የካናዳና የሳዑዲ አረቢያ ፍጥጫ Featured

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሰሜን አሜሪካዊቷ ካናዳ እና የባህረ ሰላጤዋ ሳዑዲ አረቢያ ሰሞኑን የገቡበት ፖለቲካዊ ፍጥጫ ሰላም ለራቃት ዓለም ተጨማሪ ስጋት እንዳይሆን ተሰግቷል፡፡ የካናዳ ባለሥልጣናት ሳዑዲ አረቢያ ያሰረቻቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንድትፈታ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ ‹‹ካናዳ በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው›› በማለት በሪያድ የሚገኙትን የካናዳ አምባሳደር አባርራለች፤ በኦታዋ የሚገኙትን አምባሳደሯንም በፍጥነት ወደ ሳዑዲ እንዲመለሱ ትዕዛዝ ስታስተላልፍ የአገራቱ ግንኙነት እንዲህ በፍጥነት ይቀያየራል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡

ከዚያም በተለይ የሳዑዲ አረቢያ አየር መንገድ ወደ ቶሮንቶ የሚያደርጋቸውን ቀጥታ በረራዎች ሲሰርዝና የአገሪቱ መንግሥትም ከካናዳ ጋር ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንደሚያቋርጥ ሲያሳውቅ ነገሮች ሁሉ ባልታሰበ ፍጥነት መቀያየር ጀመሩ፡፡ ቆየት ብሎም ሳዑዲ አረቢያ ካናዳ ውስጥ በትምህርት ላይ የሚገኙ ዜጎቿ ወደሌሎች አገራት ተዛውረው እንዲማሩ ለማድረግ የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ አድርጋለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ካናዳ ውስጥ በሕክምና ላይ የሚገኙ የሳዑዲ አረቢያ ዜጎች ከካናዳ ሆስፒታሎች እንዲወጡና ሌሎች ሆስፒታሎች ውስጥ እንዲታከሙ ትዕዛዝ አስተላልፋለች፡፡

ታዲያ ይህ ሁሉ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የታሰሩትን የሴት መብት ተሟጋቾችን አስመልክቶ ከካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተላፈው መልዕክት ነው፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከል አንዷ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ጭቆና በመቃወም የሚታወቁትና ለበርካታ ዓመታት የታሰሩት የዓለም አቀፍ ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ወይዘሮ ሰመር በዳዊ ናቸው፡፡ ራይፍ በዳዊ የተባሉት የወይዘሮ ሰመር በዳዊ ወንድም ደግሞ ከአራት ዓመታት በፊት የ10 ዓመታ እስራት የተፈረደባቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ የካናዳ ዜግነት ያላቸው ግለሰብ ናቸው፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ወይዘሮዋን ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ለእስር ከዳረጋቸው በኋላ የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ አረቢያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ያወጣው መግለጫ የባህረ ሰላጤዋን ኃያል አገር አስቆጥቷል፡፡

የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቲያ ፍሪላንድ ‹‹ካናዳ በግዛቷ ብሎም በዓለም ዙሪያ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ፍላጎቷ ነው፤ ድጋፍም ትሰጣለች፡፡ የሴቶች መብቶች ከሰብዓዊ መብቶች መካከል ስለሚመደቡ መብቶቹ እንዲከበሩ ለማድረግ ትጥራለች›› ብለዋል፡፡

የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለካናዳ አቻው መግለጫ በሰጠው ምላሽ የካናዳ ድርጊት የሳዑዲ አረቢያን ሉዓላዊነት የጣሰ ተግባር እንደሆነ ገልፆ መግለጫውን ክፉኛ ኮንኖታል፡፡ ‹‹ሳዑዲ አረቢያ በታሪኳ ሉዓላዊነቷን ለተዳፈሩ አካላት ትዕግሥት የላትም፡፡ ካናዳ በእኛ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ሞክራለች ማለት እኛም በካናዳ ጉዳይ ጣልቃ እንገባለን እንደማለት ነው፡፡ የካናዳ መንግሥት ተግባር ከሁለቱ አገራት ግንኙነት ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ነው›› ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ሳዑዲ አረቢ ከአቋሟ ፍንክች ማለት የፈለገች አትመስልም፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አደል አል-ጁቤይር፣ አገራቸው ከካናዳ ጋር የሚያደራድራት ሦስተኛ ወገን እንደማትፈልግ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምንም የምንደራደረው ነገር የለም፡፡ ካናዳ ከባድ ስህተት ሠርታለች፡፡ ጉዳዩ የሰብዓዊ መብት ሳይሆን የብሔራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዝርዝር ባይገልጹትም ሳዑዲ አረቢያ በካናዳ ላይ ተጨማሪ ዕርምጃዎችን እንደምትወስድም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ እስረኞቹ በውጭ አገራት ከሚገኙ አካላት ጋር ግንኙነት እንደነበራቸውም ተናግረዋል፡፡

ታዲያ ሳዑዲ አረቢያ እየወሰደቻቸው የሚገኙት ዕርምጃዎች በሳዑዲ አረቢያ ዜጎች ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ማሰብ የፈለገች አትመስልም እየተባለች እየተወቀሰችም ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ ካናዳ ውስጥ በትምህርት ላይ የሚገኙ ዜጎቿ ወደሌሎች አገራት ተዛውረው እንዲማሩ ለማድረግ የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ ማድረጓና ካናዳ ውስጥ በሕክምና ላይ የሚገኙ የሳዑዲ አረቢያ ዜጎች ከካናዳ ሆስፒታሎች እንዲወጡና ሌሎች ሆስፒታሎች ውስጥ እንዲታከሙ ትዕዛዝ ማስተላለፏ በሳዑዲ አረቢያ ዜጎች ላይ ከባድ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

የሪያድም የኦቶዋም አጋር የሆነችው ዋሽንግተን በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ ቃል አቀባይ በኩል ‹‹ሁለቱም ወገኖች ችግሩን በውይይት መፍታት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያን ደግሞ እኛ ልናደርግላቸው አንችልም›› በማለት አጋሮቿ ውዝግቡን እንዲያበርዱ ጠይቃለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቃል አቀባይዋ ሂዘር ኖሬት፣ ‹‹አሜሪካ ለዓለም አቀፍ መብቶችና ነፃነቶች እንዲሁም ለግላዊ መብቶች መከበር ያላት አቋም የማይቀየር ነው›› በማለት አንዳንዶች የሳዑዲን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሌሎች ደግሞ የካናዳን ጣልቃ ገብነት ሸንቆጥ ያደረገ ነው ብለው የተወዛገቡበትን ንግግር ተናግረዋል፡፡

የአልጀዚራዋ ዘጋቢ ኪርስተን ሳሎሚ ከቶሮንቶ ባሰራጨችው ዘገባ፣ የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየሰጣቸው የሚገኙት መግለጫዎች የባህረ ሰላጤዋ አገር ውዝግቡ እንዲበርድ ፍላጎት እያሳየች እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡ ‹‹የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዴል አል-ጁቤይር ‹ካናዳ ስህተት ሠርታለች› ከማለት በተጨማሪ ካናዳ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ውዝግብ ለማብረድ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ብሪታኒያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እንዲያደራድሯት ለማድረግ እየጣረች እንደሆነ የሚገልጽ መረጃ ሰጥተዋል›› በማለት ዘግባለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን የድርድሩን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡

ሳዑዲ አረቢያ ይህን ሁሉ የዕርምጃና የዛቻ ናዳ ስታወርድ ካናዳ የአፀፋ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥባለች፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ከካናዳ አቻቸው ጋር ውይይቶችን ማድረጋቸውንና ውይይቶቹም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የሚያደርጉትን ውይይት በሰከነ መንገድ እንደሚፈፅሙትና በሰብዓዊ መብቶች ላይ ያላቸው የጸና አቋም ግን እንደማይቀየር ሞንትርያል ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ካናዳ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጦር መሳሪያ ሽያጭ ለሳዑዲ አረቢያ ለማቅረብ ከአገሪቱ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት አለ፡፡ ይህ ስምምነት የሚሰረዝ ከሆነ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ በካናዳ የሚገኙ ሰዎች ሥራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

ይሁን እንጂ የአገራቱ ውዝግብ መነሻ በሳዑዲ መንግሥት የታሰሩት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ናቸው ቢባልም ሳዑዲ አረቢያ ካናዳን መልዕክት ማስተላለፊያ ለማድረግ እንደተጠቀመችባት ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በዴንቨር ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ናደር ሃሸሚ፣ ‹‹ሳዑዲ አረቢያ በተለይም አልጋ ወራሹ መሐመድ ቢን ሰልማን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ አገራት ስለ ሳዑዲ አረቢያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ትንፍሽ ማለት እንደማይችሉ መልዕክት ያስተላለፉበት አጋጣሚ ነው›› ይላሉ፡፡

ከዚህ ባሻገርም፣ የችግሩ ምንጭ ወጣቱ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን አገራቸው ሳዑዲ አረቢያ ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚመሩበት መንገድ እንደሆነ ሃሸሚ ይገልጻሉ፡፡

በኦቶዋ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ተመራማሪ ቶማስ ጁኒዮ በበኩላቸው የሳዑዲ አረቢያና የካናዳ ፖለቲካዊ ውዝግብ በቅርብ ጊዜ የተጀመረ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰጠው የሰሞኑ መግለጫም ካናዳ በሳዑዲ አረቢያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የነበራት የረጅም ጊዜ ቅሬታ ውጤት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

የካናዳ የውጭ ጊዳይ ሚኒስትር ክርስቲያ ፍሪላንድ አገራቸው ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ያላት አቋም በምንም መልኩ እንደማይቀየር በተደጋጋሚ መናገራቸውና የሳዑዲ አቻቻው ደግሞ የካናዳን መግለጫዎች ማጣጣላቸውና መኮነናቸው በወጣት መሪዎች የሚመሩትን የሰሜን አሜሪካዊቷን ካናዳንና የባህረ ሰላጤዋን ሳዑዲ አረቢያን ፍጥጫ እንዳያራዝመው ተሰግቷል፡፡

 

አንተነህ ቸሬ

Share.

About Author

Leave A Reply