ይድረስ ለዲያስፖራዎች፣ OMN እና ESAT ከአንድነት ውስጥ ልዩነትን ማጉላት አቁሙ!!!

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ከጠ/ሚ አብይ አህመድ ጋር ለመወያየት በስታዲዮም የተሰበሰቡት ሰዎች የያዙት የሚያውለበልቡት የባንድራ ዓይነት ለብዙዎች አስገራሚ ሆኗል። በእርግጥ ነገሩን ሰፋ አድርገን ካየነው በስታዲዮሙ ውስጥ የሚውለበለበው ባንዲራ አረንጓዴ፥ ቢጫ፥ ቀይ ቀለማት አሉት። ልዩነቱ ያለው ከቀለሙ ሳይሆን ባንዲራው ላይ ካለው ምልክት ነው። ይህ ምልክት ደግሞ እንደ አመልካቹ ወይም አምላኪዎቹ ይለያያል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ “ዶ/ር አብይን ለመቀበል በስታዲዮም የተገኙት አንድ ዓይነት ባንድራ የያዙ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ናቸው” የሚል አስተያየት በብዙዎች እየተሰጠ ይገኛል። ይህ ግን በተወሰኑ የመረጃ ምንጮች ላይ ጥገኛ ከመሆን የመጣ ችግር እንጂ በስታዲዮሙ ውስጥ ሁሉም አይነት ባንዲራ አለ። ለምሳሌ DW Amharic፣ OMN፣ ESAT እንዲሁም ወዳጄ Girma M. Yilma ከስታዲዮሙ ውስጥ በቀጥታ ስርጭት እየቀያየርኩ ተመልክቼያለሁ።

ነገር ግን ከባንዲራ ጋራ ተያይዞ የተዛባ አመለካከት የተፈጠረበት መሰረታዊ ምክንያት በOMN እና ESAT መካከል በሚደረገው አጉል ውድድርና ፉክክር ነው። ከታች ያለው የቪዲዮ ምስል በተመሳሳይ ሰዓት OMN እና ESAT በቀጥታ ያሰራጩት ነው። OMN ብቻ ለሚመለከት ሰው ስታዲዮሙ ውስጥ ከኦነግ ባንዲራ በስተቀር የሌለ ይመስላል። ነገር ግን ESATን ስትመለከቱ ደግሞ ችግሩ የት እንዳለ በግልፅ ያሳያችኋል። በዚህ መሰረት በስታዲዮሙ የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ በተከፈተበት ወቅት በOMN እና ESAT የተላለፈውን አንድ ላይ እያነፃፀራችሁ ተመልከቱና እስኪ እናንተ ፍረዱ።

ሀገራቸው አንድ ኢትዮጵያ ናት። የሚጨፍሩበት ሙዚቃ የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” የሚለው ዘፈን ነው። የያዙት ባንዲራ ቀለም አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ነው። የሚጠብቁት እንግዳ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ነው። የአንድ ሀገር ልጆች፣ በአንድ ቦታ ተሰብስበው፣ አንድ ዓይነት ቀለም ያለው ባንዲራ እያውለበለቡ፣ በአንድ ሙዚቃ እየጨፈሩ፣ አንድ እንግዳ እየጠበቁ፣… ለተቀረው ማህብረሰብ ልዩነትና መለያየትን ይሰብካሉ።

በዚህ መሰረት OMN እና ESAT እንደ ሚዲያ ከገቡበት አጉል ፉክክርና እሰጣ-ገባ ወጥታችሁ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም ስራ ብትሰሩ የተሸለ ይመስለኛል። በእናንተ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ባያስከትል በማህበረሰቡ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ስለዚህ ከአጉል ፍክክርና እልህ መወጣት አለባችሁ በማለት አስተያየት መስጠት እውዳለሁ።

እናንተ በጀርመንና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ህግ አክብረው እየኖሩ እዚህ ላሉ ወጣቶች ጥላቻና ልዩነትን መስበክ ማቆም አለባቸው። እንደ ጀርመን ባለ ሀገር ውስጥ ህግና ስርዓት ይከበራል። ስለዚህ ማንም የፈለገውን ባንዲራ ይዞ ቢወጣ ለምን ይሄን ያዝክ ተብሎ አይጠየቅም። አንዱ ሌላውን በጉልበትና በኃይል በማያስገድድበት ሀገር እየኖሩ፣ ጎን ለጎን ቆመው እየጨፈሩ፣ ነገ መንገድ ላይ “ሰላም” ተባብለው ሊያልፉ፣ እዚህ ሀገር ቤት ላሉት ወጣቶች ከአብሮነትና መቻቻል ይልቅ ልዩነትና መጠፋፋትን ይሰብካሉ። አውሮፓና አሜሪካ በሰላም እየኖሩ እዚህ ያሉ ምስኪን ወጣቶች እርስ-በእርስ ለማጋጨት ልዩነትን ይሰብካሉ።
CC:
Jawar Mohammed
Abebe Gellaw
Kibret Daniel

(መምህር ስዩም ተሾመ)

Share.

About Author

Leave A Reply