የጃዋር መሀመድ አዲሱ መንገድ ይበልጥ አደገኛ ነው!

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሰሞኑን በስሜት ተዋክቦ ከወጣበት የኮንደሚኒየም “ኬኛ” ሰላማዊ ሰልፍ በኋላ በደረሰበት ፖለቲካዊ ሽንፈት ለማገገም ወደ ሀገሩ አሜሪካ ካፈገፈገ በኋላ እዚያው ሆኖ በሚዘውረው የቴሌቪዥን ጣቢያው የቀጥታ ስርጭት ላይ በመቅረብ አዲስ መፍትሄ አለኝ እያለ ነው።

በሀገር ውስጥ ለታዩት ውንቅጥና ወጣቱን አርፎ እንዳይማርና እንዳያመርት በሚያደርጉ ውዥንብራዊ ትንታኔው በዲያስፖራው ተጠያቂ መደረጉ ያብገበገበው ጀዋር መሀመድ “ኢትዮጵያ አሁን ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እንድትወጣ ሶስቱ ብሄሮች የግድ መነጋገር አለባቸው ሲል ከነበረበት “አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት” ተሻግሮ ሄዷል።

ጃዋር ሶስቱ ብሄር ያላቸውን ኦሮሞ፣ አማራና ትግሬን በስም በመጥቀስ “እነዚህ ናቸው የሀገሪቱን ችግር በጋራ መፍታት የሚችሉት” ሲል ብቸኛ መፍትሄ ነው በማለት ተንትኗል። ይህ አስተሳሰብ ያለብን የብሄር ተኮር ፖለቲካ የበለጠ በማክረርና የሀገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ በሶስት ብሄሮች እንዲወጠር በማድረግ ይበልጥ ችግር ፈጣሪ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

ይህ ብቻም ሳይሆን ከሰማንያ በላይ ብሄር ያሰባሰበችን ሀገር የፖለቲካ ችግሯን መፍታት የሚችሉት ሶስቱ ናቸው በማለት ሌሎችን በማግለል የተለመደውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተመጽዋች ለማድረግ የታለመና ፈጽሞ ሊሰራ የማይችል ነውጠኛ የፖለቲካ ትንታኔ ነው። ኢትዮጵያ በዘመኗ በብሄሮቿ የተነሳ የገጠማት ችግር የለም። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ብዙዎቹ ብሄሮች ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ በበጎም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ አስተዋጾ ማድረጋቸውን መካድ አይቻልም።

ይሁንና ይህንን ሀቅ በመካድ በብሄር ፖለቲካ ለሀያ ሰባት አመታት የበሰበሰውን የዚህችን ሀገር ፖለቲካ የበለጠ በማበስበስ እና ለሶስት ብሄሮች ለይቶ ቅርጫ በመስጠት የሚመጣ ምንም አይነት መፍትሄ የለም። አይን ያለው፣ ማስተዋል የሚችልና ሀላፊነት የሚሰማው ማንኛውም ቅን ዜጋ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ በሀገራችን የተከሰቱት የህዝብ መፈናቀል፣ ግድያዎች፣ እንዲሁም የፖለቲካ ምስቅልቅል በብሄር ቡድኖች የተፈጠሩ መሆናቸውን ይረዳል። በመሆኑም የብሄር ፖለቲካን የበለጠ በማጦዝ ለሶስት ብሄሮች በሚሰጥ የፖለቲካ ቅርጫ የሚመጣ መፍትሄ እንደማይኖርም ይገነዘባል።

በመሆኑም የፖለቲካ ሳይንቲስት እንደሆኑ ደጋግመው የሚነግሩን አቶ ጃዋር መሀመድ የሀገራችንን ፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ ቅን ልቦና ካላቸው ወደ ባሰ ውጥንቅጥ ውስጥ የሚከተንን አዲሱን ፋሺስታዊ እቅድ ቢመረምሩት ተገቢ ነው እንላለን። ቃሊቲ ፕሬስ

Share.

About Author

Leave A Reply