የዚህች ባንዲራ ነገር – የግዮን መጽሄት ቅኝት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሰ ኔ 24 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. የአማራ ክልላዊ መንግሥት መዲና በሆነችው ባህር ዳር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተጀመሩ በጎ ተግባራት ድጋፍ ለመስጠት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የታደመበት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል።

ይህ የአዲስ አበባውን የሰኔ 16 ትዕይንተ ህዝብ ተከትሎ የተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ አንድም ባለኮከብ ባንዲራና የአማራ ክልል መለያ ሰንደቅ ያልታየበት ነበር። “አማራ የሚያነሣው ሰንደቅ፣ የኢትዮጵያዊነት መለያ የሆነውን እንጂ በብሔርተኝነት ለተሰፋ ባንዲራ ድጋፍ የለውም፤ ኢትዮጵያን የሚወክላት ሰንደቅ ዓላማ ውስጡ ምንም የፖለቲካ ምልክት የሌለበት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ብቻ ነው” በማለት ህዝቡ ሐሳቡንና ውሳኔውን በተግባር ገልጾ ነበር።

ይህንን ተከትሎ ህወሓት በትግራይ ቲቪ ባስተላለፈው ዘገባ ላይ “በአማራ ክልል የተካሄደው ሰልፍ ደርግ ያደራጀው ሰልፍ ነው። ኮከብ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ ይዞ መገኘት ሕገ መንግሥቱን ስለሚጻረር ሰልፉ በአጠቃላይ ሕገ መንግሥት የተጣሰበት ነው” በማለት ቅሬታውን አቅርቧል። በሰልፉ አመራሮችና ህዝቡ የተጠቀሟቸውን ቃላትም “ይመለከቱኛል” ዓይነት ሥጋቱን አቅርቧል። የህወሓት ወኪል የማህበራዊ ሚዲያ አንቀሳቃሾች በተለይ በባህር ዳር በተውለበለበው ባንዲራ ጉዳይ ላይ ሰፊ ተቃውሞ በማቅረብ ጉዳዩን ከአማራ ገዢ መደብ ፍላጎትና ከጠቅላይነት አስተሳሰብ ጋር አዛምደው ለመንቆር ሞካክረዋል። በዚህ ባንዲራ የተነሳው ክርክር አሁን ድረስ ያልበረደ ከመሆኑ፤ በተለይም ህዝቡ ባንዲራው እንዲቀየር አጥብቆ ከመፈለጉ ጋር በተያያዘ ከባንዲራው እና ከሀገር ፍቅር ስሜት ጋር የተያያዙ ትርክቶችን በዛሬ ጽሑፋችን እንዳስሳለን።

“ለመሆኑ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ባንዲራ የቱ ነው?” ብለንም እንጠይቃለን። ታሪክና ጀግንነት የኢትዮጵያ ህዝብ የላቀ ቦታ ከሚሰጣቸውና እንደማንነቱ መገለጫዎች ቆጥሮ ከማይደራደርባቸው ነገሮች ውስጥ ሀገር፣ ሰንደቅ ዓላማና ነጻነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ታሪክ እንደሚመሰክረው ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ ለመጣበት ግንባሩን የማያጥፍ፣ ኩሩና በነጻነት መኖርን የለመደ ህዝብ በመሆኑ መገዛት እና በሌሎች ተጽዕኖ ውስጥ መውደቅን አጥብቆ ይጠላል።

በዚህ ሳቢያም በዘመነ ቅኝ ግዛት የአፍሪካ ሀገራት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ እንደቅርጫ በተቀራመቷቸው ቅኝ ገዠዎች መዳፍ ሥር በወደቁበት ዘመን አየሯ የነጻነት ንፋስ እየነፈሰባትና አፈሯ በቅኝ ገዢዎች ሳይረገጥ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ዘመኑን የተሻገረች ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ ያላትን ጥንታዊቷን ሀገር ኢትዮጵያን ዓለም የሚያውቃት በዳበረ ታሪኳ ብቻ ሳይሆን፤ ለውጭ ወራሪ ኃይል ሳትንበረከክ ነጻነቷንና ሰንደቅ ዓላማዋን አስከብራ የኖረች ባለታሪክ ሀገር በመሆኗም ጭምር ነው። በተለይም የአፍሪካ አህጉር ህዝቦች ክብርና ማንነታቸው ተዋርዶ፣ ለባርነት ተዳርገውና በነጮች ተረግጠው ባህልና ቋንቋቸው እስኪጠፋ ድረስ በገዛ ሀገራቸው የተሰቃዩበት የቅኝ ግዛት ታሪክ ያልደፈራት በመሆኗ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ተብላ እንድትጠራ ምክንያት ሆኗል።

የጥቁሮችን ታሪክ የሚጽፉ ምሁራን ደጋግመው እንደሚያነሡትም፣ ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ዘመን ጭዳ ያልሆነችው ሳትወረር ቀርታ ሳይሆን፤ ከዚህ ቀደም በታሪክ ሊመዘገብ ቀርቶ ሊኖር ይችላል ተብሎ በማይታሰብ ቆራጥነት ነጭ ቅኝ ገዢና ወራሪ ኃይልን ጦርነት ገጥማ ድል በመንሣቷም ጭምር ነው። በዚያ የአፍሪካ ኋላ ቀር የጨለማ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝቦች ዘርና ጎሳ፣ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለዩ፤ ለአንድ ሀገራቸው በጋራ በመዝመት እስከአፍንጫው የታጠቀውንና ማንም የሚቋቋመው የማይመስለውን ወራሪ የጣልያን ጦር፤ በሀገር ፍቅር ወኔና በጀግንነት ብቻ እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ መክተው፤ ድል በመንሣት የሽንፈት ካባ ማከናነባቸው እስከዛሬም ለዓለም ትንግርት እንደሆነ ኖሯል።

ኢትዮጵያውያን ወራሪውን የጣልያን ፋሽስት የመስፋፋት ህልም በማጨንገፍ በጦር ሜዳ ገጥመው ድል የነሡበት የአድዋ ጦርነት፤ መላውን የአፍሪካና የዓለም ጥቁር ህዝቦች አንገት ቀና ያደረገ አኩሪ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያ፣ ተፈራርቀው በገዟት ኃያል መንግሥታቷ ታሪክ ውስጥ በዘመኗ አንድም ጊዜ ሌላ ሀገር ወርራ አታውቅም። ነገር ግን ከቱርክ ፓሻዎች እስከ ግብፅ ፈርዖኖች፣ ከመሃዲስቶች እስከ ደርቡሾች እንዲሁም ከእንግሊዞች እስከ ጣልያኖች ተስፋፊውን የሶማሊያ ጦር ጨምሮ ድንበሯን ጥሶ ለመግባት ተደጋጋሚ ወረራ ተፈጽሞባት በጀግኖች ልጆቿ ደምና አጥንት አጥሯን ሳታስደፍር ዘመናትን ተሻግራለች። የዚህ ሁሉ በደምና በአጥንት የተዋጀ ነጻነት ማሰሪያ ጥብጣብ፤ የኢትዮጵያ መለያ የሆነው አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ይህ ሰንደቅ ዓላማ በአምሥት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ዘመን ወድቆ፤ በጀግኖች አርበኞች መሥዋዕትነት ዳግም ወደማማው ከመመለሱ በቀር በዘመናት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንዴም የነጻነት ምልክትነቱ ሳይጠፋ ሁሌም ሲውለበለብ ኖሯል።

ብዙዎች እንደሚሉትም ከቅኝ ግዛት ዘመን ማክተም በኋላ የአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ቀለሞች የተዋቀሩት በነዚሁ ሦስት ቀለማት የመሆኑ ዋና ምክንያትም ይህንኑ የነጻነት ተምሳሌት የሆነውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለማሰብ ነው። የሀገር እና የባንዲራ ፍቅር (እድሜ ለኢህአዴግ ይሁንና) እንደዛሬ የባንዲራ ክብር በፖለቲካ አተያይ እና በተዛቡ ታሪኮች የተንሻፈፈ ትርጉም ይዞ የክርክርና የጸብ መንስዔ ከመሆኑ በፊት በዚያ የሀገር ፍቅር ስሜት በደሙ ገብቶ ያነድደው በነበረ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ውስጥ ሀገር ማለት ነጻነት፣ ነጻነት ማለት ደግሞ በኩራት የምትውለበለብ ሰንደቅ ዓላማ ማለት ነበር።

እስከዘመነ ኢህአዴግ ዋዜማ ድረስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሩ ጉዳይ በአንድ አሳብ እና በአንድ መንፈስ ተሳስሮ እንዲኖር ምክንያት የሆነው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩን ሰንደቅ ዓላማ የኔ ብሎ ተቀብሎ መኖሩና ለባንዲራው ክብርም ሕይወቱን መሥዋዕት እስከማድረግ የደረሰ ፍቅር ስለነበረው ነው። ድሮ ወራሪዎች በጦር ሞክረው አልሳካላቸው ሲል በሽንፈት የተሰናበቱበትን ኢትዮጵያን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖትና በብሔር ከፋፍሎ የማዳከም እቅድ ዛሬ በራሱ ፍላጎት በተግባር ለማሳካት እየዳከረ ያለ (በመጠኑም የተሳካለት) የፖለቲካ አመራር የሚፈነጭባትን መሬት በደምና አጥንታቸው ዋጋ ከፍለው ያስረከቡን አባቶቻችን የተዋደቁት ለሰንደቃቸው ክብር ነበር። ለኢትዮጵያዊ፣ ባንዲራ ማለት ማንነት ነው። ባንዲራ ማለት በደም የሰረጸ ነጻነት፣ የባለታሪክነት ምስክር፣ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ፣ የነጻነት ዓርማ፣ የሀገር ፍቅር ስሜት ማከማቻ ነው።

በዚህ ሳቢያም ነው ኢትዮጵያውያን በቀደመ የነጻነት ታሪካቸው መለያቸው ሆኖ የኖረ ሰንደቃቸውን በየትኛውም የዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ማውለብለብ ህልማቸው ሆኖ የሚኖሩት። በጦርነት ጊዜ “ተከተል ንጉሥህን፤ ተመልከት ባንዲራህን” ብሎ በወኔ የሚተም ተዋጊ ሠራዊት ከዚያ የጦር አውድማ የሚበተነው፤ ሰንደቁ ከዓይኑ የጠፋ እና የወደቀ እንደሆነ ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊ፣ በውጊያ ላይ እያለም ቢሆን፤ አንዱ ሲወድቅ ሌላው ሰንደቁን እያነሣ እስከመጨረሻው ባንዲራውን መሬት ላለማስነካት እየታገለ ነው መሥዋዕትነት ከፍሎ ለድል የሚበቃው። በዚህ ሳቢያ የትኛውም ቦታ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ያየ ኢትዮጵያዊ በፍጹም የሀገር ፍቅር ስሜት በዓይኖቹ ዕንባ ይሞላል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ የሌት ተቀን ሕልማቸው ነው። ለዚያም ነው ባንዲራው ሲሰቀል ዕንባቸውን መቆጣጠር የማይችሉት። በሰው ሀገር ስደት ላይ ያለ ኢትዮጵያዊም ሰንደቅ ዓላማውን ሲያይ ሀገሩን እንዳየ የሚደነግጠውና የሚደሰተው፣ “የሰው ሀገር ሰው፤ ባንዲራ ዘመዱ” ብሎ የሚተርተው ለዚሁ ነው። ኢትዮጵያዊ ማለት ለሕግ እና ለባንዲራ ታማኝ የሆነ ህዝብ ነው። በቀደመው ዘመን “በሕግ አምላክ!” ተብሎ ተጠይቆ እምቢ የሚል፣ “በባንዲራው!” ተብሎ የተጠየቀውን የሚጥስ ማንም ሰው እንደነውረኛ ብቻ ሳይሆን እንደ ከሃዲ ይቆጠር ነበር። የሕግንና የባንዲራን ክብር ማናናቅና ለቃሉም አለመገዛት ብቻውን ለክስ እና ለቅጣት የሚያበቃ ወንጀልም ነበር።

በተለይም ኢትዮጵያን ከጣልያን የግፍ ወረራ ነጻ ለማውጣት በጥንት አባቶቻችን በተካሄደው የአምሥት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመን በኋላ በነበረው የነጻነት ጊዜ “ወድቆ በተነሣው ባንዲራ!” ብሎ መለመን ወይም መገዘት፤ ብቻውን ማንኛውም ሁከት እንዲወገድ ወይም ሰዎች ከጀመሩት መልካም ያልሆነ ተግባር እንዲታቀቡ ለማድረግ በቂ ነበር። በኢትዮጵያ የባንዲራ ክብር እዚህ ድረስ ነበር። ክብርና ባንዲራ በኢትዮጵያ ከተነሱ መንግሥታት ሁሉ እንደኢህአዴግ ራሱ በሚመራት ሀገር ላይ የተሳለቀና ታሪክና ክብሯን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት መንግሥት ተነሥቶ አያውቅም። በታሪክ ተመራማሪዎች ጥያቄ የማይቀርብበት፣ በብዙ ማስረጃዎች የተደገፈውና የተረጋገጠው እውነት፤ ኢትዮጵያ የ3 ሺህ ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነች ሀገር መሆኗ ነው።

ይህንን እውነት ዓለም አክብሮት ህወሓት/ኢህአዴግ ግን የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ100 ዓመት አውርዶታል። ህወሓት ከጅምሩም ሆነ እስካሁን ድረስ አብሮት በኖረ እምነቱ “ከትግራይ ውጪ ያለው ቀሪ የኢትዮጵያ ክፍል ታሪክ አልባ ነው” ብሎ ያምናል። በህወሓት ስሌት መሠረት የኢትዮጵያ የታሪክ አስኳል ትግራይ እንደመሆኗ፤ ትግራይን መገንጠል ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ታሪክ ከምኒልክ ዘመን ጋር ብቻ አቆራኝቶ ያስቀራታል ብሎ ያምናል፤ ሲሠራም የኖረው ይህንኑ ለማስፈጸም ነበር። ከጅምሩም ትግራይን ነጻ የማውጣት ዓላማ ብቻ ይዞ ብረት ያነሣው ይህ ፓርቲ፤ በታሪክ አጋጣሚ ግንባር ፈጥሮ ኢትዮጵያን የመምራት ዕድል ሲያገኝ ለአገዛዙ እድሜ ለመቀጠል ሲል የኖረ እምነቱን ጠረጴዛ ሥር ከትቶ አስቀምጦት ኖሯል።

ያም ሆኖ አልፎ አልፎ እውነተኛ ማንነቱ ብልጭ ማለቱ አልቀረም። ህወሓት ከዚህ የ100 ዓመት የታሪክ ትርክቱ ባሻገር ግን አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ጥርስ ውስጥ የከተተው በወቅቱ የድርጅቱ ሊቀ መንበር እና የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የሆኑት መለስ ዜናዊ “ባንዲራ ጨርቅ ነው” በማለት ስለባንዲራ በአንደበታቸው የተናገሩት ንግግር ነው። ይህ ንግግር ለባንዲራው ክብር ሲል ነፍሱን አሳልፎ በሰጠው ትውልድ ዘንድ እስካሁን ድረስ በህወሓት ላይ ያልተፈታ ቂም እንዲቋጥርበት አድርጓል።

የኢትዮጵያ ባንዲራ በየዘመኑ ሀገሪቱን እንዳስተዳደሯት መንግሥታት ቀለሙ አንድ ሆኖ መሐሉ ላይ ግን ምልክት ሲቀያየርበት ኖሯል። በምኒልክ ዘመን “ም” የሚል ምልክት እንደነበረው ሲነገር፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ደግሞ የይሁዳ አንበሳ ዓርማ ነበረበት። የደርግ ዘመን በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ጊዜው ማጭድና መዶሻ ኋላም ኢህዲሪ ሲመሠረት ያንኑ ዓርማ በባንዲራው ላይ አትሟል። ደርግ ከወደቀ በኋላ፣ የኢህአዴግ መንግሥት በባንዲራው ላይ ኮከብ በማተም ሥራ ላይ አውሎታል። ያም ሆኖ ከኢህአዴግ ውጪ በነበሩት ያለፉት መንግሥታት ህዝብ በብሔራዊ፣ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ወቅት ይዞ የሚወጣው ባንዲራ፤ ምንም ዓርማ የሌለውን ሲሆን፣ ባለአርማዎቹ ባንዲራዎች ለጽህፈት ቤትና ለኦፊሴል አገልግሎት ብቻ ሲውሉ ኖረዋል። ነገር ግን ኢህአዴግ ባንዲራውን ከቀየረ በኋላ ሕግ በማውጣት፣ ኮከብ የሌለው ባንዲራ የያዘ ሰው በሕግ እንደሚቀጣ በመደንገጉ ለወትሮ ባንዲራን እንደክት ልብሱ በቤቱ በጥንቃቄ ያስቀምጥ የነበረው ኢትዮጵያዊ ባልተለመደ ሁኔታ ከአዲሱ ባንዲራ ጋር ተለያየ። ቤተ ክህነት ሳትቀር የፖለቲካ ዓርማ ያለበትን ባንዲራ ለማውለብለብ ተገደደች። ይህም ብዙዎችን አስቆጥቶ ቀን እንዲጠብቁ አደረጋቸው።

በአጼ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የፓርላማ አባል የነበሩትና የአርቃቂ ኮሚሽኑ አባል የሆኑትሻለቃ አድማሴ በ1987 ዓ.ም. የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ጉባዔ ላይ፤ የህወሓት/ ኢህአዴግ ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ኢህአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም. አካባቢ በቴሌቪዥን ቀርበው፣ “ባንዲራ ጨርቅ ነው” ብለው መናገራቸውን በመጥቀስና ታጋዮቹም ባንዲራውን የጨውና የዱቄት መጠቅለያ ማድረጋቸው ትክክል አለመሆኑን አንሥተው ባንዲራ ክብር መሆኑን ለማስረዳት ጥረው ነበር።

ሻለቃ አድማሴ፣ በወቅቱ አቶ መለስን ሲያስጠነቅቁ “በዚህች ባንዲራ ላይ አንዲት ነገር ብትጨምሩባት ህዝቡ አይቀበላችሁም፤ ይቃወማችኋል” ብለዋቸው ነበር። እንደትንቢት ሆኖም እነሆ ህዝብ በዚህች ባንዲራ የተነሣ ኢህአዴግን ሁለት ዐሥርት ዓመታት በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሲቃወም ኖረ። በወቅቱ ለሻለቃ አድማሴ ጥያቄ ከረር ባለ ድምጸት የተሰጠው የአቶ መለስ ምላሽ ግን ህወሓት እንደፓርቲ ሲታይ ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጋር ባለው የተለየ አመለካከት ጸብ እንዳለው በግልጽ ያሳየ ነበር። “ኢህአዴግ የራሱ መለያ አለው። ከባንዲራው ጋር ችግር የለበትም። ችግሩ ከባንዲራው ኋላ ካለው ‘የኔ ጥሩ፤ ያንተ ጥሩ ያልሆነ’ ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ባንዲራውን ከፈለገው የራሱ ጉዳይ ነው። ባለበት እንዲቀጥል ያደርጋል ወይም ይለወጥ ካለም ይለወጣል” በማለት “ባንዲራ ከጨርቅ የዘለለ ትርጉም የለውም” የሚለውን የቀድሞ ቃላቸውን አድሰውታል። ባንዲራው ለጨው እና ለዱቄት መያዣ መዋሉን በተመለከተ ለተጠየቁት ሲመልሱም “አንዳንድ የድርጅታችን አባላት ነገሩን በውል ባለመገንዘብ አድርገውት ሊሆን ይችላል፤ ያም ሆነ ይህ ግን ኢህአዴግ ከባንዲራው ችግር የለበትም” በማለት ፓርቲያቸው የባንዲራው ጉዳይ ያን ያህል የማያስጨንቀው መሆኑን በድጋሚ ገልጸዋል።

አቶ መለስ “ኢህአዴግ የባንዲራው ጉዳይ ያን ያህል አያስጨንቀውም” ባሉበት እና “የኢትዮጵያ ህዝብ ባንዲራውን ከፈለገው የራሱ ጉዳይ ነው፣ ይለወጥ ካለም ይለወጣል” ብለው በተናገሩበት አፍ ዛሬ ከ27 ዓመታት በኋላ በባንዲራው ጨው ሲቋጥሩበት የኖሩት የፓርቲያቸው ሰዎች ባንዲራውን ተንተርሰው ሕገ መንግሥት ተጣሰ እያሉ ነው። የቀድሞ መሪያቸው “ህዝቡ ባንዲራውን ካልፈለገው ሊለውጠው ይችላል” ያሉትን ረስተው፤ ህዝብ ወደቀድሞ መልኩ የተቀየረውን ባንዲራ ብቻ እንደሚፈልግ የተናገረበትን መድረክ “ደርግ የነገሠበት መድረክ” በማለት አጣጥለውታል። “የህዝብ ባንዲራ” ጠ/ሚ ዐቢይ ወደሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንሥቶ በይቅርታ፣ በፍቅርና በመደመር መርህ የሀገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ 360 ዲግሪ በመቀየር ማንም ያልጠበቀውን ሪፎርም ጀምረዋል። በዚህ ሳቢያም ከህዝብ ፍላጎት ውጪ በሆነ መንገድ መንግሥት ሀገር መምራት እንደማይችል በማመን፣ ኢትዮጵያ ከገባችበት የእርስ በርስ መጠላላትና ጠቅላላ ውድቀት ይታደጋታል ላሉት ለዚህ ሪፎርም እንቅፋት የሆኑትን አካላት በጊዜ ጥግ አስይዘዋቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝቡ ልብ ቀርበው የዘመናት ጥያቄዎቹን በመመለስ የወሰዷቸው በጎ እርምጃዎች ባረጀና ያፈጀ የተንኮል፣ የጭቆና እና የአውቅልሃለሁ ፖለቲካ የሚመራውን የአዛውንቶቹን ፓርቲ ህወሓትን ያስከፋው ሲሆን ከፌዴራል የሥልጣን መዋቅሩ በጡረታ የተሰናበቱ አዛውንት አመራሮቹን ይዞ መቀሌ ላይ እስከመመሸግና እንደተቃዋሚ ፓርቲ ይፋዊ የተቃውሞ መግለጫ እስከማውጣት አድርሶታል። ህወሓት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሪፎርም መንገድ በተቃራኒ የቆመ መሆኑን በተዘዋዋሪ በሚያደርጋቸው አሉታዊ ተግባራት በይፋ አውጇል። በሃገሪቱ ውስጥ እዚህም እዚያም የሚቆሰቆሱ ብጥብጦች እና አለመረጋጋቶች ይህንን የለውጥ ጉዞ ለማስቀረት የተወጠኑ እርምጃዎች መሆናቸውን የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብም፣ እነዚህን ቁማርተኞች በመቃወም ከጠ/ሚ ዐቢይ ጎን ለመሰለፍ እና ድጋፉን ለመግለጽ ታላቅ ህዝባዊ ትዕይንት ማካሄድ የጀመረው በዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ነበር። እዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ህዝቡ ቀድሞ ሲቃወመው የኖረውን፣ ነገር ግን የህወሓት/ ኢህአዴግ መንግሥት ከህዝብ ፍላጎት ውጪ የሀገሪቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ያደረገውን ባለኮከብ ባንዲራ በመተው ምንም ምልክት የሌለውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ነበር በብዛት ይዞት የወጣው።

ያ ታላቅ ትዕይንተ ህዝብ ጠ/ሚ ዐቢይ “የቀን ጅቦች” ባሏቸው የለውጥ አደናቃፊና አኩራፊ ኃይሎች በታቀደ ተንኮል በቦምብ ፍንዳታ ቢቋረጥም፤ የህዝቡ የለውጥ መንፈስ ግን ሊዳከም አልቻለም። ይህንን በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተመዘገበ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ከተሞች የተካሄዱት ሰልፎችም ተመሳሳይ ዓላማ ያነገቡና በተለይ በኮከብ አልባው ባንዲራ የደመቁ ነበሩ። ከዚህ ድጋፍ ጎራ አለመሆኗን በግልጽ ያወጀችው መቀሌ፣ ሰልፍ ማድረግ ቀርቶ በተቃራኒው የጠ/ሚ ዐቢይን ጉዞ የሚቃወም እና እርምጃው ከህወሓት ፍላጎት ተቃራኒ መሆኑን የሚያውጅ መግለጫ በማውጣት ተጠምዳ ከርማለች። የክልሉ ቴሌቪዥንም የአዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች የሚካሄዱ የድጋፍ ሰልፎችን ላለመዘገብ እንደምክንያት ያስቀመጠው ከሰንደቅ ዓላማው ጋር የተያያዘ ትርክቱን ነው።

ህወሓት ከበላይ ሆኖ የመራው ኢህአዴግ ለዘመናት የሰውን ሰብዓዊ መብት ሲገፍፍ እና መንግሥታዊ አሸባሪነት ተግባር ውስጥ ገብቶ ራሱ ሕገ መንግሥቱን ሲንድ ኖሮ፤ ከጥቅሙ ጋር የሚጋጭና ከፖለቲካ ሥልጣኑ የሚያገልለው ሂደት ሲመጣ የባንዲራውን ነገር በማስታከክ ደርሶ የሕገ መንግሥቱ ጠበቃ ሆኖ ብቅ ማለቱ ብዙዎችን አስገርሟል። በዚህ ሂደት ላይ ሳለ ነው እጅግ ብዙ ህዝብ የተካፈለበት የባህር ዳሩ ትዕይንተ ህዝብ የተካሄደው። ይህ ሰላማዊ ሰልፍ ከአዲስ አበባውም ሆነ ከክልል ከተሞች የሚለየው ነገር ሙሉ በሙሉ በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያ ባንዲራ ብቻ መድመቁ ነው። በዚህ ሰልፍ ላይ የክልልም ይሁን የፓርቲ ሰንደቅ ዓላማዎች አልተውለበለቡም። በሰላማዊ ሰልፉ የገነነው እና የጎላው ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።

በሰልፉ ላይ ህዝቡ ብቻ ሳይሆን የክልሉ ጸጥታ ኃይሎችም የያዙት ባንዲራ ይህንኑ ኮከብ አልባውን ባንዲራ ነው። ትዕይንተ ህዝቡ በተካሄደበት ስታዲየም ዙሪያ ስታንዣብብ የዋለችው ሄሊኮፕተርም በይፋ ታውለበልብ የነበረው ሰንደቅ ዓላማ ይህንኑ ነው። ከህዝብ ተቃርኖ ወዴት ይጓዟል? ህዝብ የሚፈልገውን መከተል የመንግሥትና መሪ ፓርቲዎች ድርሻ ነው። ኢህአዴግ በህዝብ የተመረጠ ፓርቲ ባይሆንም በሥልጣን ላይ ለመቆየት ቢያንስ የህዝቡን ጥያቄ መመለስና ህዝብ በሚፈልገው መንገድ መጓዝ ግድ ይለዋል። እንዲያ ካልሆነ ከህዝብ ጋር ወደቅራኔ መግባትና በመጨረሻም ራሱ ወደሥልጣን በመጣበት መንገድ በአመጽ መውረድ ዕጣ ፈንታው ይሆናል። ጠ/ሚ ዐቢይ ይህንን ቀድመው መገንዘብ የቻሉ የፓርቲው ሰው ናቸው።

እንደአጠቃላይ መዋቅር ፓርቲያቸው የሚከተለው አግላይና ጠቅላይ አመራር የዴሞክራሲያዊ መንግሥት መገለጫ አለመሆኑ በመሪና በተመሪ መካከል እያደር ያመጣውን ክፍተት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ እርቅ እና ይቅርታ በመድፈን የፓርቲውን መንገድ ለማስተካከል በመጣር ላይ ይገኛሉ። ይህ ግን “እኛ ካልሆንን ማንም በዚህ ስፍራ መቀመጥ የለበትም” ለሚሉት ህወሓቶች አልተዋጠላቸውምና በሰበብ በአስባቡ የጠ/ሚ ዐቢይን አመራር ለመተቸት ብሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተከሰተ ለሚሉት ጥፋት ሁሉ ተጠያቂ ለማድረግ ሞክረዋል። በግልጽ በስም ማጥፋት ዘመቻ ላይም ተጠምደዋል።

ከነዚህ መክሰሻ ምክንያቶቻቸው ውስጥ በ17 ዓመታት ትግላቸው ወቅት የናቁትንና የሚፈሩትን፣ አንድነትን የሚሰብክ እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስተሳስር በመሆኑ ሊያጠፉት ተነሥተውለት የነበረውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የመነታረኪያ ርዕስ አድርገው ተነስተዋል። ህወሓቶች፣ ይህ የህዝብ ምርጫ የሆነ ኮከብ አልባ ባንዲራ በሁሉም ስፍራ ሲውለበለብ ዝም ብለው፤ ነገር ግን በባህር ዳር ሲውለበለብ የተቃወሙበት ምክንያት ለዘመናት ለአማራ ህዝብ ያላቸውን ጥላቻ ስላጋለጠባቸውና የብአዴን አመራርም ሴራቸውን ደርሶበት፣ ከነርሱ መጠንቀቅ ተገቢ መሆኑን ስላወጀባቸው ብቻ ነው።

በዚህ ሳቢያ የባህር ዳሩ ሰልፍ ጸረ-ትግራይ ብቻ ሳይሆን ደርግ ያዘጋጀው ሰልፍ ነው እስከማለት የደረሰ ድፍረት ፈጽመዋል። ይህ ሴራና የለውጥ አደናቃፊነት ተግባራቸው ይቆይ ይሆናል እንጂ ራሳቸውን ከተሸሸጉበት የትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ አውጥቶ ሜዳ ላይ በመጣል በገዛ እጃቸው ባመጡት ጦስ ከባድ ዋጋ እንዲከፍሉበት ማድረጉ አይቀሬ ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply