የኦነግን ነገር በእርቅ ሰበብ አለባብሶ ማለፍ ወንጀልን እንዳያበረታታ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

(ኤልሳ ዘብሄረ ጦቢያ)

የባንክ ተጫዋቾች አሰልጣኝ ጫማዬን ልሰቅልነው አለ ሲሉ ሰማሁ ልበል፡፡ ጎሽ ደስ የሚል ዜና ነው፡፡ እርቅ ደስ ይላል፡፡ የሚያስታርቁም ብጿን ናቸው እንዲል ቃሉ እርቅን ላወረዱ ሁሉ ደግ አረጋችሁ፤ አበጃችሁ፤ ያኑርልንም ብለናል፡፡

እሺ ከዚያስ በኋላ ምን እንጠብቅ? ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ መቼም ሰውየውና ቡድኑ ከአምባ ገነኖች ጋር ግንባር ለግንባር ገጥሞና ተዋግቶ ለቶክስ አቁም ድርድር እንዳልተቀመጠ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ያው ሃገር ነፃ ወጥታ በክብር ተጋባዥነት ተጠርቶ ገብቶ ነው በሰላም ሃገር ያን ሁሉ ህፃን አዋቂ፤ ሴት ወንድ አዛውንት ሳይል ሲያስጨፈጭፍና ፀያፍ ወንጀል ሲያስፈፅም የቆየው፡፡

ከዚያም አልፎ ተርፎ ከህወሃት የተረፈችውን ሙጣጭ ሳንቲም ከየባንኮቹ በመዝረፍ እልም ያለ አሳፋሪ የስርቆት ስራ ላይ ተሰማርቶ ክፋቱን አሳይቷል፡፡ የህዝብና የመንግስት ሃብትና ንብረትን በማውደም ፍፁም ህዝብና ሰላም ጠል መሆኑን በግብሩ እረጋግጧል፡፡ ታድያ እኔን ያልገባኝ ወንጀል የሰራ በህግ ይጠየቃል እንጂ እንዴት ነው አፉ ብለናል ብሎ ጭራሽ ምንም እንዳልተደረገ አስመስሎ አምታቶ ማለፍ?

በህግ የሚጣል ቅጣት እኮ አስተማሪነቱ ወንጀሉን ለፈፀመ ሰው ብቻም ሳይሆን ለሌላው ዜጋም ጭምር ነው፡፡ ታድያ በዚህ ጉዳይ ህዝብና ትውልድን ካላስተማርንበት በምን ልናስተምርበት ይቻል ይሆን ከቶ፡፡ ይህን አይነቱን ነገር አለባብሶና በእርቅ ሰበብ አልፎስ እንዴት ያለ የሰላም ዋስትናን ማምጣት ይቻል ይሆን?

ይህ ሁሉ የሚያሳየው ሃገሪቷ በህግ የሚመራ ተቋም አልባ መሆኗ ነው፡፡ እናማ እንደህዝብና እንደሃገር ለመቀጠል ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን የማቋቋሙ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ግድ ነው ፡፡ አልያ ትንሽ ቆይቶ የባንኮች ክለብ እንደአይሲስ የአንገት መቅላት ክለብ ሆኖ ላለመከሰቱ ዛሬም ዋስትና የለም፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply