የኦሮሞና የአማራ አክቲቪስቶች ህዝብን ከህዝብ የሚለያይ ሀሳብ ከሚያራምዱ ይልቅ ህዝብን የሚያስተሳስር ጉዳይ ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። – አቶ አዲሱ አረጋ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ እየተራመደ ያለዉ የሀሳብ ልዩነት በሰለጠነ እና ጨዋነት በተሞላዉ መልኩ ከመሄድ ይልቅ ወደ መዘላለፍ እና መካረር እያመራ ነው። ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገዉ ደግሞ እየተራመደ ያለዉ ልዩነት አመክንዮን ያማከለና የሰከነ ክርክር አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የብሄር አሰላለፍን እያየዘ መምጣቱ ነዉ። በተለይ የአማራ እና የኦሮሞ አክቲቪስቶች የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ለዘመናት የኖረዉን አብሮነት እና አንድነት ማጎልበት፥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር እና አሁን የደረስንበትን አዲስ የለዉጥ ምዕራፍ ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የሚያስችሉ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ መወያየት እና መከራከር ሲገባቸዉ፣ በህዝቦች መካከል ልዩነቶችን የሚያሰፉ፣ ለግጭት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ፣ የህዝቦችን መተማመን የሚሸረሽሩ፥ አንድነታችንን ሊጎዱ የሚችሉ ትንንሽ የልዩነት ጉዳዮችን በማጉላት ላይ እየተጠመዱ ይገኛሉ። እንደዚህ አይነት ገንቢ ያልሆነ ንትርክ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አሁን የደረስንበትን የለዉጥ ምዕራፍ ወደሗላ እንደሚጎትት መታወቅ አለበት።

ይህን የማህበራዊ ሚዲያ ፍትጊያ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኦሮሞ እና በአማራ ህዝቦች አንድነት ላይ ስንጥቅ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ወገኖች እንዳሉም ታዝበናል። በርግጥ የሁለቱ ህዝቦች አንድነት እና ወንድማማችነት በማበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ በሚፈጥረዉ አሉታዊ ስሜት የሚናድ ሳይሆን ለዘመናት በፅኑ መሰረት ላይ የቆመ ጥልቅ አንድነት ነው። ችግሮች ሲፍጠሩም ሆን ልዩነቶች ሲኖሩ በዉይይት እየታረሙ መጥተዋል። ወደፊትም በዉይይት የሚታረሙ ይሆናሉ።

ስለሆነም ትንንሽ የልዩነት ሀሳቦችን አጉልተን ከመጨቃጨቅ ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ትልልቅ ሀሳቦች ላይ ማትኮር፣ ጥርጣሬን የሚያሰፉ ጉዳዮችን ከማጉላት ይልቅ መተማመንን ለማጎልበት፣ ጥላቻ፣ መራራቅ እና ለግጭትን የሚጋብዙ ሃሳቦችን ከማራመድ ይልቅ ፍቅር፥ መቀራረብ እና ሰላምን ለማረጋገጥ መስራት ለሁላችንም ይጠቅማል።

ቸር እንሰንብት!

 

Share.

About Author

Leave A Reply