ዮናስ ጋሻው፤ “እስር ቤት ውስጥ አኮላሽተውኛል”

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ጸሐፊ፡- በላይ ማናዬ
ዮናስ ጋሻው ደመቀ ይባላል፡፡ ዕድሜው 29 ዓመት ሲሆን፣ የሚኖረው ባህር ዳር ከተማ ነው፡፡ የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡
ዮናስ ከ2008ቱ የክረምት ወራት ጀምሮ በአማራ ክልል ከተስተዋለው ሕዝባዊ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደኅንነት አካላት ከፍተኛ ክትትል ሲደረግበት እንደቆየ ይናገራል፡፡ በወቅቱ ይኖርበት የነበረው ባህር ዳር ከተማ ክትትሉ ሲበዛበት አድራሻ በመቀየር ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ (ጥር 04/2009) በታክሲ ከሁለት እህቶቹ ጋር እየተጓዘ እያለ በአራት ፒክአፕ መኪና ሞልተው በመጡ ፌደራል ፖሊስ እና ሲቪል የለበሱ ደኅንነቶች በሕዝብ ፊት ከታክሲ አስወርደው አስፓልት ላይ እየደበደቡ ለእስር እንደዳረጉት በሐዘን ያስታውሳል፡፡ ዮናስ ከታሰረ በኋላ ከአንገቱ በላይ በጥቁር ልብስ ሸፍነው ወደማያውቀው ቦታ ወስደውታል፡፡ “ጫካ ውስጥ ከዛፍ ጋር አስረው ደብድበውኛል፡፡ በወቅቱ የጋብቻ ቀለበቴን እና የአንገት ሀብሌን ወስደውብኛል” ይላል፡፡ “‹ከዚህ በኋላ ልጅ ስለማትወልድ ትዳር ምን ይሰራልሃል?› እያሉ ንብረቴን ወስደውብኛል፡፡ ተሳልቀውብኛል፡፡ የግድያ ዛቻ ዝተውብኛል፡፡”
ዮናስ የማዕከላዊ ‹8 ቁጥር› ውስጥ
– ተገልሎ በጨለማ ውስጥ መታሰር
– አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ማሰቃየት
– ማንነትን መሠረት ያደረገ ዘለፋ
– ጠበቃ እና ቤተሰብ ጥየቃ ክልከላ
ዮናስ ጋሻው ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) የተወሰደው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ ከሳምንት በኋላ ነበር፡፡ የማዕከላዊ መርማሪ መጀመሪያ እሱን ያገኘው ቀን እንደተፀየፈ ሰው እየተመለከተው “ይህን ጊዜ መስጠት አያስፈልግም፤ መግደል ነው” ይል እንደነበር ይናገራል፡፡ “ወስደው ለእሱ ያስረከቡኝ ሰዎችም፣ ‹ስንይዘው እህቶቹ አይተዋል፤ ብዙ ሰዎች አይተውናል› ብለው ሲነግሩት ተበሳጭቶ ነበር፡፡ ሊገድለኝ ነበር ፍለጎቱ፡፡ ሽጉጥ አውጥቶ ግንባሬ ላይ ደቅኖብኝ ነበር” በማለት በሕይወት መትረፉ ይገርመዋል፡፡
የ29 ዓመቱ ዮናስ ጋሻው በ2010 ከተፈቱ የፖለቲካ እስረኞች አንዱ ነው፡፡ ወደ እስር ቤት በጤና ገብቶ ከአካል ጉዳት ጋር ተፈትቷል፡፡ ከሁሉም በላይ በድብደባ መውለድ እንዳይችል ተደርጓል፡፡
ዮናስ ማዕከላዊ እንደገባ በቀጥታ ‹8 ቁጥር› የምትባል ጨለማ ክፍል ነው የታሰረው፡፡ ‹8 ቁጥር› በጣም ጠባብ፣ ጨለማ እና ቀዝቃዛ ክፍል ነው፡፡ መርማሪዎቹ ዮናስን ‹በ8 ቁጥር› ውስጥ ለስድስት ወራት አቆይተውታል፡፡ ለብዙ ቀናት እጅና እግሮቹ በሰንሰለት ታስረው ነበር ቀን እና ሌሊት የሚያሳልፈው፡፡ ምርመራው ሁሌም ሌሊት፣ ሌሊት እንደነበር የሚደረግበት ይናገራል፡፡ የማዕከላዊ ቆይታውን ሲያስታውስ፣ ዮናስ “መርማሪዎቹ ሰክረው መጥተው ነው የሚመረምሩኝ፡፡ ለምርመራ ወጥቼ ያልተደበደብሁበትን ቀን አላስታውስም” እያለ ነው፡፡
ዮናስ ጋሻው በብዙ ስቃይ ውስጥ አልፏል፡፡ “በምርመራ ወቅት ጥፍሮቼን በፒንሳ ነቅለዋቸዋል፡፡ ጥፍሮቼ የተነቀሉበትን የጣቶቼ ክፍሎች በሹል ነገር እየነካኩ አሰቃይተውኛል፡፡ ብልቴ ላይ ሁለት ሊትር ውኃ እያንጠለጠሉ ግፍ አድርሰውብኛል፡፡ ይህም አልበቃ ብሏቸው፣ የተጎዳውን ብልቴን በድብደባ እያሰቃዩ አኮላሽተውኛል፡፡ ‹ከዚህ በኋላ አንተ ዘር ልትተካ አይገባም› እያሉ አሰቃይተውኛል፡፡ የቤተሰቦቼን ሥም እየጠሩ እንደሚገድሏቸው እየዛቱ የስቃይ ግፍ አድርሰውብኛል፡፡ ሰቅለው ደብድበውኛል፡፡ በኤሌክትሪክ ሾክ እና በገመድ አሰቃይተውኛል” በማለት የደረሰበትን ስቃይ በሙሉ በአጭሩ ሊጠቀልለው ይሞክራል፡፡
ዮናስ ጋሻው እቴነሽ ወልደሩፋኤል የምትባል መርማሪ በማንነቱ ላይ እየተዘባበተችበት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ እቴነሽ እና ሌሎችም “አቅም የለህም፤ ገና እንደፈለግን እናደርግሃለን፣ ማንም አይደርስልህም፡፡ የሚያድንህ ምድራዊ ኃይል የለም” እያሉ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት አድርሰውብኛል ይላል፡፡
ዮናስ ማዕከላዊ ውስጥ በተያዘበት ወቅት ለአራት ወር ሙሉ ማንም ቤተሰቡ እንዳያየው ተከልክሏል፡፡ “እኔን ልትጠይቀኝ የመጣች እህቴን አንድ ቀን አስረው አሰቃይተዋታል፤ ‹ድጋሜ እንዳትመጪ› ብለው አስፈራርተውለ ለቅቀዋታል፡፡ የሕግ ባለሙያ ማየት ተከልክዬ ነበር፡፡ ሕክምና ማግኘት አይታሰብም፡፡ በደም የተጨማለቀ ልብሴን እና ገላዬን መታጠብ አይፈቀድልኝም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ከምርመራ በኋላ ራሴን ስቼ ነበር የምመለሰው፡፡ ማሰቃየቱ የቀነሰልኝ ‹በፀረ ሽብርተኝነት ዐዋጁ 652/2001 አንቀጽ 4 የተመለከተውን ተላልፈሃል› በሚል ክስ ተመስርቶብኝ ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ከተዛወርኩ በኋላ ነበር፡፡ ቂሊንጦ በአንፃራዊነት ስቃዩ ቀንሶልኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በማዕከላዊ የደረሰብኝን ጉዳት በአግባቡ እንዳልታከም ተከልክያለሁ፡፡”
ማሰቃየት ያስከተለው አካል ጉዳተኝነት
ዮናስ በማዕከላዊ በተፈፀመበት ማሰቃየት ተግባር ብዙ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግር ደርሶበታል፡፡ “በድብደባው እና በኤሌክትሪክ ሾክ በደረሰብኝ ግፍ ቀኝ እግሬ መታጠፍ አይችልም፤ የአካል ጉዳተኛ አድርገውኛል፡፡ የግራ እግሬም ይንቀጠቀጣል፤ የነርቭ ችግር አለብኝ በድብደባው ምክንያት፡፡ ወገቤ፣ አከርካሪዬ ክፉኛ በመጎዳቱ በቮንቤልት አስሬ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ በእነዚህ ሁሉ አካላዊ ጉዳት ምክንያት አሁን ላይ በአካል ጉዳተኛ መደገፊያ በመታገዝ ነው የምቆመውና ከቦታ ቦታ የምቀሳቀሰው፡፡ ለእስር ከመዳረጌ በፊት ምንም ዓይነት የአካል ጉዳት አልነበረብኝም፤ አሁን አካል ጉዳተኛ አድርገውኛል” ይላል፡፡
ዮናስ ላይ የደረሰው ጉዳት አካላዊ ብቻ አይደለም፡፡ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስም ደርሶበታል፡፡ “አሁን ላይ ለእኔ እንቅልፍ መተኛት ከባድ ነው፤ መድኃኒት ወስጄ ነው እንቅልፍ የሚወስደኝ፡፡ በዚህም በቤተሰቤም ላይ ተጨማሪ ችግር ሆኜባቸዋለሁ” ይላል በሐዘን፡፡
ሕይወት ከፍቺ በኋላ
ዮናስ ጋሻው መንግሥት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መወሰኑን ተከትሎ በ2010 “በይቅርታ” ከእስር ተፈቷል፡፡ ዮናስ በሚኖርበት ባህር ዳር ከተማ በእስር ቤት በደረሰበት ግፍ ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት ለመዳን ሕክምና እየተከታተለ ይገኛል፡፡
ዮናስ “ይህንን ሁሉ የሰብዓዊ መብቶቼን የገረሰሱ ሰዎች ላይ ምንም ዓይነት የሕግ ተጠያቂነት ስለመኖሩ አላውቅም፤ የተደረገ ነገር ቢኖር እሰማ ነበር” ይላል፡፡ “ለእኔም ለደረሰብኝ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን በሕግም ሆነ በገንዘብ የተደረገልኝ አንድም ነገር የለም፡፡ በሞራል በኩል ከህዝቡ ‹አይዞህ› የሚል ድጋፍ አለኝ፡፡ ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከመንግሥት በኩል ግን ለእኔ የተደረገ አንድም ነገር የለም፡፡ እንኳን ካሳ ሊደረግልኝ ይቅርና አሁንም ‹ሕዝብን ያነሳሳል› እየተባልኩ ክትትል አለብኝ፡፡ የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት ስሔድ እንኳ ‹በቂ ዋስትና የለህም› እያሉ እያጉላሉኝ መታወቂያ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በአጠቃላይ ምንም ያገኘሁት ካሳ የለም፡፡” በማለት ሕይወት ከእስር በኋላ ወደ በፊቱ መመለስ እንዳልቻለ ይገልጻል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply