ያልተመዘገቡ የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች በኢትዮጵያ ገበያውን አጥለቅልቀዋል፤ ተጠቃሚዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ባለስልጣኑ አስጠንቅቋል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ያልተመዘገቡ የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች በገበያ ላይ መገኘታቸውን የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ባደረገው የድህረ ገበያ ቅኝት መድኃኒቶቹ ገበያ ላይ መገኘታቸውን በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።

በተደረገው የቁጥጥር ስራ በተቋሙ ያልተመዘገቡ፣ ጥራትና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የተለያዩ የስንፈተ ወሲብ መድሃኒቶች መገኘታቸው ተረጋግጧል።

በዚህም መሰረት ቪጎ 50፣ ቪጎ 100፣ ቬጋ 50፣ ቬጋ 100 ፣ ፊካ 50ና ፊካ 100 የተሰኙ የወሲብ ማነቃቂያ መድሃኒቶች በገበያ ላይ ውለው ተገኝተዋል።

ስለሆነም መድሃኒቶቹ በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ በመሆናቸው፥ ህብረተሰቡ ምርቶቹን ከመጠቀም ራሱን እንዲቆጥብና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶችን ከሀኪም ትዕዛዝ ውጪ የሚሰጡና የሚያሰራጩ ህገ ወጥ የመድኃኒት ተቋማት እንዳሉ በመስሪያ ቤቱ ተረጋግጧል።

ስለሆነም ማህበረሰቡ መሰል ተግባር ሲፈፀም ከተመለከተ በአከባቢያው ላሉት ተቆጣጣሪ አካላት፣ ለጤና ቢሮ ፣ለፖሊስና በነጻ ስልክ መስመር 8482 በመደወል ለባለስልጣን መስሪያቤቱ እንዲያሳውቅ ተጠይቋል፡፡

መደኃኒቶች ህጋዊ መሆን አለመሆናቸውን ለመለየት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስርዓት የዘረጋ ሲሆን፥ይሄንም የመድኃኒቱን ስም በwww.mris.fmhaca.gov.et በሚለው ዌብሳይት በማስገባት መድኃኒት በሀገራችን መመዝገብ አለመዝገቡን እና ሌሎች ከመድኃኒቱ ጋር ተየያዥነት ያላቸው መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply