የወለጋ መንገድ በኦነግ ኃይሎች ተዘግቶ ዋለ – አቶ ለማ መገርሳ ማስጠንቀቂያ ሰጡ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

(ዘ-ሐበሻ) ባለፉት ሁለት ቀናት የመከላከያ ሰራዊት በምዕራብ ኦሮሚያ በሚንቀሳቀሱ የኦነግ ታጣቂዎች ላይ የከፈተውን ዘመቻ የተቃወሙ ጥቂት የአካባቢው ነዋሪዎች ዘግተው ውለዋል:: በም ዕራብ ኦሮሚያ በተከሰተው ውጥረት ዙሪያ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ማሳሰቢያ ሰጡ::

በተለይ የለማ መገርሳ አስተዳደር በቅርቡ ለቀድሞው የኦነግ አባላት ለጀነራል ከማል ገልቹ ስልጣን ከሰጠ ብኋ;አ በመንግስት እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ መካከል የነበረው የቃላት ጦርነት አሁን ወደ ለየለት ውጊያ እንደተሸጋገረ መሆኑ እየታየ ነው:: ዕራባዊ ኦሮሚያ ክልል በሚገኙት አከባቢዎች የኦሮሞ ነፃ አዉጭ ግንባር /ኦነግ/ ስራዊት ናቸዉ በተባሉና በኢትዮጵያ መከላክያ ሰራዊት መካከል ላለፉት ቀናቶች ግጭት ተቀስቅሷል። በሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለልቻ በሚመራው የሃገር መከላከያ ሰራዊትና በዳውድ ኢብሳ በሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወታደሮች መካከል ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ ፤ አቶ ለማ መገርሳ “ሁኔታዉ በጣም እንዳሳዘናቸዉ ገልፀዋል። ወጣቶች መሳርያ በመታጠቅ ዘመናዊ መሳርያ ከታጠቀዉ ከመንግስት ሰራዊት ጋር ለመወጋት ወደ ጫካ መግባታቸዉ ስህተት መሆኑን እና ትክክለኛ የትግል ስልት አለመሆኑን” ተችተዋል ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኦነግ ጦር ምዕራብ ኦሮሚያን እንዲቆጣጠር መንግስት እውቅና እንዲሰጠው ግንባሩ ያቀረበውን ጥያቄ በመንግስት በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ውድቅ መደረጉ ተገልጿል። በኦነግና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በተደረገ ውጊያ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት የተከሰተ ሲሆን ፤ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የሰው ህይወት የጠፋ ሲሆን ይሄን በተመለከተ እስካሁን ሁለቱም ወገኖች በይፋ የሰጡት መረጃ ባይኖርም፤ በምዕራብ ወለጋ እና ነቀምት መንገዶቹ ተዘግቷል ፣ ባለዉ የፀጥታ አለመረጋጋት ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴን እና የንግድ ሂደት ተቆርጧል ።

መንገዶች በመዘጋጋታቸው የተነሳ የመማር ማስተማሩ ሂደት መስተጓጎሉን የሚገልጹት ምንጮች ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መሄድ ሳይችሉ ቀርተው እንደነበር በፎቶ ግራፎች ጭምር ተረጋግጦ የደረሰን መረጃ ጠቅሟል:: በተለይም ከባህር ዳር ወደ ነቀምት የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ ቢውልም የኦሮሚያ ፖሊስ አካባቢውን በመቆጣጠር እንዳስከፈተው መረጃዎች ደርሰውናል::

በወለጋ ጉሊሶና ደምቢዶሎም መንገዶች ተዘጋግተው የዋሉ ሲሆን ወደ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት እየሄዱ የነበሩ ከሌሎች ክልሎች የመጡ ተማሪዎች መንገድ ተዘግቶ መጉላላት ደርሶባቸዋል::

በሌላ በኩል መንግስት የኦነግ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የጀመረውን ዘመቻ በመቃወም በጉሊሶ፣ በአዶላና በጊምቢ ከተሞች ሰልፎች እንዲደረጉ ተደርጓል:: ለሰልፉ ከፍተኛ በጀት መመደቡን የሚገልጹት ምንጮች ኦነግ ይህንን ያህል ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ከየት አመጣ ሲሉ ይጠይቃሉ::

በሌላ ዜና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት “ወጣቶች መሳርያ በመታጠቅ ከመንግስት ሰራዊት ጋር ለመወጋት ወደ ጫካ መግባታቸዉ ስህተት ነው” አሉ
በወለጋ አከባቢዎች የኦሮሞ ነፃ አዉጭ ግንባር /ኦነግ/ ስራዊት ናቸዉ በተባሉና በኢትዮጵያ መከላክያ ሰራዊት መካከል ላለፉት ቀናቶች ግጭት መከሰቱን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ “ሁኔታዉ በጣም አሳዝኖኛል” አሉ::
“ወጣቶች መሳርያ በመታጠቅ ዘመናዊ መሳርያ ከታጠቀዉ ከመንግስት ሰራዊት ጋር ለመወጋት ወደ ጫካ መግባታቸዉ ስህተት ነው” ያሉት አቶ ለማ “ይህ ትክክለኛ የትግል ስልት አይደለም” ብለውታል::

“አከባቢዉ ላይ ባለዉ የፀጥታ አለመረጋጋት ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴን እና የንግድ ሂደቱን አግቷል::” የሚሉት አቶ ለማ ጫካ የገቡት እነዚህ ወጣቶች ወደ ቀያቸዉ እንዲመለሱ ለማድረግ ከሽማግሌዎች ጋር በመሆን እንደሚሞክሩ እንዲሁም ማህበረሰቡ በጠረጴዛ ዙርያ መወያያት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል:: አቶ ለማ አክለውም “ይህ የማይሆን ከሆነ ለተከሰተዉና ለሚከሰተዉ ችግር መፍትሄ መስጠት እንደሚያስቸግር” ተናግረዋል::

ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ በተለይ በወለጋና አካባቢው ኦነግ ትጥቅ ላለመፍታት ወጣቶችን ሰልፍ ማስወጣቱን ዘ-ሐበሻ መዘገቡ አይዘነጋም:: ይህ የኦነግ ጥያቄም በአሪሲና አካባቢው ተቀባይነት እንዳላገኘም ተዘግቧል::

አቶ ዳውድ ኢብሳ የ40 ዓመት የጦርነት ቆይታቸው በቀላሉ አልላቀቅ ብሏቸው ፤ ዘንድሮውም ከሰላማዊ ትግል በተፃራሪ መንገድ በመቆም ” ትጥቅ ብሎ መፈታት የማይታሰብ ነው ፤ ትጥቅ መፍታት የሚባል (sensitive) ጥያቄ ነው” በማለት ” ትጥቅ ፈቱ መባልም ተገቢ እ አይደለም ከማለታቸው በተጨማሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ “ትጥቅ የሚፈታም የሚያስፈታም የለም” ማለታቸው የሚታወቅ ነው።
በአቶ ዳውድ የሚመራው ኦነግ ትጥቅ መፍታት እንደማይፈልግ መግለጽን ተከትሎ መንግስት በሰጠው መግለጫ ” ኦነግ ትጥቅ ያላስፈታቸውን የሰራዊቱን አባላት ትጥቅ የማያስፈታ ከሆነ መንግስት የዜጎቹን ደህንነትና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማስጠበቅ ሲል” እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቦ እንደነበረ የሚታወስ ነው።  – ዘሀበሻ

Share.

About Author

Leave A Reply