የኦዲፒ ኢትዮጵያ (አንሙት አብረሀም)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በነ ዐቢይ አህመድ እና ለማ መገርሳ የሚመራው ODP የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣንን እንደሚፈልገው በይፋም በህቡዕም ያደረገው ትግል ተሳክቶ ይዘውት አንድ አመት ሞላ፡፡

የነበረውን ፍላጎት በቀና ልቦና ላየው በኃይለማርያም ደሳለኝ አመራር ወቅት የገጠሙ ችግሮችን እና ሌሎች አገራዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት ከነበር ምንም ችግር አልነበረውም፡፡ ያለፈው አንድ አመት ይህንን ያሳዬ ነበር ወይ? የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡

አመራሩ አመቱን የኢትዮጵያ ምርጡ አመት ቢያስመስለውም፡ በእኔ ግምገማ ግን የነባር ቅራኔዎች እድሳትና ነባር አገራዊ ቅራኔዎችን ስፋትና ጥልቀት የሚሠጡ አዳዲስ ቅራኔዎች ተፈጥረዋል፡፡

1) ቀዳሚው በገዢው ግንባር አባላት መካከል የኖረው ቅራኔ ከመጥበብ ይልቅ ይበልጥ ሰፍቶ በጋራ የአስተሳሰብ መርህ እና ርዕዮተ-ዓለም የመመራት ጉዳይ ለስሙም ጠፍቷል፡፡ በጋራ መክሮ አገር መምራት እና መወሰን ቀርቶ ጥቂት ቡድን ወይም ግለሠብ የፈለጉትን የሚያደርጉበት እንጂ የአገሪቱ ገዢ ግንባር አይመስሉም፡፡ በህወሓት እና ሶዴፓ መካከል ልዩነት የለም፡፡ ደብረፅዮን እንዳለውም “ከህዝብ እኩል ውሳኔ እየሠሙ ነው፡፡ የአካሄድ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ልዩነት መስራች አባላቱን ለያይቷል፡፡ የይስሙላ አብሮነት እንጂ የፖለቲካ ሰልፍ ግንባርነት ሞቷል፡፡ እንዲያውም በአንድ ገዢ ፓርቲ ውስጥ የተፈፀመ የአመራር ለውጥ ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ያህል ሆኖ እየቀረበ ነው፡፡ ተቋማዊ ስርዓት ባልፈጠረ አገር አገራዊ አንድነትና መግባባት በሌለው አገር ከጭንቅ መውጫ የአስተሳሰብ መስመር እና ፖሊሲ ትርፍ ነገር ሆኗል፡፡ እናም ተሰባስበን እንጨፍለቅ እየተባለ ነው፡፡ እየተለያዩ መጣመር የድርጅት ቁጥር ቅነሳ ግብ ብቻ ያለው፡ የመለያየት ዋዜማ ብቻ ሳይሆን የፈላጭ ቆራጭነት ጥማት ነው፡፡

2) ክልሎች ፡- በክልሎች ዘንድ ያለፈው አመት ቅራኔዎች ተባብሰው የታዩበት ነው፡፡ አገራዊ አንድነት ከባድ አደጋ ተደቅኖበት ሁሉም በውስጡ plan B የሚያሰላስበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡

ሶማሌ፡ ከወቅቱ አመራር ጋር ቀደም ብሎ የገባው ቅራኔ ባይታወር አርጎታል፡፡ በተቆጠበ አገላለፅ፡ አመቺ ሁኔታን የማግኘት ጉዳይ እንጂ ተጠቃን የሚለው የስነልቦና ስሜት የአብሮነት አይደለም፡፡

ደቡብ በbalkanization ፈተና፡ በእርስ በርስ ግጭት፡ በመፈናቀል ሂደት ፡ ወዘተ ይፋ ባልሆነ ወታደራዊ ቁጥጥር እንዲሠነብት የተወሠነበት ለመጭው ጊዜ ቅራኔን ያረገዘ ክልል ነው፡፡በሙፈሪያት ካሚል የሚመራውን ድርጅት seriously የሚመለከተው እምብዛም ነው (ማን ያውቃል፡ ቀን ሲያልፍ ደግሞ ”ድርጅታዊ ነፃነታችንን ጠብቀን ነው የኖርነው፡ ማንም የማንም ተለጣፊና ተላላኪ አይደለም” ሲባል እንሰማለን፡፡)

ሐረሪ፡ ተመልካች ያጣ ፡ መንግስት አልባ ባድማ ነው፡፡ ለአመራሩ ዐይን የማይሞላ ባለታሪክ ምድር ነው፡፡ በሐረሪና በሞቃዲሾ መካከል ያለው ልዩነት ምን እንደሆነ እንጃ፡፡ አሁን እንደ ደቡብ ክልል በፌዴራል የፀጥታ ኃይል ስር ያለ ነው፡፡ ቤቱ በወጣቶች ተሠብሮ ለግድያ የተፈለገው አመራር ክልሉን ለቆ ወጥቷል፡፡

ትግራይ ፡ እንዲያው ለነገሩ ነው የአገረ መንግስቱ አካል የሚመስለው፡፡ የኢትዮጵያ ነገር፡ የ4ኪሎ ውሳኔ ምናቸውም አይመስል፡፡ የአዲሱ አመራር ጋር ያለው ባይታወርነት ሰፊ ነው፡፡ ከሆነ ይሆናል፡ ሲቀር ይቀራል፡ የቤት ስራችን ላይ እናተኩር ብለዋል፡፡ ሁሉም ደመኛ ያረገን፡ ወርቃማ አገራዊ ውጤታችን ትቢያ ተጣለበት የሚል ጥልቅ ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል፡፡

ኦሮሚያ ፡ ውስጡ ጉዳንጉድ ነው፡፡ የODP መዋቅር የፈረሰባቸው እና የአካባቢ ‘ጎበዝ አለቃ’ የያዛቸው መኖራቸው በስፋት ይገኛል፡፡ እኔ በማውቀው ሐረርጌ የመንግስት ተግባር አለ ማለት ይከብዳል፡፡ ልክ በአንዳንዶቹ ክልሎች እንዳለው የመንግስት የኃይል ቁጥጥር መጥፋት በኦሮሚያ ይብሳል፡፡ ኦነግም ክልሉን ለመረከብ ምርጫን እየጠበቀ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ODP በበኩሉ ፌደራል መንግስቱን እና አዲስአበባን ይዞ “ሌሎችን” በመከላከል መቀጠል የፈለገ ይመስላል፡፡

አማራውም አፋሩም ቤጉ ሁሉም የሚነገርላቸው አዳዲስ ቅራኔ ሞልቷቸዋል፡፡

3) ኢኮኖሚው፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና እንደዚህ ወቅት ተመልካች ያጣበት ዘመን የለም፡፡ እውነት ለመናገር አመራሩ እና ገጠሩ ተለያይተዋል፡፡ “ቤተመንግስቱ ጥሩ ገፅታ ሲይዝ አዲስአበባ ይቀየራል ÷ አዲስአበባ ሲቀየር ኢትዮጵያ ትቀየራለች” ሲባል ነው ተስፋ የቆረጥኩት፡፡ stractural falacy at its best form ! ስለ አገሪቱ ወጭ ንግድ ከተመከረ ስንት ጊዜው፡፡ GTP የሚባል የተስፋ ዳቦ በተደፋበት እያረረ ይመስላል፡፡ በሚቀጥለው አመት 17ሺህ ሜዋ ተብለን አሁን 4,200 ሜዋ ላይ ነን፡፡ 10 ስኳር ፡ አስር ማዳበሪያ ፋብሪከዎች፡ 5ሺህ ኪሜ ባቡር..ሁሉም ዝምታ ውጧቸዋል፡፡ አሁን ትልቁ ልማት የወንዝ ዳርቻ ነው፡፡ ጎዳና የወጣው ወጣት ጥያቄ ‘በለምለም ምላስ’ የሚለዝብ አይመስለኝም፡፡ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ይሸተኛል፡፡

4) ጎረቤት አገራት፡ የኤርትራ ነገር አወንታዊ ቢመስልም፡ መሬት ቆንጥጦ የመቀጠል ጣጣ አለበት፡፡ ምክንያቱም ከፋፋይ ስምምነት ነው፡፡ ኦሮሚያን ወይም አማራን እንጂ አጎራባች ትግራይን እና አፋርን ማቀፍ የመሪዎች ፍላጎት አይመስልም፡፡ ከጎረቤቶች በተለይ ጅቡቲና ሱማሊ ላንድ በፅኑ የተከፉ ናቸው፡፡ ብዙ ውስጣዊ ቅራኔዎች ተፈጥረዋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply