ይህ ስርአት ይቀጥል ማለት እነ ጃዋር መፈንጨታቸው ይቀጥል፣ በኦሮሞ ክልል የሌሎች መብት እንደተረገጠ ይቀጥል ማለት ነው – ግርማ ካሳ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

“ዶ/ር አብይ ከለቀቀ አገር ትፈርሳለች ፣ የሚተካው የለም፣ ከዶ/ር አብይ አመራር ጋር ወደፊት” የሚል አሉ። ይህ አይነቱ አነጋገር ፣ ሕዝብን መስደብ ነው። ያኔም መለስ ዜናዊ ከሌለ አገር ትፈርሳለች ሲባል እንደነበረው።

ዶ/ር አብይ ትልቅ የሕዝብ ድጋፍ ነበረው።በሚያስደንቅና በሚያሰደምም ሁኔታ። ነገር ግን ቃል እንደገባው ፣ ከቃላት ባለፈ በፖሊሲ የሰበከውን የመደመርና የኢትዮጵያዊነት ፖሊሲ መተግበር አልቻለም። ችግሮች እየተባባሱ መጡ።አገርን ማረጋጋት አልቻለም። ሕግና ስርዓትን ማስጠበቅ አልቻለም። በርሱ አስተዳደር ላይ ተንጠላጥለው አገር አፍራሽ የኦሮሞ ጽንፈኞች አገርን እያመሷት ነው። በርሱ አመራርና እትስፋ ሰጪ ንግጎርች ሕዝብ ጸሃይ ሊወጣልን ነው ብሎ ጠብቆ ነበር። ግን አሁን በዶ/ር አብይ አመራር እየጨለመ ነው። አገር ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ከነበረው ስጋት ወደ ባሰ ስጋት እየተዘፈቀች ነው።

ይኸው በባህር ዳር ሕግን እያስከበረ አይደለም ወይ የሚሉ አሉ። አዎን ሕግ ላስከብር ብሎ ተነስቷል። ግን የተነሳውም እሳቱና ችግሩ ባለስልጣናት ጋር ስለደረሰ፣ ለስልጣኔ ያሰጋኛል በሚል እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። እስቲ በባህር ዳር ሆነ ሌላ ቦታ፣ ሌሎች ዜጎች ሞቱ ተገደሉ ቢባል ዶ/ር አብይ እርምጃ ይወስድ ነበር? መልሱን ለናንተ እተዋለሁ።

ዶ/ር አብይ ጥሩ ልብና ጥሩ ሐሳብ ሊኖረው ይችላል። ለዚህም ነበር እኔንም ጨምሮ ብዙዎቻችን በዶ/ር አብይ ላይ እምነት አለን ብለን ስንጽፍና ስንከራከር የነበረው። ግን አሁን በእጅጉ ሐሳቤን እየመረመርኩ ነው።

በኔ እይታ አሁን የፌዴራል መንግስትን ከኦህዴድ እጅ ማስወጣት አስፈላጊ ነው የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ። ኦዴፓዎች እድል ተሰጥቷቸው እድላቸውን አበላሽተዉታል። በነርሱ ውስጥ ያሉ ጸረ-ሕዝብና ጸረ-አገር ዘረኛ ጽንፈኞችን ማራገፍ አልቻሉም። የልዩ ጥቅም፣ የኦሮሞ ብቻ፣ አድሎአዊ፣ አፓርታይዳዊና ዘረኛ በሆነው የኦነግና የነጃዋር ፖለቲካ የተተበተቡ ናቸው።

ኦህዴዶች የበላይ የሆኑበት የዶ/ር አብይ አስተዳደር ይቀጥል ማለት እነ ጃዋር መፈንጨታቸው ይቀጥል፣ በኦሮሞ ክልል የሌሎች ማህበረሰባት መብት እንደተረገጠ ይቀጥል፣ ዜጎችን መጤ እያሉ ማፈናቀል ይቀጥል፣ ባንኮችን መዝረፍ ይቀጥል፣ የኬኛ ፖለቲካ ይቀጥል ….ማለት ነው። ለዚህም መከራከሪያ ብዙ መሄድ አያስፈልግም። የኦህዴድ የድርጅት ጽ/ቤት ሃላፊ የሆነውን አዲሱ አረጋ ቂጤሳ ከሁለት ሳምንት በፊት የተናገረውን ጸያፍና ነዉረኛ ንግግር መጥቀሱ ይበቃል።

“አይ ወንድም ግርማ ካሳ ተሳስተሃል። የዶ/ር አብይ አስተዳደርና ድርጅቱ ኦህዴድ ለእኩልነት፣ ለፍትህ ፣ ለሁሉም ዜጎች ሰላምና ደህንነት የቆሙ ናቸው። የዘርና የጎሳ ልዩነት ሳይኖር ሁሉም እኩል የሆኑባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት የቆረጡ ናቸው። እድል ሊሰጣቸው ይገባል።ተስፋ መቁረጥ የለብንም” ካላችሁኝ አሳምኑኝ። የምሬን ነው የምላችሁ ትላንት ስደግፋቸው የነበሩትን ዛሬ መደገፍ በጭራሽ አይከብደኝም። እኔ ብቻ ሳልሆን፣ ከአንድ አመት በፊት ሆ ብሎ ሲደግፋቸው የነበረ ህዝብ እንደገና በብዙ እጥፍ ሆ ብሎ ለድጋፍ ይወጣል።

እንዴት ነው ኦህዴድ/ኦዴፓ ከፌዴራል መንግስት ማስወገድ የሚቻለው? ተብሎ ሊጠየቅ ይችላ። ሶስት አማራጮች አሉ። ከነዚህ አማራጮች መካከል ሁለቱ ዶ/ር አብይን ያካተቱ ናቸው።

1. የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ከአጋሮቻቸው ጋር (እነ ዶ/ር ብርሃኑን ጨምሮ) ዉህደት ቢመሰርቱ፣ ኦህዴድ/ኦዴፓ ይከስማል። በኦሮሞ ክልል አዲሱን ፓርቲ ኦሮሞ ያልሆኑም ይቀላቀሉታል። እንደነ አቶ ሙስጠፋ ያሉም እንደዚሁ ይገባሉ። በዚህ አገር አቀፍ በሆነና በዘር ላይ ባልተማከለ ድርጅት ውስጥ እንደ ጃዋር ያሉ ጽንፈኞች መጠላጠያ አያገኙም። ድርጅቱ ለአንድ ጎሳ ልዩ ጥቅም ሳይሆን ለሁሉም ዜጎች እኩልነት ይሰራል። ዶ/ር አብይም የዚህ አገር አቀፍ ፓርቲ ሊቀመንበርና የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መቀጠል ይችላል።

2. አዴፓ ጠንካራ አመራሮችን ወደፊት ማምጣት ከቻለ፣ ከሕወሃት ጋር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ፣ እንደ ወልቃይት ባሉ ችግሮች ሁሉንም አሽናፊ ባደረገ መልኩ በመፍታት የመቀራረብ እድሉ ከተከፈተ፣ ምን አልባት ከነ ሚሊዮን ማቴዎስ ከመሳሰሉ የሲዳማ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች በቀር አብዛኛውን ደሃዴን በመያዝ ከኦህዴድ/ኦዴፓ ውጭ የሆነ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርን መመረጥ ይችላል። ዶ/ር አብይ ስልጣን የያዘው በዋናነት ብአዴን/አዴፓ ሙሉ ድምጽ ስለሰጠው ነበር። የአዴፓን ድጋፍ ካጣ ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መቀጠል አይችልም። ሰለዚህ በራሳቸው በኢሕአዴግ አሰራር፣ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እንደተቀየረው፣ ዶ/ር አብይም ሊቀየር ይችላል። በማን ብትሉኝ የኢሕአዴግ አባል የሆኑ ብቃት ያላቸው በርካታ አመራሮችን መዘርዘር ይቻላል።

3. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ የታየው አሳዛኝ ክስተት በኢሕአዴግ ድርጅት ውስጥ ትልቅ እርስ መርስ ያለመተማመን እንዳለ ነው ያሳየው። ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አሰራሩ፣ ሃላፊነቶችን በብቃት ሳይሆን በዘር ኮታ እያደረገ መቀጠሉ ችግር ስለሆነ፣ አዲስ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሽግግር መንግስት በማቋቋም አገር እንድተረጋጋና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ ማድረግ ይችላል። ዶ/ር አብይ የዚህ የሽግግር መንግስት መሪ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል።

Share.

About Author

Leave A Reply