የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ለአዲስ አበባ ህዝብ ስድብ ነው! (ያሬድ ጥበቡ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማንና የኦሮሚያን ክልል ወሰኖች ጉዳይ ለማጥናት ባዋቀረው አዲስ ባለ ስምንት አባላት ኮሚቴ ውስጥ አምስት ኦሮሞዎችና ሦስት ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች ያሉበት አካል አቋቁሟል። ይህ ለአዲስ አበባ ህዝብ ስድብ ነው። ዓይኑ ላይ የመትፋትን ይህል ይቆጠራል።

እንዴት ነው የኦሮሞን ባለቤትነት ለማስፈፀም የተጎለተ የአዲስአበባ ከንቲባና ግብረአበሮቹ አዲስአበባን ወክለው ከመሰል ካድሬ ጓደኞቻቸው ከሆኑ የኦዴፓ አባላት ጋር ሊደራደሩ የሚችሉት? እንዴትስ ነው የሃገር አስተዳደር፣ የደህንነት ወዘተ ብዙ ሥራዎችን ጠቅልላ የያዘችና በኦዴፓ ወገንተኝነቷ የምትታማዋን ሙፍሪያትን ከፌዴራል መንግስቱ የምትወከለው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ማሳየት ከፈለጉ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ግልፅ የሆነ አቋም ያላቸውን ምክትላቸውን አቶ ደመቀ መኮንንን በሰብሳቢነት መወከል በተገባቸው ነበር። የወሰን ኮሚቴው መመስረት ካለበትም አዴፓ የሚመለከተው መሆኑንና መወከልም እንዳለበት ውሳኔ ማስተላለፍ ይኖርበታል።

ይበልጥ ግን አዲስአበባ ምርጫ አድርጋ የራሷ ከንቲባና ከአብራኳ የወጡ ልጆቿ የሚመክሩበት ምክርቤት እስክታገኝ ድረስ ይህ የወሰን ጉዳይ መነሳት የለበትም። ኦዴፓ የኦሮሚያ ክልንንም አዲስ አበባንም ወክሎ እርስ በርሱ የመወሰን ሥልጣን ሊኖረው አይገባም። ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን “ምን ትሆናላችሁ” ትዕቢት የአዲስ አበባ ህዝብ በዝምታ ማሳለፍ የለበትም። በሰላማዊ ሰልፎችና በቤት ውስጥ ቆይታ አድማዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያደርጓቸው የኦሮሞ ብሄርተኛ ተግባራት እንዲቆጠቡ ማድረግ ተገቢ እየሆነ መጥቷል። ዶክተር አቢይ በኢትዮጵያ ፍቅር ቃላት እያስተኙን፣ በጠባብ ኦሮሞ ብሄርተኛ ተግባራት እያቆሰሉን መቀጠል አይችሉም።

አካፋን አካፋ ላለማለት የብዙ ወራት ትእግስትን ብናሳይም ያንን እንደ ጅልነት የቆጠሩብን ይመስላልና፣ ለህልውናው የሚሰንፍ ህዝብ እንደሌለ ማሳያው ወቅት የደረሰ ይመስለኛል። የአዲስ አበባ ህዝብ እጅግ ሰላማዊ የሆነውን የእምቢተኝነት ድምፁን ማሰሚያው ወቅት አሁን ነው። ተቃዋሚ ነን የሚሉትም ሃይሎች ከአዲስ አበባ ጎን ይሰለፉ እንደሆን የሚፈተኑበት ወቅት አሁን ነው።

ራሱን ያከሰመውን ቲም ለማ በመተካት የሚሠራ የሽግግር መንግስት እንዲመሠረት የአዲስ አበባን አደባባዮች ሞልተን እጅግ ሰላማዊ በሆነ የሃገር ፍቅር ትከሻ ለትከሻ የምንቆምበት ወቅት ዛሬ ነው። አዲስ ምከር! አዲስ ለመብትህ ቁም! አዲስ ከእንቅልፍህ ንቃ! የሽግግር መንግስት ይቋቋም ብለህ በየአደባባዩ፣ በየሰፈሩ ድምፅህን አሰማ! ትናንት በኦሮሚያ ክልል ለቄሮ የተፈቀዱ የሰላማዊ ሰልፍ መብቶች ያንተም መሆናቸውን ለደቂቃም አትጠራጠር። መብትህን በእጅህ አስገባ! እምቢ ለዘረኝነት በል። የሽግግር መንግሥት ዛሬ ብለህ በየአደባባዩ ትመም!

Share.

About Author

Leave A Reply