የደቡብ ክልል፡ ውስብስቡ የዐብይ ፈተና

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ፥ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት የወሰዳቸው የፖለቲካ ማሻሻያ እርምጃዎች በብዙኃን ዘንድ በአዎንታ መወሰዳቸው የሚታወቅ ነው።

ይሁንና በዚያው ልክ ከአንድ ዓመት የማይሻገር ዕድሜ ያስቆጠረውን እና አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች አሁንም ጉልበቱ አልጠናም የሚሉትን አስተዳደር የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብቅ ብቅ ማለት፥ ብሎም መገንገን መያዛቸውም ማስተዋል ይቻላል።

የፖለቲካ እና የፀጥታ ፈተናዎችን ብቻ ብንመለከት እንኳ ገና ከማለዳው ጀምሮ ከትግራይ ክልል የፖለቲካ ልኂቃን የተሰነዘረውን ተቃውሞ፥ በምዕራብ ኦሮሚያ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂ ቡድኖች የገጠመውን እምቢታ፥ የተፈናቃዮችን በሚሊዮኖች መቆጠር፥ የአዲስ አበባን አጨቃጫቂነት መካረር፥ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል ሲሰክን የማይታየውን ፍጥጫ ማንሳት ይቻላል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የሚስተዋሉ የፖለቲካ ትብታቦች ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና አስተዳደራቸውን ከሚፈታተኑ እጅግ ውስብስብ ችግሮች መካከል የሚመደቡ ናቸው። እንቆቅልሾቹን ለመፍታት አዳጋች የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ።

ከአንድ ወደብዙ ክልሎች የደቡብ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወደ110 ሺህ ገደማ ካሬ ኪሎሜትር መሬት ላይ ያረፈ ከትልልቆቹ የኢትዮጵያ ክልላዊ መስተዳድሮች አንዱ ነው።

በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ በሺህዎች እስከሚቆጠሩ ተወላጆች ያሏቸው ከሃምሳ በላይ ብሄሮችን በውስጥ የያዘው ይህ ክልል ከምሥረታውም ጀምሮ በአወቃቀሩ ላይ ጥያቄዎች ሲነሱበት ቆይቷል።

አነስተኛ ቁጥር ያላቸው እና የአገሪቱን ትልቁ የአስተዳደር አሃድ፥ የክልል መስተዳደር የያዙ ብሔሮች የመኖራቸው ሃቅ በደቡብ ብሔር፥ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ከተሰባሰቡ ብሔሮች መካከል የሕዝብ ብዛታቸው ከፍ ያሉ ሆኖም በአንፃሩ ዝቅ ባለው የዞን አስተዳደር ብቻ የተወሰኑ ብሔሮች ከመኖራቸው ጋር እየተመሳከረ የአመክንዮ ጥያቄ ይሰነዘርበታል።

በክልሉ የሚገኙ ብሔሮችም በተለይ በአንዳንዶቹ በራሳቸው ክልል የመተዳደር ፍላጎትን በአንድ ወይንም በሌላ መልኩ ማቅረባቸው አዲስ ክስተት አይደለም።

ይህ ፍላጎት በተለየ ጠንከሮ የሚስተዋለው በሲዳማ ብሔር ሲሆን ባለፉት ጥቂት ወራትም የጥያቄው ግፊት የበረታ ይመስላል።

ሲዳማን ተከትለው በክልሉ የሚገኙ ከአምስት በላይ ብሔሮች በዞን መስተዳደሮቻቸው በኩል የክልል እንሁን ፍላጎቶች መኖራቸውን አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ እስካሁን ከክልሉ መንግሥት የክልል መሆን ያለመሆንን ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ ፍቱልን በሚል የደረሳቸው አንድ ጥያቄ ብቻ ሲሆን እርሱም የሲዳማ ብሔርን የሚመለከት እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሲዳማ የክልል የመሆን ጥያቄ በአፋጣኝ ያለመስተናገዱ ቅር ያሰኛቸው የብሔሩ ተወላጆች በክልሉ መናገሻ በሐዋሳ ከተማ ትዕይንተ ሕዝብ ያካሄዱ ሲሆን፥ ተቃውሞና የሥራ ማቆም አድማ በተለያዩ ጊዜያት ተጠተው ነበር::

የምርጫ ቦርድ ሊቀ መንበር ብርቱካን ግን የቦርዱ አባላት እስካሁን ያለመሟላት ጥያቄውን ለማስተናገድ እንቅፋት እንደሆነባቸው ይገልፃሉ።

የሲዳማ ብሔር በሕዝበ ውሳኔ ክልል የመሆን ጥያቄን ቢቀበለውና ይህም ሒደቱን ተከትሎ ቢስተናገድ፥ በሌሎች ብሔሮች የታዩ ፍላጎቶች ይበልጥ ጠንክረው እንደሚወጡ መገመት አይገድም። ይህም የክልሉን ወደበርካታ ክልሎች የመከፋፈል ዕጣ እንዲገጥመው ያደርጋል።

ጥያቄዎቹ እንዲመሱ የሚፈለግበት ፍጥነት እና ጥያቄዎቹን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አስተዳደራዊ የራስ ምታቶች ለጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተዳደር ፈታኝ ይሆናሉ።

ቢያንስ እስከቀጣዩ ምርጫ ድረስ ጥያቄዎቹን እያንከባለሉ የመቆየት ፍላጎት በመንግሥት በኩል ቢኖር እንኳ፥ በተለይ ከሲዳማ ጥያቄ አቅራቢዎች በኩል በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ያለው ፍላጎት ከዕለት ወደዕለት ሲበረታ መስተዋሉ እረፍት የሚሰጥ አይመስልም።

እኩል የመታየት ጥያቄዎች በክልሉ በርካታ ብሔሮች ቢገኙም በአስተዳድራዊ መዋቅሮች እና ውሳኔዎች ሁሉም ብሔሮች እኩል ይታያሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው የቢቢሲ ዘጋቢ በሐዋሳ ከተማ በተገኘበት ወቅት የገለፁለት አስተያየት ሰጭዎች አሉ።

በተለይም የሕዝብ ቁጥሮቻቸው አነስተኛ የሆኑ ብሔሮች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን ያህል ከግምት ውስጥ እንደማይገቡ እንደሚያምኑ ይናገራሉ እነዚህ አስተያየት ሰጭዎች።

ክልሉን ከምስረታው አንስቶ በርዕሰ መስተዳድርነት የመሩት ከሁለቱ ትልልቅ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች፥ ከሲዳማ እና በወላይታ ብሔሮች ተወላጆች መሆናቸውን ለዚህ በአስረጂነት ይጠቅሳሉ።

(አባተ ኪሾ፥ ኃይለማርያም ደሳለኝ፥ ሽፈራው ሽጉጤ እና ደሴ ዳልኬ ከዚህ ቀደም ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት የመሩ ባለስልጣናት ሲሆኑ አሁን ስልጣን ላይ ያሉት ደግሞ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ናቸው።)

ይህንን አስመልክተው አስተያየታቸውን ያጋሩን የኮንሶ ብሔር ተወላጅ ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የክልሉን መዲና ከፖለቲካ አጋሮቻቸው ጋርም ሆነ ከጎብኚ የውጭ አገር መሪዎች ጋር በተደጋጋሚ ቢመላለሱባትም፥ በቆይታቸው ወቅት የክልሉን ኅብረ ብሔራዊነት የሚያንፀባርቁ ትዕምርታዊም ሆነ ተግባራዊ እርምጃዎችን ሲወስዱ አላየሁም ሲሉ ይወቅሳሉ።

ግጭቶች እና መፈናቀል

በአገሪቱ በጥቅሉ በተለያዩ ብሔሮች መካከል የሚነሱ ውጥረቶች እና ግጭቶች ባለፈው ዓመት በርከት ብለው ተስተውለዋል።

በአጠቃላይ በአገሪቷ ያሉ ተፈናቃዮች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን ሲልቅ እርዳታ ፈላጊዎች ደግሞ ከስምንት ሚሊዮንም በላይ ናቸው።

የደቡብ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልም ይሄንን ገፈት ከቀመሱ ክልሎች አንዱ ነው።

ባለፈው ሰኔ በሐዋሳ ከተማ የተከሰተው እና ሞትን እንዲሁም የንብረት ውድመትን ያስከተለው ግጭት የብሄር መልክ ነበረው።

የግጭቱ ዳፋም እስካሁን የዘለቀ ይመስላል።

ኦሮሚያን በሚያዋስኑ የጌዲዮ ዞን አካባቢዎች ግጭት እና ስጋት ለአያሌ ሺህ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሲሆን፥ ክስተቱ የሚገባውን ያህል አትኩሮት አላገኘም ሲሉ ነቀፌታ የሚሰንዝሩ በርካቶች ናቸው።

የዞኑ አስተዳደር በኩሉ በዚህ ሳምንት ከመቶ ሰባ ሺህ ለሚልቁ ተፈናቃዮች እርዳታ እያደረሰ እንደሆነ ገልጿል።

የግጭት ሰለባዎች እና ተፈናቃዮች የሌሎችም ክልሎች ችግሮች ቢሆኑም በተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተጠመደውን የደቡብ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልን ለችግሩ የሚገባውን ያህል አትኩሮት ከመስጠት እንዳያግደው ስጋት እንዳላቸው ለቢቢሲ የገለፁ የክልሉ ነዋሪዎች አሉ።

የተለያዩ የክልሉን ብሔሮች ያካተተው ገዥው ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የበዙትን ፍላጎቶች ለማስታረቅና ለማመቻቸመች፥ የበረቱትን ጥያቄዎች የአንገብጋቢነት ቅደም ተከተል ለማስያዝ እና በዚያውም ልክ ለማስተናገድ የሚያበቃ ብቃት እንዲሁም የአመለካከት አብሮነት አለው ወይ? የሚልው አብዩ ጥያቄ ነው። የፈተናዎቹ መዘዝ ግን በክልሉ የሚወሰን አይሆንም።

ቢቢሲ

Share.

About Author

Leave A Reply