበሽታው በተለከፉ እንስሳት ንክሻ ማለትም በውሻ፣ በድመት፣ በቀበሮ፣ በተኩላና በሌሎችም ሊሆን ይችላል ወደ ጤናማ ሰው ሊያስተላልፍ የሚችል አደገኛ በሽታ ነው፡፡ የእብድ ውሻ በሽታ በለሊት ወፍ አማካኝነትም ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ይህ በሽታ የሚከሰተው በቫይረስ አማካኝነት ሲሆን ከፍተኛ የአንጎል መጉረብረብን በሰዎች እና በሌሎች ደመ-ሞቃት እንስሳት ላይ ማስከተል የሚችል ነው። በዚህ በሽታ የተያዘ እንስሳ የተለየ ጠባይ ማሳየት ይጀምራል፤ በተለይ መቅበጥበጥና መበሳጨት ያሳያል፤ አረፋ ይደፍቃል፣ መብላት ወይም መጠጣት አይችልም፣ አንዳንድ ጊዜ ያለምክንያት በመበርገግ ያገኘውን ሰው ወይም እንስሳ ይነክሳል፤ እንዲሁም የለሃጭ መዝረብረብ ያሳያል፡፡
የቅድሚያ ምልክቶቹ ትኩሳት እና በተነከሱበት ቦታ ማሳከክ ወይም ማቃጠልን ያካትታል። እነዚህ ምልክቶች ከሚከተሉት አንድ ወይም የበለጡ ምልክቶችን አስከትለው ይመጣሉ፤ ኃይል የታከለባቸው የሰውነት እንቅስቃሴዎች፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ መሸበር፣ የውኃ ፍራቻ፣ የሰውነት ክፍልን ለማንቀሳቀስ መቸገር፣ ግራ መጋባትና ህሊናን መሳት ሊሆኑ ይችላሉ። ምልክቶቹ ከታዩ በኋላ፣ የእብድ ውሻ በሽታ በአብላጫው ሞትን ያስከትላል። በበሽታው የተያዘ እንስሳ ከ5-7 ባለው ቀናት ውስጥ ሊሞት የሚችልበት ሁኔታም ሊያጋጥም ይችላል፤ በሰዎች ላይ የሚታየው ምልክት ግለሰቡ ንቁ ቢሆንም ቁጡ ይሆናል፣ ወፈፍ ያደርገዋል፣ የብርሃን ጥላቻም ስለሚያድርበት ጨለማን ይመርጣል፣ ፀጥ ብሎ በሰላም ከቆየ በኋላ በድንገት የመበርገግ ጠባይ ይታይበታል፤ በመጨረሻም አቅሉን ስቶ አረፋ እየደፈቀ ሰውነቱ ሽባ ሆኖ ይሞታል፡፡
በበሽታው ለመያዝ ምልክቶቹ መታየት የሚጀምሩበት የጊዜ ገደብ ከአንድ እስከ ሦሥት ወራት ባሉት ጊዜ ውስጥም ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን፣ ይህ የጊዜ ገደብ ከሳምንት ባነሰ እና ከአመት በበለጠ ጊዜ ሊለያይ ይችላል። የጊዜ ገደቡ የሚወሰነው የበሽታ አምጭው ረቂቅ ህዋስ ወደ ማዕከላዊ የነርብ ስርዓት ለመድረስ የሚፈጅበት እርቀት ነው።የእብድ ውሻ በሽታ ረቂቅ ህዋስ ወደ አንጎል የሚጓዘው ዘርፋዊ ስርዓተ ነርቭን ወይም ፐሪፈሪያል ነርቭስ በመከተል ነው። በሽታው ሊታወቅ የሚችለው ምልክቶቹ ከጀመሩ በኋላ ነው። የእብድ ውሻ በሽታ ወደ ሰዎች የሚተላለፈው በአበደ ውሻ ንክሻ ወይም በሌሎች በተለከፉ እንስሳት እንደመሆኑ መጠን በበሽታው የተበከለ እንስሳ ሌላ እንስሳ ወይም ሰው ሲቧጭር ወይም ሲናከስ የእብድ ውሻ በሽታ ሊያስተላለፍ ይችላል። የተበከለ እንስሳ ምራቅ ከሌላ እንስሳ ወይም ሰው የሰውነት ፈሳሽ አመንጭ ህዋስ ያሉበት ማስተላለፊያ ጋር ከተነካካ የእብድ ውሻ በሽታ ሊተላለፍ ይችላል። አብዛኛዎቹ በሰዎች ላይ የተከሰቱ የእብድ ውሻ በሽታዎች መንስያቸው የውሻ ንክሻ ነው።
የተወሰኑ የዓለም ክፍሎች የሚያደርጉት የእንስሳት ቁጥጥርና ክትባት መርሃግብሮች በውሻ የሚመጣ የእብድ ውሻ በሽታን ተጋላጭነት በእጅጉ ቀንሰዋል። ከፍተኛ ተጋለጭነት ላለባቸው ሰዎች ለበሽታው ከመጋለጣቸው በፊት አስቀድሞ የመከላከያ ክትባትን መስጠት ይቻላል፤ ይመከራልም።

ከፍተኛ-ተጋላጭነት ያላቸው የእብድ ውሻ በሽታ በአብዛኛው የሚከሰትበት አካባቢ የሚሰሩ ሰዎች ናቸው። በእብድ ውሻ በሽታ ለተጠቃ ሰው፣ የእብድ ውሻ በሽታ ክትባት እና አንዳንድ ጊዜም የእብድ ውሻ በሽታ ኢሚዩኖግሎቢን ታካሚው የእብድ ውሻ በሽታ ምልክቶች ማሳየት ከመጀመሩ በፊት ህክምናውን ከአገኘ በሽታውን ሊከላከል ይችላል።
በአበደ ውሻ ወይም ሌላ ማንኛውም እንስሳ የተነከሰውን ወይም የተቧጨረውን ቦታ ለ15 ደቂቃ በውኃ እና በሳሙና ማጠብ፣ በአዮዲን ወይም በሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሾች ማጠብ ቫይረሱን ሊያስወግድ ስለሚችል፤ እንዲሁም የእብድ ውሻ በሽታ መተላለፍን ሊከላከል ስለሚችል በተገቢው ፍጥነትና ሁኔታ መተግበር አለበት። በተጨማሪም በሽታውን ለመከላከል ውሾችን በየጊዜው ማስከተብ፣ ከተነከስን ደግሞ በጤና ማዕከላት የሚሰጠውን ክትባትና ተያያዥ ሕክምና በጊዜ መውሰድ አለብን፡፡ የማንኛውንም የእብድ ውሻ በሽታ ሊያስተላልፉ የሚችሉ እንስሳትን ንክሻ ማወቅ ስለማይቻል፣ ንክሻው ካጋጠመን ሳናቅማማ ክትባቱን መውሰድ የሚመከር ነው፡፡

survival101

Share.

About Author

Leave A Reply