የግዕዝ ጉባኤ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ፡፡

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ሰብ ትምህርት ዘርፍ በግዕዝ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት የመጀመሪያው የግዕዝ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ‹‹ዩኒቨርሲቲው ብቸኛ በሆነባቸው መሬት አስተዳደር እና ማሪታይም አካዳሚ እንደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃው ከፍ ብሏል፤ የግዕዝ ትምህርት ክፍልን አጠናክረን ብንቀጥል ደግሞ ከዚህ በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንችላለን›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ በዩኒቨርስቲው የግዕዝ ቋንቋ በትምህርትነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሀገራዊ አደራም ጭምር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በጉባኤው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ ግዕዝ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ኅልውና ንግግር አድርገዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትልቁ ድርሻ ዕውቀትን ማሻገር በመሆኑ ትምህርት ክፍሉ የብዙ ዕውቀቶች ሚስጥር የሆነውን ግዕዝ ማሰልጠን፣ መሰብሰብ፣ መተንተን እና ጥናቶችን አጠናቅሮ መያዝ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አምሳሉ ተፈራ በበኩላቸው ግዕዝ በዘመናዊ ትምህርት ለምንና እንዴት መሰጠት አለበት በሚለው ሐሳብ መነሻነት ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

በጽሑፋቸውም በቋንቋው ዙሪያ እንደ ተግዳሮት ለሚነሱ ጉዳዮች ግዕዝ የሞተ ቋንቋ ስለሆነ አይሠራበትም፣ በሙያው የሠለጠኑ ምሁራን የሉንም፤ ግዕዝን በሥርዓተ ትምህርት ለማስገባት በቂ ሰዓት የለም በሚሉት ዙሪያ የመፍትሔ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡
በዐውደ ርዕዩም ከፊደል መቁጠር እስከ ቅኔ ሲሰጥበት የነበረበት ሁኔታ፣ የግዕዝ ቅኔ ትምህርት የመማር ማስተማሩ ሂደት በተባዕታይ መምህር እና በአንስታይ መሪ እመቤት እንዴት እንደሚሰጥ እና የብራና አዘገጃጀት፣ ከቆዳና ቀለም ዝግጅት እስከ ድጉሳት ድረስ ያለውን ሥራ በተግባር ታይቶበታል፡፡

ምንጭ፡- የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

Share.

About Author

Leave A Reply