“ደስ ስላላችሁ ደስ ብሎኛል” አና ጎሜዝ ለኢትዮጵያዊያን

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ኢትዮጵያ ለመብቷና ለነፃነቷ የሚያግዟትን አውሮፓውያን ወዳጆች አጥታ አታውቅም፤ በተለይም ፖርቱጋል ለኢትዮጵያ የክፉ ቀን ደራሽ መሆኗን የዓፄ ልብነ-ድንግልና የልጃቸው የዓፄ ገላውዴዎስ ታሪኮች ምሥክሮች ናቸው፡፡ የፖርቹጋላዊያን እና የኢትዮጵያዊያን ታሪካዊ ትስስር ዘመናትን ተሻግሮ እስከ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስር ይሰድ ዘንድ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን የነፃነት ድምፆች ከፍ አድርገው በአውሮፓ መድረኮች ለዓመታት ያሰሙ የአውሮፓ ምክር ቤት አባል ተገኝተዋል፤ አና ጎሜዝ፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ‹‹ሀና ጎበዜ›› የሚል ሀገረኛ ቅፅል ስም የተሰጣቸው ፖርቹጋላዊቷ አና ጎሜዝ ለዘመናት ጥብቅና ወደ ቆሙላት ኢትዮጵያ ትናንት ገብተዋል፡፡

አና ማርያ ሮሳ ማርቲንስ ጎሜዝ ባጭሩ አና ጎሜዝ ይባላሉ፡፡ የካቲት 9 ቀን 1954 እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት በፖርቹጋሏ መዲና ሊዝበን ተወለዱ፡፡ በ2004 የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት አባልነት የሀገራቸውን የሶሻሊስት ፓርቲ እንዲወክሉ ተመረጡ፡፡ ከዚያ በፊት ግን በተባበሩት መንግሥታት ቆንስላዎች ውስጥ ከኒዮርክ እስከ ጄኔቭ፤ ከቶክዮ እስከ ለንደን በፖርቹጋል ኤምባሲ ሀገራቸውን ወክለው አገልግለዋል፡፡ አና ጎሜዝ የፖርቹጋልንና የኢንዶኔዥያን የሻከረና የከረረ ግንኙነት አለዝበው መልክ እንዳስያዙም ይነገርላቸዋል፡፡

የሊዝበን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሩቋ አና ጎሜዝ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ ድምጽ በመሆን በዓለም መድረኮች በመሞገት እና በመመስከር ታሪክ የማይረሳው ምዕራፍ አላቸው፡፡ በ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክን በመምራት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አና ጎሜዝ በወቅቱ መንግሥት በምርጫው ሂደት ላይ ‹‹ሸፍጥ ሠርቷል›› በማለት አጋልጠዋል፤ አሁንም ድረስ ስለጉዳዩ ሲነሳባቸው የሚያሳዩ ስሜት ከአውሮፓ ኅብረት ልዑክ አባልነት በላይ የኢትዮጵያ ዜጋም ያስመስላቸዋል፡፡

የ1997 ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ሥራው ሀገሪቱ አይታው በማታውቀው መንገድ አንጻራዊና ሰላማዊ ውይይቶችና ክርክሮች የተስተናገዱበት ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን የዚህ ታሪካዊ ምርጫ ተሳታፊ በመሆን የፈለጉትን ለመምረጥ ጉጉት ቢያድርባቸውም ፍጻሜው ግን እንዳጀማመሩ ሳይሆን ቀረና አና ጎሜዝ በአውሮፓ ታላላቅ መድረኮች ስለኢትዮጵያውያን ጥብቅና ቆሙ፡፡

አና ጎሜዝ የምርጫ ሂደቱን በቅርብ ሆነው ስለተከታተሉ ከምርጫው ማግስት ጀምረው በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ እና በታላላቅ የዓለም የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች እየተገኙ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንባ ጠባቂ በመሆን በዓለም ሕዝብ ፊት ስለኢትዮጵያውያን ተሟገቱ፡፡ ለታሰሩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ድምጽ ሆኑ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለተቃውሞ ሰልፍ በወጡባቸው ቦታዎች ሁሉ እየተገኙ ድጋፍ ያደርጉም ነበር፡፡ ከአንድ የሀገርና የሕዝብ ዜጋ በላይ ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉት ፖርቹጋላዊት እናት የኢትዮጵያውያን የክፉ ቀን ባለውለታ ተደርገው እየተቆጠሩ ነው፡፡

ትናንት ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት አና ጎሜዝ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ደጋፊዎቻቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ አና ጎሜዝም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያውያን አስፈላጊ ነው፤ እርሱን ደግሞ አሁን እያየሁ ነው›› ያሉት አና ጎሜዝ ከዚህ ቀደም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እና የዜጎች ነፃነት እንዲከበር የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ደስ ስላላችሁ ደስ ብሎኛል!›› ሲሉም በመልዕክታቸው አካትተዋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply