“የወላጆቻችን ልብ”

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ቢቢሲ የአማርኛው ክፍል እንደ ዘገበው አዛውንቷ ወይዘሮ ሙሉነሽ ነዋሪነታቸው የአንድ መቶ ሀምሳ ሰባት ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው አውሮፕላን በተከሰከሰበት ቱሉ ፈራ በተባለው ሥፍራ ሲሆን በተመለከቱት አሰቃቂ አደጋ ሳቢያ ከዚያች ዕለት በኋላ እጅጉን አዝነው እንቅልፍ አጥተዋል። እንባቸውንም በአደጋው ለተቀጠፉት ለማያውቋቸው ሰዎች እያፈሰሱ ቀናት ተቆጥረዋል።

የቱሉ ፈራ የሟርት ተራራ እንደማለት ነው። ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት እኚህ እናት ቤታቸው አደጋው ከደረሰበት ሁለት ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት ቢኖረውም ከአደጋው ቀን አንስቶ አንድም ቀን ከቦታው ርቀው አያውቁም። ከመጣው ቤተሰብ ጋር ሁሉ ያለቅሳሉ “እስካሁን ደጋግሜ ከአደጋው ቦታ ሄጄ ባለቅስም ሃዘኔ አልወጣልኝም” ይላሉ። እንዲያውም እንደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ለማያውቋቸው ሟቾች ተዝካር ለሙታን የሚደረግ ጽሎት ለማውጣት መዘጋጀታቸውን ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ነግረዋል፡፡

እውነተኞቹ ወላጆቻችን እንኳንስ አብረው በልተው አብረው ጠጥተው በማኅበራዊ ኑሮ በባህል እና በሃይማኖት ለሚዛመዱት ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ላማያውቁት መንገደኛ ባዕድ ሳይቀር የሚንሰፈሰፉ እጅግ ምጡቅ የሆነ ስብእና ባለቤቶች ናቸው፡፡

ይህንን ልብ የሚነካ ታሪክ ሳነብ በግሌ እንዲህ የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡ ለመሆኑ እኛ የማ ልጆች ነን? ለሰው ልጅ ሁሉ ማዘንን፣ መተሳሰብን እና ሰብአዊነትን እንዴት እማማ ሙሉን ከመሰሉ ወላጆቻችን ሳንማር ቀረን? ፊደል ቆጥረን ዘምነን እና ሠልጥነናል እያልን ሰብአዊነት ተለይቶናል፡፡ እንከኳንስ ለማናውቃቸው ለእበሮ አደጋችን እና ኢትዮጵያዊ ለሆነ ወገናችን መራራት አቅቶን በጭካኔ ስለት ድንጋይ እና ዱላ የምናነሳው ምን ሆነን ነው? ይህን ክፋትስ ከየት ነው ያገኘነው ?

ስለልጆቻን ሳስብ ይበልጥ ሃዘን ይሰማኛል፡፡ እኛስ እድለኞች ሆነን እማማ ሙሉን የመሰሉ ለሰው ዘር ሁሉ የሚያዝኑ፣ የሚራሩ እና የሚያለቅሱ ወላጆችን በዘመናችን አይተናል፡፡ ወደፈጣሪ ስንጽልይም ‹‹የእናት የአባቶቻችን አምላክ ሆይ ይቅር በለን›› እንላለን፡፡

ይብላኝ ለልጆቻን! ወላጆቻቸውን ስንጣላ እጂ ስንታረቅ፣ ስንጨካከን እንጂ ስንተዛዘን፣ ስንከፋፋ እንጂ ስንስማማ ዓይተው ላላደጉት፡፡ ሰለዚህም ልጆቻችን ወደፊት ወደ አምላካቸው ሲጽልዩ እንዲህ የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ፈጣሪያችን ሆይ ወላጆቻችን የማይተዛዘኑ ጨካኞች እንደነበሩ አንተ ታውቃለህ፡፡ እባክህ ስለአያቶቻችን ብለህ ይቅር በለን›› ፈጣሪያችን ሆይ ለልጆቻን የእኛንሳይሆን የወላጆቻችንን ልብ ስጥልን! የእኛውንማ ልብ እያየኸው ነው። ዮሀንስ መኮንን

Share.

About Author

Leave A Reply