የጥምቀት በዓልን በቅርስነት ለማስመዝገብ የሰነድ ውጤት እየተጠበቀ ነው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የጥምቀት በዓልን በዓለም የማይዳስስ ቅርስነት ለማስመዝገብ ለተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት የማስመዝገቢያ ሰነድ ተልኮ ውጤቱ እየተጠበቀ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ። በባለስልጣኑ የማይዳሰሱ ቅርሶች አስመዝጋቢ የጥናት ቡድን አስተባባሪ አቶ ገዛኸኝ ግርማ፤ ለአዲስ ዘመን ብቻ እንደገለጹት በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የማስመረጫ ሰነድ ለማዘጋጀት በጥር ወር 2009 ዓ.ም እና ጥር 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በአክሱም፣ በዝዋይ፣ በላሊበላና በሌሎች ቦታዎች መረጃ መሰብሰቡን ገልጸዋል። መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኋላም የማስመረጫ ሰነዱ ተዘጋጀቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አስተያያት እንዲሰጡበት ተደርጓል።

የተስተካከለው ሰነድም በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ለድርጅቱ መላኩን አቶ ገዛኸኝ ጠቁመው፤ ድርጅቱም የማስመዝገቢያ ሰነዱን ገምግሞ በጥቃቅን ያልተሟሉ ጉድለቶች ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ሀሳብ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ማስተካከያ እንዲደረግባቸው የተሰጡ ሀሳቦችም ማስተካከያ ተደርጎባቸው ለድርጅቱ የተላከ ሲሆን፤ ድርጅቱም ሙሉ መሆኑን በማረጋገጥ በራሱ ድረ ገጽ ላይ እንዲለቀቅ ማድረጉን ነው አስተባባሪው ያስረዱት።

አስተባባሪው እንዳሉት፤ በዘንድሮው የድርጅቱ ጉባዔ የጥምቀት በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ መመዝገቡን፣ በምዝገባው ሂደት የተለያዩ ባለድርሻዎች አካላት መሳተፋቸውን፣ ቅርሱ የሕዝቡ መሆኑና ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ፋይዳ ይገመገማል። ከዚህም በተጨማሪ ኅብረተሰቡና መንግስት ቅርሱን ጠብቀው ለትውልዶች ማስተላለፍ የሚችሉና ቀጣይነት ያለው መሆኑ፤ በዓሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብትን የሚያከብር፣ በሕዝቦች መካከል መልካም ግንኙነት የሚፈጥር፣ የቅርሱ መመዝገብ ለሌሎች ቅርሶች አስተዋፅዖ የሚያበረክት መሆኑና መሰል ጉዳዮች በጉባዔተኛው ይታያል፡፡

የጥምቀት በዓል በእነዚህ መስፈርቶች የሚያልፍ ከሆነ በህዳር 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ አራተኛው የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንደሚመዘገብ አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡ ከጥምቀት በዓል በተጨማሪ የአሸንዳ በዓልን በቅርስነት ለማስመዝገብ የሰነድ ዝግጅት ስራ መጀመሩንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የማይዳሰሱ ቅርሶች መመዝገባቸው የአገሪቱን ባህሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ይረዳሉ፡፡ የቱሪዝም ፍሰቱን በከፍተኛ ደረጃ ለመጨመር ያግዛል፤ ቅርሶችንም ለመጠበቅ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚዊ ጥቅሞችን ያሳድጋል። ኢትዮጵያ ዘጠኝ የሚዳሰሱና ሶስት የማይዳሰሱ በአጠቃላይ 12 ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በቅርስነት አስመዝግባለች፡፡

አጎናፍር ገዛኸኝ

Share.

About Author

Leave A Reply