ድንበር የማይወስነው ጉዞ በአፍሪካ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሻሂዳ ሁሴን

በዓለም ላይ በድህነታቸው የሚታወቁት 75 በመቶ የሚሆኑ አገሮች መገኛቸው አፍሪካ ነው ይላል አንድ ሰነድ፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሆኑ አሥሩ አገሮች ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ሕዝባቸው 48 በመቶ የሚሆኑት በቀን 1.25 ዶላርና ከዚያ በታች ያገኛሉ፡፡ ከሦስት ሰዎች መካከል ለአንዱ በቂ ምግብ ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም እርሻና ምግብ  ድርጅት (ፋኦ) እ.ኤ.አ. በ2010 ባወጣው ሪፖርት ከሰሃራ በታች የሚኖሩ 239 ሚሊዮን አፍሪካውያን ረሃብ እንደሚያጠቃቸው ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ 40 በመቶ ለሚሆኑ አፍሪካውያን በልቶ ማደር ህልም ነው፡፡ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ 80 በመቶ የሚሆኑ አፍሪካውያን እንደ ኃይል ምንጭ የሚጠቀሙት አሁንም ድረስ ባዮማስን ነው፡፡

738 ሚሊዮን የዓለም ሕዝቦች ለንፁህ ውኃ ያላቸው ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 37 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ይኖራሉ፡፡ ካለው የንፁህ ውኃ ተደራሽነት ጉዳይ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ 500 ሚሊዮን አፍሪካውያን ለውኃ ወለድ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሌኒየም ፕሮጀክት እንደሚያሳየው፣ 50 በመቶ የሚሆኑ አፍሪካውያን እንደ ኮሌራ ባሉ ውኃ ወለድ በሽታዎች ይጠቃሉ፡፡

እንደ ወባ ያሉ ወረርሽኞች እስካሁን የአፍሪካውያን ሞት ምክንያት ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እንደ ኢቦላ ያሉ ደግሞ በአንድ ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን ሕይወት በመቅጠፍ አኅጉሪቱን የሞት ቀጣና ያደርጓታል፡፡ እነዚህና ሌሎችም አፍሪካን የረሃብና የችግር ተምሳሌት አድርገዋት ቆይተዋል፡፡

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ችግር ይቺን የችግር ቋት የሆነች አኅጉር ሸሽተው ዕጣ ፈንታቸውን ለመቀየር ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለመግባት በሕገወጥ መንገድ ድንበር ያቋርጣሉ፡፡ አፍሪካ ውስጥ ካለው  ረሃብ ሞት ይሻለናል ብለው በረሃ ሲያቋርጡ በውኃ ጥም መሞትንና በአውሬ መበላትን ይመርጣሉ፡፡

በአፍሪካ ለሌሎች አገሮች የሚተርፍ ሀብት እንዳለ ቢታወቅም ያለውን ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ አውሎ ለችግራቸው መድረስ የማይፈታ ህልም ሆኖ እስካሁን ቆይቷል፡፡ በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዳይሆኑ ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁንም ድረስ ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው ልዩ ዕርዳታ የሚጠብቁ አገሮች መኖር አሳዛኙ የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ሆኗል፡፡

እነዚህ ለዘመናት መቋጫ ያልተገኘላቸው የአፍሪካውያን ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ተብለው ከቀረቡ ሐሳቦች መካከል አንድና ጠንካራ አፍሪካን መፍጠር፣ አገሮች ከብሔራዊ ማንንታቸው፣ ከድንበር ክልላቸው ባለፈ አፍሪካዊነትን እንዲያስቀድሙ፣ አፍሪካውያን ከአንዱ አገር ወደ ሌላው በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ማድረግ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት ጀምሮ የነበረ ነው፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ዓላማ አንድና የተዋሃደች አፍሪካን መፍጠር ነው፡፡ ቅኝ ገዥዎች ለአስተዳደር እንዲመቻቸው ካሰመሯቸው የፖለቲካ ድንበሮች ባለፈ አገሮች አብሮነታቸውንና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ፣ አፍሪካን ለአፍሪካውያን የተመቸቸ የማድረግ ህልም ነበረው፡፡ በመካከላቸው ያለውን የመራራቅና ሥር የሰደደ ብሔራዊነት አጥፍቶ አንድ አፍሪካን መፍጠር ከተቻለ የሰዎች በነፃነት ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ የመኖር ጥያቄ በአገሮች ድንበር አይወሰንም የሚል ራዕይ ያነገበ ነበር፡፡ በድንበር ሳይገደቡ በአፍሪካ ከጥግ እስከ ጥግ የመንቀሳቀስን ጉዳይ በተመለከተ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በግልጽ ያስቀመጠው ነገር ባይኖርም መንፈሱ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡

‹‹የምናጠፋው ጊዜ የለንም፡፡ አሁን አንድ መሆን አለብን አለዚያ እንጠፋለን፤›› የሚለው የክዋሜ ንኩሩማ ታዋቂ ንግግርም ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1963 የተወጠነው በአፍሪካ ምድር በነፃነት የመንቀሳቀስ ጉዳይ ጎልቶ መውጣት የጀመረው ግን እ.ኤ.አ. ከ1980 እስከ 2000 ድረስ ነበር፡፡

በአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው የሌጎስ ፕላን ኦፍ አክሽን መቋቋምን ተከትሎ ነበር በአፍሪካ በነፃነት የመንቀሳቀስ ሐሳብ መጉላት የጀመረው፡፡ የሌጎስ አክሽን ለአፍሪካውያን የጋራ ገበያ መፍጠርና ሥራ ፈላጊ አፍሪካውያን በነፃነት የትም ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተፈጻሚነት አልነበረውም፡፡

እ.ኤ.አ. በ1991 የወጣው የአቡጃ ስምምነትም ሰዎች በአፍሪካ ምድር በነፃነት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ፣ አባል አገሮችም ይህንን የማስፈጸም ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ስምምነቱን ከ55ቱ አባል አገሮች 49ኙ አፅድቀውትም ነበር፡፡ በአፍሪካ አገሮች በነፃነት መንቀሳቀስ፣ መኖርና መቋቋም የሚፈቅዱ ፕሮቶኮል ለማዘጋጀትም ተስማምተው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2001 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ሲቀየር የተዋሃደችና አንድ የሆነች አፍሪካን የመፍጠር ሐሳቡ ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ እ.ኤ.አ. 2004 በዳካር ሴኔጋል ከአፍሪካ ዳያስፖራዎች ጋር በተደረገ ኮንፈረንስ ስለአፍሪካዊ ዜግነትና አፍሪካዊ ፓስፖርት ስለመያዝ አስፈላጊነት በምክረ ሐሳብ ደረጃ ቀርቦ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ አኅጉራዊ ነፃ ገበያ ቀጣና እንዲቋቋም መወሰኑም አንድ ዕርምጃ ነበር፡፡

ውሳኔው ድንበር ተሻጋሪ የሰው ኃይል የመፍጠር ዓላማም ነበረው፡፡ በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ማጠናከርም እንደዚሁ፡፡ በመካከላቸው ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከርም ሰዎች በአፍሪካ ውስጥ በነፃነት መንቀሳቀስ መቻል ወሳኝ እንደሆነም ያሳያል፡፡ ስለዚህም አባል አገሮች ሰዎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት የሚሆኑባቸውን እንደ ቪዛ ያሉ ነገሮችን እንዲያነሱ ይጠይቃል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ የምሥረታ በዓል ላይም የአፍሪካ መሪዎች ሰዎች በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችሉባቸውን መንገዶች እንዲያመቻቹ፣ ይህም የአፍሪካ ዜግነት፣ ፓን አፍሪካኒዝምና የአፍሪካ ህዳሴን ለመፍጠር ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነ ተነግሮ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 በጆሀንስበርግ ደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ጉባዔም በነፃነት የመንቀሳቀስና የአፍሪካ ፓስፖርትን በተመለከተ ገንቢ ውሳኔ ተላልፎም ነበር፡፡

‹‹ዘ አፍሪካ ዊ ወንት›› የሚለው ጠንካራ አንድነት ያላትን አፍረካ የመፍጠር ግብ ያለው አጀንዳም በዚህ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ አጀንዳው እ.ኤ.አ. በ2063 በአኅጉሪቱ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች መካከል ነፃ እንቅስቃሴ ለመፍጠር ዕቅድ ይዟል፡፡ እስከ መጪው ዓመት አጋማሽ ድረስም በአፍሪካ ውስጥ ያለ ቪዛ መንቀሰቀስ እንዲቻልም የተለጠጠ የሚመስል ዕቅድ ይዟል፡፡ እንደ ቤኒን፣ ሩዋንዳ፣ ጋና፣ ሞሪሺየስና ሲሸልስ ሁሉ አፍሪካውያን በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ የሚፈቅዱ አሠራሮችን እንዲዘረጉ ሌሎች አባል አገሮች ተጠያቂ ያደርጋል፡፡

የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፉ የስደት ድርጅት (አይኦኤም) ከአፍሪካ ኅብራት ጋር በመተባበር በዚህኛው ሳምንት መግቢያ ላይ ይፋ ያደረጉት ‹‹ሰዎች በአፍሪካ በነፃነት መንቀሳቀሳቸው የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና ተግዳሮቶች›› የሚለውጥ ጥናት ውጥኑን ከማስፈጸም አንፃር እስካሁን የተመጣበትን ርቀትና ያጋጠሙ ፈተናዎችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

የአይኦኤም ቺፍ ኦፍ ሚሽን ሙሪን አቺን ‹‹ይህ ዓመት ለአፍሪካ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ያስገኘ ነው፡፡ በጥር ወር የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ሦስት ወሳኝ ኩነቶችን አፅድቀዋል፡፡ አንደኛው አኅጉራዊ ነፃ የገበያ ትስስር ነው፡፡ ሲንግል አፍሪካን ኤር ትራንስፖርት ማርኬትና የሰዎች በአፍሪካ በነፃ የመንቀሳቀስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊት በፊርማ የፀደቀው የአፍሪካ የሰው ኃይል የተመለከተው ፕሮግራምም የዚሁ አካል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

82 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካውያን ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ እዚሁ አፍሪካ ውስጥ በአገሮች መካከል የሚደረግ ሆኖ ሳለ ከአገር አገር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከሌሎቹ የዓለም ሕዝቦች በተለየ ከበድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡ በነፃነት የመንቀሳቀስ ጉዳይ ከክዋሜ ኒክሩማ ጊዜ ጀምሮ የተጠነሰሰ ሐሳብ ቢሆንም አሁንም ድረስ በአፍሪካ ውስጥ መንቀሳቀስ በተለይም ለአፍሪካውያኑ ከባድ ነው፡፡ እስካሁን አፍሪካውያን ያለ ቪዛ መንቀሳቀስ የሚችሉባቸው የአፍሪካ አገሮች 20 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡

‹‹ሰዎች  በቀላሉ ድንበር ተሻግረው መንቀሳቀስ እስካልቻሉ ድረስ አኅጉራዊ ንግድና ኢንቨስትመንት ያንን ያህል ሊያደርግ አይችልም፤›› ሲሉ ሙሪን በነፃነት መንቀሳቀስ የሚቻልባቸው አሠራሮች እስካልተዘረጉ ድረስ ለአፍሪካ ዕድገት ርቋት እንደሚቆይ ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2045 በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሰዎች በነፃነት መንቀሳቀስ መቻል ወሳኝ ነው፡፡ በድንበር አካባቢዎች በሕገወጥ ንግድ ላይ ለተሰማሩ 43 በመቶ የሚሆኑ አፍሪካውያንም መሻሻል በነፃነት መንቀሳቀስ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ እያደገ ነው የሚል አዎንታዊ ምልከታ አለ፡፡ የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2017 ባወጣው ሪፖርት ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች ኢኮኖሚ ዕድገት እያሳየ ይገኛል፡፡ አጠቃላይ የአኅጉሪቱ ዕድገት እ.ኤ.አ. በ2018 ወደ 3.2 በመቶ፣ በ2019 ደግሞ ወደ 3.5 በመቶ ከፍ እንደሚልጥ ይጠበቃል፡፡ ይሁንና ዕድገቱ ሁሉንም አካታች አይደለም ሲባል ይተቻል፡፡

ያላት ትኩስና ያልተነካ የወጣት ኃይል ትልቅ ሀብት ለሆናት አፍሪካ ጭላንጭል ተስፋ እየታየ ነው፡፡ ያላትን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብቶች አቀናጅቶ በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋልና ከሌሎች አቻዎቿ እኩል ትሆን ዘንድ የአገሮች ትስስርና ኅብረት ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን ለማሳለጥ እንደ አንድ መፍትሔ የመጣው የሰዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን በበቂ ተፈጻሚ ሊሆን አልቻለም፡፡

ጥናቱ ለተፈጻሚነቱ እንቅፋት ናቸው የሚላቸውን ነገሮች በአራት ይከፍላቸዋል፡፡ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች፣ የአገሮች አቅምና ሀብት ውስን መሆን፣ ብሔራዊ ደኅንነትና የሕዝቦች የጤና ጉዳይ ዋና ዋናዎቹ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

በአገሮች መካከል የሚካሄዱ ጦርነቶችና በመካሄድ ላይ ያሉ ከሳምንታት በፊት አዲስ ምዕራፍ እስኪከፈት ድረስ የኢትዮ ኤርትራ፣ ሩዋንዳ ከብሩንዲ፣ ብሩንዲ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎና ሶማሊያ ከኬንያ ሰዎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት ሆነው የቆዩ አሳዛኝ ክስተቶች ናቸው፡፡ ከአፍሪካዊነት ይልቅ ለአገራዊ ሉዓላዊነትና ለድንበር ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጥበት ሁኔታም በነፃነት መንቀሳቀስ ከባድ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

ውስን የሥራ ዕድል መኖሩም መጤዎች ሥራችንን ነጠቁብን ኑሮ አስወደዱብን የሚል ጥላቻ መፍጠሩም ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተደጋጋሚ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ የሚታየው የዘር ጥላቻን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ አንድ ማሳያ ሆኖ በጥናቱ ቀርቧል፡፡ እንደ ወባና ኢቦላ ያሉ ወረርሽኞችም በአፍሪካ ምድር በነፃ መንቀሳቀስ ቀላል እንዳይሆን በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ የወንጀለኞችና የአሸባሪዎች ጉዳይም አገሮች ለነፃ እንቅስቃሴ ድንበራቸው ክፍት እንዳያደርጉ ትልቅ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

የአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በ2017 አፍሪካውያን በአፍሪካ ምድር በነፃ መንቀሳቀሳቸው የሚያስገኘው ጥቅም፣ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ከሚሠጋው ችግር የበለጠ ጥቅም ያስገኛል የሚል መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በድንበር ያልተከፋፈለች አንድና የተዋሃደች አፍሪካን ለመፍጠር አባል አገሮች ተባብረው ሊሠሩ እንደሚገባ ምክር ቤቱ መክሮም ነበር፡፡

 

Share.

About Author

Leave A Reply