የኦሮሞ ህዝብ በአስቸኳይ መታጠቅ አለበት ~ ኦነግ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

«የኦሮሞ ህዝብ ራሱን ከጥቃቶች ለመከላከል መታጠቅ እንዳለበት» ኦነግ እንደ ድርጅት እንደሚያምንበት የግንባሩ ቃል አቃባይ አቶ ቶሌራ አደባ ዛሬ ለDW ገለጹ። የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በበኩላቸው «መንግስት የማህበረሰቡን ሰላም ያስጠብቃል፣ ሁለት የታጠቁ አካላት በአንድ ክልል ብሎም አገር ዉስጥ መንቀሳቀስ የለባቸዉም፤ ኦነግ ትጥቁን መፍታት አለበት» የሚል አቋም ማንጸባረቃቸውን ቀጥለዋል።

እንደ አቶ ቶሌራ አባባል «ህዝብ የኦነግ ሰራዊት ትጥቅ ይፈታል ሲባል ፍራቸዉን ስገልፅ ነበር። ይህም ፍራቻ የመነጨዉ ከባለፉት አመታት ትዉስታ እና አሁን መሬት ላይ ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርጎ ነዉ» ብለዋል። «በኦሮሚያ ክልል አጎራባች አከባቢዎች ያሉት ህዝቦች ሁሉ የታጠቁ» እንደሆኑ የጠቀሱት የኦነግ ቃል አቃባይ «የኦሮሞ ህዝብ ባለመታጠቁ ጥቃቶች እየደረሰበት ይገኛል» ሲሉ ወንጅለዋል። «የኦሮሞ ህዝብ በልዩ ልዩ አቅጣጫዎች እየተጠቃ ስለሆነ ያለዉ መንግስትም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አይቶ ራሱን የሚከላከልበትን መንገድ ያፈላልጋል» የሚል ተስፋ እንዳላቸዉም ገልጸዋል።

አቶ ቶሌራ ይህን የድርጅታቸዉን አቋም የገለፁት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ አስተዳደራቸዉ «አንድም ቀን የኦሮሞ ህዝብ ትጥቁን ይፍታ ብለዉ እንደማያዉቁ፤ እንዲፈቱም እንደማይፈልግ» በትላንትው ዕለት መግለጻቸውን ተከተሎ ነው። አቶ ለማ የክልሉ አስተዳደር «ትጥቅ የማስፈታት አጀንዳም እንደሌለዉ» ትላንት ከአባገዳዎች እና ከህዝብ ተወካዮች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ባደረጉት ውይይት ወቅት ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ እና በአገሪቱ ዉስጥ ባለዉ የፀጥታ ችግር ላይ ድርጅታቸዉም ሆነ ኦነግ ሊወያይበት እንደሚገባ በዉይይቱ ላይ ለታደሙት ሰዎች አስረድተዋል።

ኦነግ በአላማ ደረጃ በሰላማዊ ትግል ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የትጥቅ ትግል አቁሞ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ቶሌራ «የኦነግ ወታደሮች እንዴት በሰራዊቱ፣ በፖሊስ እንዲሁም በሲቪል አስተዳደር ዉስጥ እንደሚታቀፉ ከመንግስት ጋር ተወያይተን የምንፈታው ይሆናል» ብለዋል። «አሁን ትጥቅ ይፈታሉ፣ አይፈቱም የሚለው ለምን የመከራከርያ ነጥብ እንደሚሆን አይገባንም» ያሉት አቶ ቶሌራ ነገር ግን በድርጅታቸዉ ስም ሰላምን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ካሉ እነሱን እንደሚታገሉ ገልፀዋል።

Share.

About Author

Leave A Reply