የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ የሚመክሩበት መድረክ እንዲመቻች ተጠየቀ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በቅርቡ ከውጭ የተመለሱና ነባር የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከገዥው ፓርቲ ጋር በጋራ በሀገሪቱ የወደፊት አቅጣጫዎችና የህግ የበላይነት ጉዳይ ላይ የሚመክሩበትን መድረክ፤ መንግስት
ኃላፊነት ወስዶ እንዲያመቻች ሰማያዊ ፓርቲ ጠየቀ፡፡
ፓርቲው ትናንት በሰጠው መግለጫ፤ በሀገሪቱ የሚታዩ የህግ አለመከበርና የዜጎች እንግልት እንዲገታ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ሁኔታ ላይ የጋራ አቋም ይዘው
እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ውይይት ማካሄድ ያስፈልጋል ብሏል።
ይህን የውይይት መድረክም የሀገርን ሰላምና መረጋጋትን የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት የሀገሪቱ መንግስት እንዲያዘጋጅ ፓርቲው በመግለጫው ጠይቋል፡፡ ይህ መድረክ ቢዘጋጅ “ትጥቅ
ፍታ አልፈታም የሚል ውዝግብን በማስቀረት በሀገሪቱ ጉዳይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝም አጋዥ እንደሚሆን ሰማያዊ ጠቁሟል፡፡ “የሀገርና ህዝብን ሰላምና መረጋጋት ከማስፈን አንፃር፤
የፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ሊገድቡን አይገባም” በሚል መርህ ፓርቲው ባወጣው የአቋም መግለጫው፤ “ይሄ የኔ ሀገር ነው፤ ያ ያንተ ነው መባባሉ ቀርቶ፣ የጋራ ሃገራችንን
ወደ መገንባት ሂደት መግባት አለብን” ብሏል፡፡ “ፖለቲከኞች ከጋሞ ሃገር ሽማግሌዎች መማር አለባቸው” ያለው ፓርቲው ለፀብ መነሻ የሚሆኑ አጀንዳዎችን በመተው፣ ህዝብን አንድ
በሚያደርጉና በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቋል፡፡
መንግስት እንዲያዘጋጀው በሚፈለገው የጋራ መድረክም፣ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ እወክለዋለሁ የሚሉትን የማህበረሰብ ክፍል የማረጋጋትና አቅጣጫ የማስያዝ
ስራ እንዲሰሩ ይጠበቃል፤ ይህም የሃገርን ሰላም ለመመለስ አጋዥ ነው የሚል እምነት እንዳለው፤ ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በግለሰብም ይሁን በቡድን እየተንቀሳቀሱ የዜጎችን ሰላም የሚያውኩትን አውግዟል፤ መንግስትም በቆራጥነት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ጠይቋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply