የጄኔራል ሰዓረ መኮንን የሕይወት ታሪክ::

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2011ዓ.ም (አብመድ) ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ከአስር አለቃ መኮንን ይመር እና ከወይዘሮ ሕይወት ይህደጎ በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገዳ ጽምብላ ወረዳ እንዳባጉና ከተማ 1954 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በእንዳባጉና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1-6ኛ ክፍል እንዲሁም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሽሬ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ ነገር ግን በመማር ላይ እያሉ የደርግን ሥርዓት ለመታገል በህወኃት የሚመራው የትጥቅ ትግል እየተካሄደ ስለነበር ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በ1969 ዓ.ም የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡ በጉንደት ስልጠና ማዕከል ስልጠናቸውን አጠናቅቀው እስከ ታኅሳስ 1971 ዓ.ም ድረስ በህወኃት 91ኛ እና 73ኛ ሻምበሎች በተዋጊነት እና በጓድ መሪነት አገልግለዋል፡፡

ከታኅሳስ 1971 እስከ ታኅሳስ 1972ዓ.ም ደግሞ በህውኃት የጋንታ አመራር ሆነው ታግለዋል፡፡ ከታኅሳስ 1972 እስከ ግንቦት 1973 ዓ.ም 537ኛ እና የ753ኛ ሻለቃዎች የሻምበል መሪ ነበሩ፡፡ ከ1974 እስከ 1975 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በብርጌድ 43 ውስጥ የሻለቃ መሪ በመሆን በኤርትራ ምድር የደርግ ሠራዊት ያካሄደውን የቀይ ኮኮብ ዘመቻ መክተዋል፡፡

ከ1974ዓ.ም እስከ 1977ዓ.ም በብርጌድ 43 እና 45 የሻለቃ አዛዥ በመሆን እና በ1978ዓ.ም የብርጌድ 77 ምክትል ብርጌድ አዛዥ በመሆን በራያ አካባቢ ደርግ ሲያካሂዳቸው የነበሩ ተደጋጋሚ ዘመቻዎችን መክተዋል፡፡

ጥር 30 ቀን 1978 ዓ.ም ከመቀሌ ከተማ የደርግ ወህኒ ቤት 1ሺህ 300 እስረኞች ነፃ ባወጣው ታሪካዊ ‹የአጋዚ ኦፕሬሽን› የብርጌድ ምክትል አዛዥ በመሆን ሙሉ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡
ከ1979 እስከ 1981 ዓ.ም የብርጌድ 70 አዛዥ ነበሩ፤ በ1980 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ በተካሄደው ተከታታይ ‹‹ዘመቻ ብሩህ›› ከምንጉላት፣ ስንቃጣ፣ ውቅሮ፣ ገለበዳ ድረስ ‹‹ዘመቻ ድልድል›› በሚል ስያሜ የሚታወቀውን የደርግ 17ኛ ክፍለ ጦር ደምስሰዋል፤ በዚህም አክሱም፣ ዓድዋ፣ ሽሬ፣ ከተሞችን ነፃ አውጥተዋል፡፡ ከኮረም እስከ አምባላጄ የደርግን 1ኛ ክፍለ ጦር ለመደምሰስ በተደረጉ ውጊያዎችም በብቃት ብርጊዳቸውን በመምራት ለድል ያበቁ ታጋይ ነበሩ፡፡

ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ከመስከረም 1981ዓ.ም እስከ 1983ዓ.ም ግንቦት ወር የደርግ ሥርዓት እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ የአውሮራ ክፍለ ጦር አዛዥ ነበሩ፤ ከመስከረም 1981 ዓ.ም እስከ የካቲት 12 ቀን 1981ዓ.ም በሽሬ እና አካባቢው መሽጎ የነበረውን የደርግ 604ኛ ኮር በተከታታይ ውጊያዎች አዳክሞ ለመደምሰስ በተደረጉ ውጊያዎች እንዲሁም የደርግ ሠራዊት አብዛኛውን የትግራይ አካባቢዎች ለቅቆ ከወጣ በኋላ ‹‹ሠላም በትግል ዘመቻ›› ተብሎ በሚጠራው ከማይጨው እስከ ጎብዬ የደርግን 605ኛ ኮር ለመደምሰሰስ በተደረገው ዘመቻ ክፍለ ጦራቸውን በብቃት በመምራት ወታደራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
ከመስከረም እስከ ጥር 1982 ዓ.ም ድረስ ‹‹ፋና ኢህአዴግ›› ተብሎ በተሰየመው ዘመቻ ደቡብ ወሎን፣ ከፊል ሰሜን ሸዋን እና ደቡብ ጎንደርን ነፃ ያወጣውን ዘመቻ ክፍለ ጦራቸውን በብቃት መርተው ለድል አብቅተዋል፡፡

በ1982ዓ.ም መጨረሻ ደርግ ሲመካበት የነበረውን 3ኛ ክፍለ ጦር ለማዳከም መራኛ ላይ በተደረገው ውጊያም በከፍተኛ ብቃት መርተዋል፡፡

ከ1983ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ‹‹ዘመቻ ዋለልኝ›› በሚል ደሴ እና ከፊል ሰሜን ሸዋን ነፃ ለማውጣት በተደረገው ውጊያ እና ‹‹ዘመቻ ወጋገን›› በሚል የደርግን ሥርዓት ለመደምሰስ በተደረገው ውጊያ በድል እየታጀቡ ጦራቸውን መርተው እስከ ኦጋዴን ድረስ መዝለቅ ችለዋል፡፡

ጀኔራል ሰዓረ መኮንን ከደርግ ውድቀት በኋላም በሽግግር መንግሥቱ የሀገራዊ ሠራዊት አደረጃጀት የምሥራቅ ዕዝ ዘመቻ ኃላፊ በመሆን እና ከየካቲት 1987ዓ.ም ጀምሮ በኢፌዴሪ ሀገር አቀፍ የመከላከያ ሠራዊት ምሥረታ የምሥራቅ ዕዝ ዘመቻ ኃላፊ በመሆን ተልዕኳቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡

በግንት ወር 1990ዓ.ም የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ደግሞ የቡሬ ግንባር አዛዥ በመሆን የሀገሪቱን ዳር ድንበር አስከብረዋል፡፡ በየካቲት 1991ዓ.ም የኤርትራን ሠራዊት ከባድመ ባስወጣው ‹‹ዘመቻ ፀሐይ ግባት›› የባድመ ግንባር ግራ ክንፍ አዛዥ በመሆን ዘመቻው ለፍጻሜ እንዲበቃ አድርገዋል፡፡
ጀኔራል ሰዓረ መኮንን ከ1992 -1994 ዓ.ም የ107ኛ ኮር ዋና አዛዥ፣ ከ1994 -1997 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የሰሜን ግንባር ዋና አዛዥ፣ ከ1997 እስከ 2006ዓ.ም ድረስ የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ በመሆን ሀገራቸውን በቅንነት እና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡

በትጥቅ ትግሉ እና በመደበኛ ሠራዊት ግንባታ ያካበቱትን ዕውቀት እና ልምድ ተጠቅመው ሠራዊቱን በወታደራዊ ጥበብ እንዲያጎለብቱ ከ2006 – 2010 ዓ.ም የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ለረጅም ዓመታት የመከላከያ ካውንስል አባል በመሆን ሠራዊቱ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ መወጣት እንዲችል ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም የሴኩሪቲ ካውንስል አባል በመሆን ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠር የበኩላቸውን አበርክተዋል፡፡
ጀኔራ ሰዓረ በነበራቸው የአመራር ብቃት ከመጋቢት – ግንቦት 2010ዓ.ም ድረስ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም እና ከግንቦት 2010ዓ.ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ድረስ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆነው ኢትዮጵያን አገልግለዋል፡፡

ጀኔራል ሰዓር ኢታማዦር ሹም የሆኑበት ወቅት ፈታኝና የፀጥታ መደፍረስ በየአካባቢው የነበረበት ቢሆንም ከፀጥታ ማስከበሩ ጎን ለጎን ሠራዊቱን በተቋማዊ ለውጥ በመምራትና በማደራጀት ላይ ነበሩ፡፡

በነበራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በ1988 ዓ.ም በሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረግ ጀምረው በ2010 ዓ.ም የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ ደርሰዋል፡፡ በነበራቸው የትጥቅ ትግል ተሳትፎ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳልያን ጨምሮ በርካታ ኒሻኖችን ከኢፌዴሪ መንግሥት ማግኘታቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ጄኔራል ሰዓረ ባላቸው ከፍተኛ የመማርና ራስን በትምህርት የማሳደግ ፍላጎት በ‹ማኔጅመንት› የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በ‹ትራንስፎርሜሽን› እና ‹ሊደርሽፕ› ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪኒዊች ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ጀኔራል ሰዓረ ባላቸው ከፍተኛ የማንበብ ልምድ የሚታወቁና ለሌሎችም አርዓያ የነበሩ መሪ ናቸው፡፡

ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚያዩ፣ ሁል ጊዜም ራሳቸውን እንደ ተራ ወታደር የሚቆጥሩ፣ ከጓደኞቻቸው እና እኩያዎቻቸው ጋርም ተግባቢ እና ሳቂታ ነበሩ፡፡ ከውጊያ በፊት፣ በውጊያ ጊዜ እና ከውጊያ በኋላም የተጋጣሚን ኃይል ሁኔታ በውል የሚረዱ በመሆኑ በአሸናፊነት የሚታወቁ የጦር መሪ እንዳደረጋቸውም ይነገርላቸዋል፤ ‹‹አባ እሳቱ›› በሚል ቅጥያም ይጠሩ ነበር፡፡ ወታደሮቻቸውን እንደራሳቸው አድርገው በመቅረጽም በጀግንነታቸው የሚታወቁ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ጀኔራል ሰዓረ በጥቃቅን ችግሮች የማይንበረከኩ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በድል አድራጊነት የተወጡ፣ የተዋጣላቸው ተማሪ እና መሪ እንደነበሩ ግለ ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡ በመሪዎች ዘንድ ፍጹም ተወዳጅ እና ‹‹የአስቸጋሪ ሁኔታ ቀያሪ›› ተብለው የተመረጡ እና ሲሰማሩ በነበሩበት ሕዝባዊ እና መንግሥታዊ ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የሚታወቁም ነበሩ፡፡

ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም አመሻሽ በአማራ ክልል መንግሥት የተደረገውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለማክሸፍ እየሠሩ ባለበት በመኖሪያ ቤታቸው በጠባቂያቸው መገደላቸውን መንግሥት አስታውቋል፡፡ ጀኔራል ሰዓረ መኮንን ባለትዳር እና የአንድ ወንድ እና አንድ ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
በ57 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው ጀኔራል ሰዓረ መኮንን የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ሰኔ 19 ቀን 2011ዓ.ም በመቀሌ ይከናወናል፤ አስከሬናቸው ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የጦር መኮንኖች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ሽኝት ተደርጎለታል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply