የጡት ቆረጣ ነገር (በእውቀቱ ስዩም)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በአርሲ ዘመቻ፣ የምኒልክ ወታደሮች፣ የሴቶችን ጡት ቆርጠዋል የሚለውን ክስ፣ ብዙ በራዥ ብሔርተኛ ጸሐፊዎች ባንድ ድምጽ የተቀበሉት ቢሆንም፣ እንደ ተስፋዬ ገብረአብ ያህል ሲኒማዊ ምስል ሰጥቶ ያቀረበው የለም።

ተስፋዬ ገ/ አብ አንድ ገጸ-ባሕርይውን እንዲህ ያሰኘዋል:- “(ነፍጠኞች) የሴቶቻችንን ጡት እኛ ከበግ ላይ ጸጉር እንደምንሸልተው እንዲያ ነበር የሚቆርጡት። እነዚህ ሰዎች በግ ሲያርዱ በስመአብ ብለው ይጀምራሉ። የሴቶቻችንን ጡት ሲቆርጡ ግን በስመአብ አይሉም። ግን ሃይማኖት አለን ይሉናል።”የበደሉ ሴቶችን ጡት በመቁረጥ መቅጣት በታሪክ ውስጥ በቀዳሚነት ተጠቅሶ የምናገኘው በአክሱም ነገሥታት ዜና መዋእል ውስጥ ነው። ዮዲት የተባለች የንጉሥ ዘር የሆነች አንዲት ሴት ትቸገርና ወደ አክሱም ትወርዳለች።

በዚያም በሴተኛ አዳሪነት ትሰማራለች። በዚህ ዐይነት ስትኖር ከአክሱም ጽዮን ዲያቆናት አንዱ በፍቅሯ ይነደፋል። የግብረሥጋ ጥያቄ ሲያቀርብላት እምቢ ትላለች። በፍትወት የነደደው ዲያቆን እሷን ለመማረክ ከአክሱም ጽዮን ቤተክርስትያን የወርቅ መጋረጃ ቀድዶ ያመጣላታል። በዚህ የተቆጡት የአክሱም ጽዮን ካህናት ዮዲትን አይቀጡ ቅጣት እንድትቀጣ ይፈርዱባታል። ቅጣቱ ምን ነበር? “ወፈትሁ

ፍትሐ እንዘ ይብሉ ይምትሩ አጥባእቲሃ ዘየማን ወይስድድዋ እምሃገር ወገብሩ ከማሁ” ይላል ታሪክ ነገስት። ትርጉሙ፣ “ቀኝ ጡቷን ቆርጠው ካገር እንዲያባርሯት ፈረዱባት። እንደፈረዱትም አደረጉ” ማለት ነው።

ዮዲት ቁስሏ ከዳነላት በኋላ ለብቀላ በአብያተክርስትያናት ላይ ውድመት እንዳደረሰች በሰፊው ይተርካል። ትረካው እውነት ይሁን አይሁን ማረጋገጥ ከባድ ነው። ይሁን እንጂ የጡት ቆረጣ ቅጣት የማይታሰብ እንዳልነበረ ይህ ትረካ ያስረዳል።

“ለኔ የማይገዛ ካለ ወንዱን ቁላውን ሴቱን ጡቱን እሰልባለሁ” የሚለው ዐዋጅ  በነገሥታት እና ዘመን ባስነሳቸው አምባገነኖች ይነገር ነበር። አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ፤ የየጁው ኦሮሞ ጉግሳ እና የሸዋው መርድ አዝማች ስብስትያኖስ ጡት መስለብን የሚገልጽ ዐዋጅ እንደነበራቸው ሲጠቅስ ፣ አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ ደግሞ ዐጼ ዮሃንስ አራተኛ ወደ ጎጃም በዘመተ ጊዜ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ዐዋጅ አንዳስነገረ ጠቁሟል።

ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ዐዋጅ ሽብር ከመንዛት ዓላማ ባለፈ በተግባር ስለመፈጸሙ የሚያስረዳ ሰነድ አላጋጠመኝም። የወንድን ብልት መስለብ በብዙ ቦታ ይፈጸም እንደነበር የሚያሳዩ የተረጋገጡ ሰነዶች ከውጭ ሀገር መንገደኞችም ሆነ ከአገራችን ጸሐፌ ትእዛዛት ስናገኝ ጡት ቆረጣ መፈጸሙን የሚያረጋግጡ ምስክርነቶች ግን አልደረሱንም።

አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት፣ በአርሲ ጦርነት የሴቶች ጡት ተቆርጦ ከሆነ በጊዜው የነበሩት የታሪክ ጸሐፊዎች ለምን አልመዘገቡትም? የሸዋ ጸሐፊዎች አለቃ አጽሜና አለቃ ገብረስላሴ በዚህ ጉዳይ ላይ የመዘገቡት ነገር የለም። እኒህ ጸሐፊያን የራሳችው ወገን የሆነው ሰራዊት የሚፈጽመውን ግፍ በኩራት አልፎ አልፎም በወቀሳ የመዘገብ ልምድ እንዳላቸው ስናይ፣ ሆን ብለው ዘለውት ነው የሚለውን ድምዳሜ መቀበል ያቅተናል።ስለአርሲ ጦርነት መረጃ የሰበሰቡ፤ የኦሮሞ ወዳጅ እና የምኒልክ ነቃፊ የነበሩ የአውሮፓ መንገደኞች ስለ ጉዳዩ ያሉት

ነገር አለመኖሩ ጥርጣሬያችንን የበለጠ ያጎላዋል። ለምሳሌ ማርቲያክ ደሳልቪያክ ከጦርነቱ ጥቂት ጊዜ በኋላ መጥቶ ከአርሲዎች የሰበሰበውን ታሪክ ሲያካፍል ስለጡት መቁረጥ የዘገበው ነገር የለም። ይህ ጸሐፊ የምኒልክ ሰራዊትን፣ “ጭካኔ ማጋለጥ” የሕይወቱ አንድ ትልቅ ተልእኮ አድርጎ የሚቆጥር ሰው እንደመሆኑ መጠን፣ ጡት ቆረጣው ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ሳይመዘግበው አያልፈውም ነበር።

ጁልየ ቦረሊ የተባለው ሌላው በወረራው ዘመን የነበረ የፈረንሳይ ጎብኚ ከአርሲ ዘመቻ በኋላ፣ የወቅቱን አባ ሙዳ አነጋግሯል። ከኦሮሞ ጓደኞቹ መረጃዎችን አሰባስቧል። ጡት ቆረጣን አስመልክቶ ግን ያስቀረልን አንዳች ነገር የለም። ይህ ጸሐፊ ምኒልክንና ጣይቱን ውሃ ቀጠነ ብሎ በመዝለፍ የታወቀ በመሆኑ የንጉሡን ገመና ይደብቃል ተብሎ የሚጠረጠር አይደለም። ስለዚህ በየትኛውም አግባብ እንዲህ አይነቱን ዐቢይ ዜና ሰምቶ ሊያልፍ የሚችልበት ምክንያት አልነበረም።

እንዲያውም ቦረሊ በመጽሐፉ፣ ምኒልክ በአርሲ ጦርነት ወቅት አንድ ባስገባሪው ሰራዊት በኩል የተሰለፈ ወታደር (ወታደሩ ብሔሩ አልተገለጸም) የወደቀ አርሲ ሲሰልብ አግኝቶ ሞት እንደፈረደበት ዘግቧል። ምኒልክ ብሔርተኞች እንደሚስሉት ዓይነት ጭራቅ ቢሆን ኖሮ ሰላቢውን ወታደር ሹመት እንጂ ሞት አያቀዳጀውም ነበር።

ቸሩሊ የተባሉት የጣልያን ሊቅ፣ “የኦሮሞ ሕዝብ ስነ-ቃል” በሚል ጥናታቸው በአርሲ ወረራ ወቅት በአርሲዎች የተገጠሙ አያሌ ግጥሞችን እንጉርጉሮዎችን እና ሽለላዎች አጠራቅመው አሳትመዋል። ይሁን እንጂ ከተሰበሰቡት ግጥሞች መካከል ስለ ጡት ቆረጣ የሚያወሳ አንድም ስንኝ የለም። ይሄን የመሰለ ክስተት ደርሶ ከሆነ ከአዝማሪዎቹ እንጉርጉሮ እንዴት አመለጠ?

በአጠቃላይ በምኒልክ ተፈጸመ የተባለው የአኖሌ የጡት ቆረጣ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሰነዶች ላይ ያልተመሠረተ ለመሆኑ ይሄ በቂ ማስረጃ ይመስለኛል። በአርሲ ታሪክ ጥናት ዋና ባለሙያ የሆነው ፕሮፌሰር አባስ ገነሞ በመጽሐፉ ውስጥ ጡት ቆረጣ መፈጸሙን የሚያሳይ አንድም የታሪክ ሰነድ ማቅረብ አልቻለም።

* ከአሜን ባሻገር: ከገፅ 185-188

Share.

About Author

Leave A Reply