ደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ በታጣቂዎች ጥቃት እንቅልፍ ላይ የነበሩ ባልና ሚስትን ጨምሮ 4 ሰዎች ባለፉት 2 ቀናት መገደላቸውን ነዋሪዎችና የወረዳው ፖሊስ ገለጹ።

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት እንቅልፍ ላይ የነበሩ ባል እና ሚስትን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና የወረዳው ፖሊስ ገለጹ። ጥቃቱ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት ውስጥ የተፈጸመው ጉሙሬ ፤ ነዲዴ እና ቆሬ በተባሉ ሦስት የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው ተብሏል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጎጂ ዞን በኩል ወደ ቀበሌዎቹ ዘልቀው በገቡ የታጠቁ ቡድኖች መሆኑን በአካባቢው የነበሩ አይን እማኞች ተናግረዋል። በታጣቂዎቹ ከተገደሉት መካከል ሁለቱ በእንቅልፍ ላይ የነበሩ ባልና ሚስቶች መሆናቸውን የሟቾቹ ጎረቤት ነኝ ያሉ እንድ አዛውንት ለዲ ደብሊው በስልክ ገልጸዋል።

የዐይን እማኙ «ሟቾቹ የቅርብ ጎረቤቶቼ ናቸው ። ወይዘሮ ፋንቱ ጌታነህ እና አቶ አድማሱ ወሌ ይባላሉ ። አነኝህ ባልና ሚስቶች ትናንት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት በታጠቁ ሰዎች ተገድለዋል። ገዳዮቹ የሰዎቹን ሕይወት ካጠፉ በኋላ ንብረታቸውን ዘርፈው ነው የሄዱት ፤ ተገድለዋል» ብለዋል።

የአማሮ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሲዳሞ ማዳቦ ወረዳው ከምዕራብ ጉጂ ዞን በሚወሰንባቸው ቀበሌዎች በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከወረዳ እና ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ እየሆነ ይገኛል ብለዋል። አዛዡ «በምዕራብ ጉጂ ዞን አጎራባች ቀበሌዎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ሀይሎች ከባለፈው የሰኔ ወር ጀምሮ በወረዳው ነዋሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ።

አሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ ከወረዳውም ሆነ ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ ሆኗል፡፡ ፀረ ሰላም ሀይሎቹ የአሁኑን ጥቃት ጨምሮ እስከ አሁን ሰማኒያ ዘጠኝ ነዋሪዎችን ገድለዋል፡፡ አንድ መቶ ሃያ አምስት ንጹሃን ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት አድረሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ የደቡብ ክልልም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ችግሩን ባለመፍታታቸው አሁንም ጥቃቱ ተባብሶ እየቀጠለ ይገኛል። ሲሉ በአካባቢው ይታያል ያሉትን ችግር አብራርተዋል::

የደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ እና የኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞንን በሚያዋስኑ ቀበሌዎች በታጠቁ ሐይሎች ጥቃቶች እየተፈጸሙ እንደሚገኙ የወረዳው ባልሥልጣናት በተደጋጋሚ እየገለጹ ይገኛሉ። እስከ አሁንም በሰው ሕይወትና አካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ከሃያ እንድ ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀል በኬሌ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ የሐዋሳው የDW ወኪል ሸዋንግዛው ወጋየሁ ከወረዳው መስተዳድር ጽህፈት ቤት ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል።

Share.

About Author

Leave A Reply