የጥላቻ ንግግር ህግ ኢትዮጵያን ይታደጋት ይሆን?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የዕለተ ሀሙስ ጥቅምት …ቀን የፓርላማ ማብራሪያ አንድ ወሳኝ ነገር ብልጭ አለች፡፡ ነገርየዋ በቀላሉ አለፍ ያለች ብትመስልም ከባድ ሚዛን መሆኗ ግን እሙን ነው፡፡
ይህችም ጉዳይ ከጥላቻ ንግግር ጋር በተያያዘ መንግስት ሕግ ለማውጣት በዝግጅት ላይ መሆኑን የምትገልፀዋ ማብራሪያ ናት፡፡ ነገርየዋን እጅግ ወሳኝ ያደረጋት ደግሞ በሀገራችን ያለው ከባቢያዊና ነበራዊ ሁኔታ በጥላቻ ንግግር የተሞላ መሆኑ ነው፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያን ማህበራዊ ሚዲያ ለአፍታ የተመለከተ ሰው ሀገሪቱ ምን ያህል በጥላቻ እየታመሰች መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ካለው ማንነትን መሰረት ካደረገ ግድያ፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመትና ጅምላ ፍረጃ ጀርባ የጥላቻ ንግግር መኖሩ አጠያያቂ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ከሌላው ዜጋ ጋር የግል ፀብ ከሌለው በስተቀር፤ አንዱ ዜጋ ሌላውን ከመሬት ተነስቶ ሊያጠቃ የሚችልበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም፡፡
ያም ሆኖ ከግለሰቦች ዕለታዊ ፀብ ያለፈ ጉዳይ ሲፈጠር ግን የጀርባውን መንስኤ በሚገባ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ከድርጊት ጀርባ ሀሳብ ያለ መሆኑ ግን ሊዘነጋ አይገባም፡፡
የጥላቻ ንግግር ሲባል አገላለፁ በቀጥታ ከአንደበት ወይም ከንግግር ጋር የተያያዘ ይመስላል እንጂ በውስጡ በርካታ ጥቅል ሀሳቦችን የያዘ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ የጥላቻ ንግግር በአንደበት አማካኝነት በመድረክ ከሚነገረው ንግግር ጀምሮ በፅሁፍ እንደዚሁም በኤሌክትሮኒክስና በምስል ጭምር እስከሚገለፀው የጥላቻ ድርጊት ደርስ አካቶ የሚይዝ ነው፡፡
አገላለፁ በፈረንጆቹም ጭምር “Hate Speech” በሚለው አጠርር ስለሚታወቅ ጉዳዩ ከአንድበት ንግግር ጋር ብቻ የሚያያዝ ይመስላል፡፡ ሆኖም ትንታኔው በጥልቀት ሲመረመር የጥላቻ ንግግር (Hate Speech) መገለጫው አንድን ማህበረሰብ ወይንም ግለሰብ ለማጥቃት ለማሸማቀቅና ለማግለል በማሰብ በንግር፣ በምስል ፣በፅሁፍ፣ በካርቱን፣ በቅርፃ ቅርፅና በልዩ ልዩ ምልክቶች ተደግፎ ጥላቻን ማሰራጨት ማለት ነው፡፡ ጥላቻው የሚሰራጨው ከግለሰቡ ወይንም ከማህበረሰቡ ዘር፣ ማንነት፣ የቆዳ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ ዜግነት፣ ፆታና የጤንነት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡
አንድ ነገር በመጨረሻ ከሚታየው ውጤት በፊት እንደ የሁኔታው የሚያልፍባቸው ደረጃዎች አሉት፡፡ በርካታ የማህበራዊ ጥናት ባለሙያዎች እንደሚያመለክቱት ከዘር ማጥፋት፣ ዜጎችን ከማፈናቀል፣ የጅምላ ጥቃትን ከማድረስ በፊት ወይንም ጀርባ የጥላቻ ንግግሮች አሉ፡፡ የጥላቻ ንግግሮች አንድን አካል ሰይጣናዊ መልክ ሰጥተው በመፈረጅ በተዳሚያኑ አዕምሮ ውስጥ ጥልቅ ጥላቻ እንዲኖር የማድረግ ኃይል አላቸው፡፡ ይህ ጥላቻ አንድ ጊዜ በታዳሚው አዕምሮ ውስጥ ከሰረፀ በኋላ ደግሞ ማህበራዊ መደላድልን በሚያገኝበት መልኩ በደንብ ይብላላል፡፡
ተብላልቶም አያበቃም፡፡ በጥላቻ አይን እንዲታይ የጥላቻው ስብከት ሰለባ የሆነው ማህበረሰብ ክፍል፤ በሂደት ሥርዓት ባለው መልኩ ቅርፅና ይዘት ተሰጥቶት ከተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲገለል ይደረጋል፡፡ የጥላቻው ንግግር ሰለባ የሆነው ማህበረሰብ በሌላው አዕምሮ እንዲሳል (Portrayed) የተደረገበት መንገድ አደገኛ በመሆኑ፤ ሰለባውን በሂደት ከማህበራዊ ትስስር ከመነጠልና ከማግለል ባለፈ የተፈረጀውን የህብረተሰብ ክፍል ወደ ማጥቃትና ለማጥፋት ወደመነሳት ተግባር የሚገባበት ሁኔታ አለ፡፡
እናም ይህንን ሁኔታ ስንመለከት የጥላቻ ንግግር የዘር ማጥፋት ዋነኛ መሰረት መሆኑን እንረዳለን፡፡ የጥላቻ ንግግር ከጀርባው ያላስተናገደ አንዳች አይነት የዘር ማጥፋት በዓለማችን አልተፈፀመም፡፡ ናዚ በአይሁዳዊያን ላይ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት መፈፀም ከመጀመሩ በፊት ጀርመናዊያን በአይሁዶች ላይ የከፋ ጥላቻን እንዲያዳብሩ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ መደላድልን ሰርቷል፡፡
ይህ ጥልቅ የሆነ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በእያንዳንዱ ጀርመናዊ አዕምሮ ውስጥ በመስረፁ የአይሁዳዊያን በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በመርዝ ጭስ መገደል፣ ቆዳቸው እንደ እርድ እንስሳ በህይወት እያሉ መገፈፍና እንደ ዝንጀሮ የመድሀኒት መሞከሪያና መማሪያ መደረጉ እንደ ድል ብስራት ተደርጎ የሚነገርበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህም የናዚ ፀረ ሴማዊ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ምን ያህል የጀርመናዊያንን ከሌሎች ጋር አብሮ የመኖር መሰረት ንዶት እንደነበር ግልፅ ማሳያ ነው፡
የናዚን ትዕዛዝ የሚያስፈፅሙ አካላትም ቢሆኑ በዚህ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ስርፀት ውስጥ ያለፉ ስለነበሩ ሲፈፅሟቸው በነበሩት እኩይ ተግባራት ሁሉ ሊያመዛዝን የሚችለው ሰብዓዊ የህሊና ክፍላቸው ሙሉ በሙሉ የታወረ ስለነበር፤ ድርጊታቸውን እንደ ፅድቅ የሚቆጥሩበት ሁኔታ ነበር፡፡
በሩዋንዳ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከደረሰው የዘር ማጥፋት ጀርባ በሬዲዮ ፕሮፖጋንዳ ጭምር የታገዘ የጥላቻ ንግግር ዘመቻ ነበር፡፡ በተለይ በቱትሲዎች ላይ የጅምላ ግድያው ሲፈፀም፤ የቱትሲዎችን ነፍስ ለማሳነስ “በረሮዎች” ወይንም “cockroaches” የሚል የጥላቻ ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር።
በመሆኑም አንድ ሁቱ፤ አንድን ቱትሲ ሲገድል የሚሰማው ስሜት በረሮ የገደለ ያህል ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ በሀገረ ሩዋንዳ በቱትሲና ሁቱ መካከል በተሰራጨው የዘር ጥላቻ ከአንድ ሚሊዮን ላላነሱ ሰዎች የዘር ጭፍጨፋ ምክንያት ሆኗል፡፡
ሀገሪቱ ከተረጋጋች በኋላ በርካታ በድርጊቱ የተሳተፉ ሩዋንዳዊያን በቁጥጥር ሥር ውለው ሲጠየቁ በጊዜው በነበረው የጥላቻ ንግግር በከባድ የበቀል ሥካር ስሜት ጥቃቱን የፈፀሙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ እናም እነዚህ ሁኔታዎች ሲታዩ የጥላቻ ንግግር ምን ያህል ለጥፋት አቀጣጣይ ነዳጅ እንደሆነ ግልፅ ማሳያ ነው፡፡
በጥላቻ ንግግር የተመረዙ ሰዎች በዚያ በተመረዙበት ጉዳይ ሊያመዛዝኑ የሚችሉበት የአዕምሮ ክፍል(Reasoning Faculty ) ሙሉ በሙሉ ዝግ ነው፡፡ እናም በውስጣቸው ከሚነደው የጥላቻ እሳት የተነሳ የጠሉትን ሰው ሲያርዱ፣ ሲደበድቡ፣ ሲገሉና አካሉን ሲቆራርጡ የሚሰማቸው ውስጣዊ ስሜት፤ ፍርሀትና ፀፀት ሳይሆን፤ ደስታ ነው፡፡ ከዚህ አሰቃቂ ድርጊት ጀርባ ያለው ነዳጅ ደግሞ ጥላቻ ነው፡፡ እናም የጥላቻ ንግግር ለጥፋት ያለው እምቅ አቅም ከ…እስከ.. ተብሎ የሚገለፅ አይደለም፡፡
የጥላቻ ንግግርን በህግ መገደብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ህግ በማውጣት ችግሩን መቀነስ ይቻላል እንጂ ከምንጩ ማድረቅ የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡ ህግ አንድን ድርጊት በወንጀልነት ለይቶ ቅጣትን በመደንገግ በዚያ ድንጋጌ መሰረት አጥፊው ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኝ ማድረግ ይችላል እንጂ የችግሩን ምንጭ የማድረቅ አቅም የለውም፡፡
እናም የጥላቻ ንግግር የራሱ የሆነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰረት ያለው በመሆኑ፤ ከሁሉም በፊት ሊሰራ የሚገባው እነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በማንነት ላይ የተመሰረተው የዘር ፖለቲካ በዜጎች መካከል “እኛ እና እነሱ” የሚል የቡድንተኝት ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
ጉዳዩ “በእኛ እና በእነሱ” ሳያበቃ የጥላቻ መፈራረጁም ይሄንኑ “እኛ እና እነሱን” መሰረት ያደረገ ነው፡፡ እናም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በነበሩት የሀገሪቱ የፖለቲካ አወድ ጥላቻ፣ እርስ በእርስ መጠራጠር፣ መፈራረጅ፣ ታሪክን ለመናቆሪያነት መጠቀምና ዘርን መሰረት አድርጎ መጠቃቃት በእጅጉ ነግሶ ታይቷል፡፡
ይህንን ችግር ከመሰረቱ ማጥናቱ ምን አልባትም የችግሩን ምንጭ ለመለየት በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል የሚያደርግ ህግን ማውጣት ብዙም ከባድ አይሆንም፡፡ ሆኖም ህጉ ጥላቻን ለመከላከል ድጋፍ ሰጪ ይሆናል እንጂ ህጉ በራሱ ብቻውን መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግስት ይህንን ህግ በዚህ መንፈስ ለማውጣት አስቦ ከሆነ በእጅጉ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከማንነታቸው ጋር በተያያዘ ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ ሲታይ ጥላቻ በሀገሪቱ ምን ያህል እንደነገሰ ግልፅ ማሳያ ነው፡፡ ግለሰቦች አካላቸው በአደባባይ ተቆራርጦ ሲጣል ጥላቻ በሀገሪቱ ምን ያህል ሰፊ መደላድል እንዳገኘ ተጨባጭ ማመላከቻ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ በሌላ ኢትዮጵያዊ በህይወት እንዳለ በቁሙ በእሳት እንዲጋይ ሲያደረግ የችግሩ ግዝፈት ጥልቀትም ጭምር የታከለበት መሆኑን በሚገባ ያሳያል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ በየቀኑ የሚታየው የጥላቻ ንግግር፣ የግለሰቦችን ፎቶግራፍ እየለጠፉ ለጥቃት ማጋለጥና፤ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ መቀስቀስ በሀገሪቱ ያለውን የጥላቻውን ርቀት በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ሲታዩ ህጉ ዘገየ ቢባል እንጂ፤ ለምን ይወጣል የሚያስብል አይሆንም፡፡
ይሁንና ከማህበራዊ ሚዲያዎች ጋር በተያያዘ ከቴክኖሎጂው ተለወዋዋጭ ባህሪና ውስብስብነት አንፃር በሚዲያዎች የሚሰራጩትን የጥላቻ ንግግሮች ህግን በማውጣት ብቻ ገደቦ እንዲቀር ማድረግ ይቻላል ማለት የዋህነት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ወሳኙ ነገር ዜጎችን ለጥላቻ ንግግር የሚያነሳሳቸውንና ታደሚያንንም በቀላሉ ለዚህ የጥላቻ ንግግር ተጋላጭ ሆነው ወደ ጥፋት ድርጊት እንዲገቡ የሚያደርጋቸው መሰረታዊ የፖለቲካ አውድ ምንድን ነው? ብሎ መለየቱ ላይ ነው፡፡
ይህ እውነታ ተጠንቶ ሊለይ ይገባል፡፡ በቅርቡ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስትር አንገብጋቢ አጀንዳዎች መካከልም ይሄው የዘር ጥላቻን የሚመለከተው ጉዳይ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ህጉን ከማውጣትና መተግበር ጎን ለጎን የጥላቻ መንስኤ የሆኑ ከባቢያዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን ለይቶ መፍትሄ እየሰጡ መሄዱ፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን አደገኛ የዘር ጥላቻ አዝማሚያ ዘለቄታዊ መፍትሄ እየሰጠው የሚሄድ ይሆናል፡፡ ለጥላቻ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ እየሰጡ በመሄዱ ሂደት ህጉን በሥራ ላይ ማዋሉ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ሆኖም የጥላቻ ንግግር ህግን ብቻ በማውጣት በኢትዮጵያ አሁን ያለውን ሥር የሰደደ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ታስቦ ከሆነ ትርፉ ድካም ነው፡፡
ህጉን በማውጣት ሂደት ውስጥ የሚኖሩ ሥጋቶች?
ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ ጋር በተያያዘ የሚወጡ ህጎች ሁልጊዜም ለትርጉም ተጋላጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ስላለ፤ ህጎቹ ሲተገበሩ ከፍተኛ የሆነ አወዛጋቢ ጉዳይ ይነሳል፡፡ በተለይ በጥላቻ ንግግር ሥም የዜጎችን የመናገርና የፕሬስ ነፃነት የማፈን ሥራን የሚሰሩ በርካታ መንግስታት መኖራቸው ሲታይ የእኛስ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ በመሆኑም ህጉ ሊወጣ የሚገባው የህገ መንግስቱን የመናገርና የፕሬስ ነፃነት መንፈስን የተከተለ ሊሆን ይገባል ማለት ነው፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply