የገዛህኝ ነብሮ ግድያ ሆን ተብሎ የታቀደ ነው ተባለ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢትዮጵያውያን የመብት ተሟጋች ገዛህኝ ገብረመስቀል ነብሮ ግድያ ሆን ተብሎ የታቀደ መሆኑን አንድ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ገለጸ።

ሳምንታዊው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ሜይል ኤንድ ዘጋርዲያን በዛሬው እትሙ ግድያው ከዘረፋ ጋር ያልተያያዘ መሆኑን የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ዝርዝር ሪፖርት አቅርቧል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጥር ሚያዚያ 21/2018 ከቀትር በኋላ 11 ሰአት ላይ በቀን ብርሃን፣ሕዝብ በሚተራመስበት ጎዳና ያምፔራ በተባለ ምግብ ቤት ደጃፍ ነበር በገዛህኝ ገብረመስቀል ላይ ግድያ የተፈጸመው።

ግድያውን የፈጸመው ግለሰብም ወጣትም ቀጭን እንደሆነ ለሜይል ኤንድ ጋርዲያን ምስክርነቱን የሰጠው ግለሰብ እንደተናገረው ወጣቱ በፍጥነት ስለተሰወረ መልኩንም ሆነ ልብሱን መለየት አልቻለም።

ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ፖሊሶች በስፍራው ለመድረስ 40 ደቂቃ እንደፈጀባቸው እንዲሁም አስከሬኑን ለማንሳት ደግሞ ተጨማሪ 2 ሰአት እንደወሰደባቸው ሜይል ኤንድ ጋርዲያን በዘገባው ገልጿል።

ግድያው የታቀደ ስለመሆኑም አንድ የፖሊስ ባልደረባን ጠቅሶ ዛግቧል። “ገዳዩ የሚፈጽመውን በደንብ ያውቃል፣የታለመ ግድያ ነው”ሲል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የፖሊስ ባልደረባ ከአደጋው ስፍራ ለጋዜጣው ገልጿል።

ፓስካል የተባለውን የአይን ምስክር ጨምሮ ሌሎችም ተጨማሪ ምስክሮች ግድያው ከዘረፋ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ለጋዜጣው ገልጸዋል።

የኪስ ቦርሳውና የእጅ ቦርሳው እንዲሁም የያዛቸው ሁለት ዘመናዊ የእጅ ስልኮችም አለመነካታቸው በአስረጅነት ቀርቧል።

በእጁ የነበረው 15ሺ የደቡብ አፍሪካ ራንድ (በኢትዮጵያ ብር 190 ሺ ብር) አለመነካቱም በዘገባው ተመልክቷል።

አክቲቪስት ገዛህኝ ገብረመስቀል ከመገደሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዛጋጀው ፕሮግራም ላይ እንዳይገባ መከልከሉና በኋላም የማስፈራሪያ መልዕክት እንደደረሰው ጓደኞቹን በመጥቀስ ሜይል ኤንድ ጋርዲያን ዘግቧል።

በማግስቱም መገደሉን አክሏል። በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሊቀመንበር አቶ ታምሩ አበበ ይህ ተራ ግድያ አይደልም ብለዋል።

ከመቶ ፐርሰንት በላይ ተጠያቂው የሕወሃት አገዛዝ እንደሆነም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ ለጋዜጣው በጽሁፍ በሰጠው ምላሽ እንዳይገባ አልከለከልነውም ገብቶ በራሱ ፈቃድ ነው የወጣው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ሆኖም የደቡብ አፍሪካው ፖሊስ ምስክርነት፣ የአይን እማኞች ቃልና የጋዜጣው ዝርዝር ሪፖርት ይበልጥ በሕወሃት አገዛዝ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ሆነው ተገኝተዋል።

ላለፉት 20 አመታት በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የነበረው ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት አክቲቪስት ገዛህን ገብረመስቀል ነብሮ በመብት ተሟጋችነቱና ለኢትዮጵያውያን በሚያደርገው ድጋፍ ይታወቃል።

የ12 አመት ልጁ ሜላት ገዛህኝ እደተናገረችውና የደቡብ አፍሪካው ጋዜጣ እንደተጠቀሰው አባቷ ትክክለኛ ስራ እየሰራ ነበር

“አባቴ ትክክለኛ ስራ ነበር የሚሰራው፣ለነጻነት ታግሏል፣ቃሉም እውነት ነበር፣ለሁሉም ሲል መስዋዕትነት ከፍሏል።ማን እንደሆነ ለማያውቁት ጭምር”ብላለች የ12 አመቷ ታዳጊ ሜላት ገዛህኝ።

Share.

About Author

Leave A Reply