“የዮቶር ልጅ ርስቱ፤ አባይ ሆኖ ጣና ዳር ቤቱ…” – ዮቶር ማን ነው?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ዮቶር ማን ነው?

የሰው ልጆች ጥበብ ፣ ባህል፣ እምነት እና ታሪክ ለአንድ ሀገር ዘላቂ እድገት እና ለውጥ የህልውና መሰረቶች ናቸው። ዘመን ተሻጋሪ የሆነ አኩሪ ባህል እና ታሪክ ያለው ህዝብ በእያንዳንዱ ቀጣይ ስራዎቹ ጀርባ የብርታትና የአብሮነት መንፈስን  በማጎናጸፍ በተሰማራበት የህይወት መስክ ሁሉ የስኬት ምንጭ ናቸው። ታሪክ የሌለው ህዝብ መነሻ የሌለው ነው። መነሻውን የማያወቅ ደግሞ መድረሻው ምን መሆን እንዳለበት ለመወሰን ያዳግተዋል። “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ፣” አይደል የሚባለው? ኪነ-ጥበብ ደግሞ ጠቅለል ባለ መልኩ ስንገልጸው ልክ እንደ መስታዎት ፍንትው አድርገው የሕዝብን ሁኔታ፣ የአኗኗር ዘይቤን ፣ ባህልን፣ ፍቅርን፣ ብሶትን፣ አንድነትንና ታሪክን በተከሽኑ ህብረ -ቀለማት እና ዜማዎች አዋህዶ በማቅረብ ማንነትን ማሳየት እና መስበክ፥ ሰውንም ያለጉልበት ማሳመን የሚችል ነው።

ወደ አነሳሁት ርዕስ ልመለስ፡ ዩቶር ማነው? ዩቶር መጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ የሰው ስም ነው። “ዮቶር” /ራጉኤል/ የተባለው ሰው ኢትዮጵያዊ ሲሆን በጊዜው የጣና ሀይቅና የአባይ ዙርያ አካባቢ መጠርያ ስም “ሞርያም” ይባል ነበር። ዮቶርም የሞርያም ካህን ነበር በዚህ ጊዜ ሙሴ ከግብፅ ከፈርኦን ፊት ወደ ኢትዮጵያ /ሞርያም/ ምድር መጥቶ ይቀመጣል።

7 ሴት ልጆች የነበሩት ዮቶር ከአባይ ወንዝ ከብቶችን ውሃ እንዲያጠጡ ልጆቹን ሲልክ ሙሴን አግኝተው ይመለሳሉ። ሙሴና ዮቶር ሲገናኙ ደግሞ ዮቶር ሲፓራ የተባለችውን ሴት ልጁን ለሙሴ ይድርለታል ….ሁለት ልጆችንም ወለደ፡፡ አልዓዛር እና ጌርሳምን [ኦሪት ዘጸአት፡ 18፥ 3-4]። ኢትዮጲያዊው ካህን ዮቶር እና ሙሴ አማት እና አማች ሆኑ ማለት ነው።

[ኦሪት ዘኁልቅ 121] ላይ እንዲህ የሚል ቃል ይገኛል ‹‹ሙሴም ኢትዮጵያዩቱን አግብቷልና ባገባት በኢትዮጵያዩቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በርሱ ላይ ተናግሩ። እነርሱም በእዉኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሯልን፧ በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን አሉ እግዚአብሔርም ሰማ

ሙሉውን ቃል ማንበብ ይቻላል።

ካህኑ ዮቶር ከዘመናት በኋላ የልጅ ልጆቹንና የሙሴን ሚስት (ሲጳራን) ይዞ ሙሴን ሊጎነኘው ሄዷል፡፡ ሙሴም ዕብራዊያንን ይዞ ከግብጽ ምድር ሥለወጣ እና ዮቶርም እግዚአብሔርን ሊያመሰግን በተገናኙበት ጊዜ፤ ሙሴ በዕብራዊያንን ላይ ተስፋ ቆርጦ እና ለማስተዳደርም አስቸግረውት ሲሰቃይ፤ ሕዝብን የማስተዳደርን ጥበብ፣ ዘዴ እና ሥልጣኔ ዮቶር አስተምሮታል [ኦሪት ዘጸአት፡ 18፥ 14-26]።

  • መሪው በእግዚአብሄር ፊት ለሕዝቡ ይቆማል
  • ሥርዓቱንም ሕጉንም ያስተምራል፤ ያሳያል
  • መሪውም ከሕዝቡ መካከል አዋቂዎችን ይመርጣል፤ (እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፤ የታመኑትን፤ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን፤) እነርሱንም አለቃ አድርጎ ይመርጣል
  • በሕዝብ ላይ ይፈርዳሉ፤ ከዚህ የበለጠውንም (የከበዳቸውንም) ወደ መሪው ይወስዱታል፤ ለመሪውም ሸክሙን ያቀሉለታል…

ዮቶር ይህንን ጥበብና ሥርዓት ለሙሴ አስተማረው።

እንግዲህ እናስተውል፡ ሕዝብን የማስተዳደር ጥበብ ግሪካዊያን የዲሞክራሲን ጽንሰ ሐሳብ ከመስበካቸው በፊት፡ዮቶር /ራጉኤል/ ለሙሴ ሕዝብን በዲሞክራሲያዊ ሁኔታ የማስተዳደር ጥበብ አስተምሮታል፤ ይህም የሆነው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በሀገራችን መከናወኑን ስናስብ ካህኑ ዩቶር ኢትዮጵያውያን የሰው ልጅ ስልጣኔ ምንጭ መሆናቸው አስረጂ የሚሆን ታላቅ አባት ነበር። ታሪኩ እንዲህ እያለ ይቀጥላል……

ታድያ ቴዲ ይህን ታላቅ ሰው ታሪካዊ ዳራው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ነበር ስሙን ጠርቶ ያዜመው! አዳሜ ወደ ቀልብሽ ተመለሽ ሲል ነበር። የተጠራጣሪነትና የባንዳነት መንፈስ የተጠናወተህ/ሽ እንግዲህ ምንም ማድረግ አይቻልም አዲሱን የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” አልበም ለ7 ቀናት በተከታታይ በጽሞና አዳምጡት። ፍቱን መድሀኒት ነው፡ ቀኑ በዛ እንዳትሉ ያው ግጥሙ ቅኔ አለው፤ ይበልጥ እያደር ይደምቃል …። ሌላው ደግሞ ይሄ ምንድን ነው የምትሉት … “ዘፋኝ መንግስተ-ሰማያትን አይወርስም“ ምናምን እያልሽ በምላስሽ፡ ነገር ግን በልብሽ ምድር ላይ ለአንድ ደቂቃ እንኳ ማቆም የማያስችል ሴራ የምትበጥሽውን አልሰማሽም።

ዖና አርጌው ታሪኬን

(አምሳሉ ከንዱ – ፒ.ኤች.ዲ)

 

Share.

About Author

Leave A Reply