የወያኔ ዲኤክስ፣ የወያኔ አረምና ሌሎች ነገሮች…..

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +
  1. አፋር ውስጥ በአንድ ወቅት በተለምዶ “ወያኔ” የሚባል ዛፍ በቅሎ የአካባቢውን ውሃ በረጃጅም ስሮቹ እየመጠጠ ሌሎች ተክሎች በጥማት እንዲጠወልጉ ምክንያት በመሆን የአካባቢውን ስነምህዳር እንዳልሆነ አደረገው። በኋላም ያንን ስግብግብ ዛፍ የማጥፋት ጥረት ተጀመረ።

ይህንኑ ችግር ለመዘገብ አንድ የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ቡድን ወደስፍራው ያቀናል። የአካባቢውን የግብርና ተወካይ ኢንተርቪው በማድረግ ነበር ቡድኑ ስራውን የጀመረው።

የግብርና ተወካዩ ታዲያ ያንን የመጤ አረም ዛፍ በተመለከተ ማብራሪያ ሲሰጥ “ወያኔ” የሚለውን ስም ላለመጥራት ይጠነቀቅ ጀመር። ጋዜጠኛው ግን በመሃል ሰውየው የፈራውን ጥያቄ ሰነዘረ።

“ለመሆኑ ይህ በቀላሉ የሚዛመትና በአካባቢው ምንም እፀዋት እንዳይበቅሉ የሚያደርግ ዛፍ አረም ስሙ ምንድነው?”

ሰውየው መልሱን ለመመለስ አላመነታም።

” ደርግ ይባላል”

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ከቃለምልልሱ በኋላ “ምን ነካህ?” ቢሉት

“ታዲያ ማንም ያወጣውን ስም እኔ ጠርቼ ምላሴን ይቁረጡት?” አለ አሉ።

ይህ ሰውዬ ባለፈው ወር በቲቪ ቀርቦ “ሽፈራው” ስለሚባለው ተክል ሲያወራ ግን ሽፈራው ሽጉጤ ይደብረዋል አላለም ነበር።

  1. አውቶሞቲቭ ጆርናል የተባለ የራዲዮ ፕሮግራም ላይ አንድ አድማጭ ስልክ ደውለው የመኪናቸውን ችግር እያብራሩ ነው”

“ፍሬን ስይዝ የኋላ እግር ድምፅ ያወጣል።በዚህ ላይ ነዳጅ ይበላል።ኢግኒሽን ፕለግ ዘይት እየተኛበት እንጉልፋቶ ይሆናል……ደሞ…………”

አዘጋጁ አቋረጣቸውና ” በቅድሚያ የመኪናዎን ብራንድና ሞዴል ቢነግሩን ”

“ወያኔ ፣ 1992”

“ሽሽሽሽሽሽሽሽ……”

ዝግጅቱ ለሰከንዶች ተቋረጠና ሰውየው ከመስመር ጠፉ

አዘጋጁ ምን ቢል ጥሩ ነው? “አድማጮቻችን ……ስንደውል መኪኖቻችንን በተለምዶ ስም ባንጠራቸው?”

አባዱላ ስለተባለው መኪናቸው ብልሽት ለመናገር በስልክ ተራ ይዘው የነበሩ ሰውዬ ይህን ማስጠንቀቂያ ሲሰሙ ፈርተው ስልኩን ዘጉት።

ቀደም ብሎ እኮ አዘጋጁ ራሱ D4D የተባለውን ቶዮታ መኪና አሰራር ሲያብራራ “ዶልፊን” እያለ ነበር በተለምዶ ስሙ የጠራው።

  1. ጃንሆይ ሉሉ የተባለች ውሻቸውን አስከትለው በአንድ ኮሌጅ የራዲዮ ኮሙኒኬሽን የሚማሩ ወታደሮችን እየጎበኙ ነው። በመሃል ሉሉ አንዱ ሻምበል እግር ስር ገብታ እየነካከሰች አላሰራ አለችው።

ሻምበሉ “ክስ! ሂጂ ከዚህ ” ብሎ ሊያባርራት አስቦ “ኋላ ደግሞ ውሸዋን መናቅ ጃንሆይን መናቅ ይመስልብኛል” ብሎ ተወው ። የውሻዋ ንክሻ ሲበዛበት ግን ምን ቢሉ ጥሩ ነው?

“ይሂዱ ከዚህ አንቱ !”

ይህን ካለ በኋላ ደግሞ ደንገጠ። ” አለቀልኝ! ጃንሆይ እሳቸውን መስሏቸው ጉዴን አፈሉት !” ብሎ ሲንቀጠቀጥ እሳቸው አልሰሙት ኖሮ ለጊዜው ተረፈ።

ባለፈው ወር በቲቪ ቀርበው ” መንግስት ለተፈናቃዮች “አርከበ ሱቅ” እንኳን ቢሰጠን ምናለበት? ” ያሉት ሴትዮ ውስጤ ናቸው።

(ጋዜጠኛ መላኩ ብርሀኑ)

Share.

About Author

Leave A Reply